ፕላስቲክ የሚያብላሉት የአፍሪካ ነፍሳት

ዶ/ር ፋቲያ ካሚስ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ ቤተ ሙከራ ምርምር እያደረገች ነው።

እሷ የምትመራው ቡድን ፕላስቲክ የሚበላ ነፍሳት ላይ ነው ጥናት የሚሠራው።

"ጠዋት ስንገባ ሁላችንም ደስ አለን። ፕላስቲኩ ተፈርፍሯል" ትላለች።

ጥቁሩ ነፍሳት ፕላስቲኩን መብላቱ ትልቅ ድል ነው። ነፍሳቶቹ ፕላስቲኩን ከበሉ በኋላ ማብላላት ይችላሉ።

ከነፍሳቱ ሰውነት የሚመነጨው ኢንዛይም ፕላስቲክን ወደ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ይሰብራል።

"3.6 ግራም ስታይሮፎም (ፕላስቲክ) ከ100 እስከ 150 ለሚሆኑ ነፍሳት ሰጥተናል" ትላለች ሞለኪውላር ባዮሎጂስቷ ዶ/ር ፋቲያ።

"አንጀታቸው ውስጥ ከፍተኛ ባክቴሪያ አለ። ይህም ፕላስቲክን ማብላላት ይችላል" ትላለች።

በኬንያ ኢንተርናሽናል ሴንተር ኦፍ ኢንሴክት ፊዝዩሎጂ ኤንድ ኢኮሎጂ ጥናቱ የተጀመረው እአአ በ2020 ነበር።

ዶ/ር ፋቲያ ጥናቱን ሲያደርጉ አሜሪካ ውስጥም ተመሳሳይ ነፍሳት ፕላስቲክ ለማብላላት ጥቅም ላይ እንደዋል አወቁ።

ዶ/ር አንጃ ብራንደን በአሜሪካ በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ጥናቱ ሲሠራ ተሳትፋለች። አሁን ኦሽን ኮንሰርቫንሲ ውስጥ የፕላስቲክ ፖሊሲ ዳይሬክተር ናት።

ሁለት ዓይነት ፕላስቲክ ላይ ነው ጥናት የሠሬሩት።

"ስታይሮፎም ወይም ፖሊስተሪን እንዲሁም ፖሊአንተሊን የፕላስቲክ ዓይነቶች ላይ ምርምር የተደረገው። መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል (ሪሳይክል ለማድረግ) ከባድ የሆኑና አካባቢ የሚበክሉ ፕላስቲኮችን ማብላላት ነበር አላማው" ትላለች።

ፕላስቲክ አካባቢ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት የመላው ዓለም ችግር ነው። ብዝኃ ሕይወት ላይ የሚያሳድረው ጫና ቀላል አይደለም።

የምግብ ሰንሰለትን ያዛባል። ለሰዎች ጤናም ጠንቅ ነው።

በየዓመቱ በዓለም ከ450 ሚሊዮን ቶን በላይ ፕላስቲክ ይመረታል ሲል አወር ወርልድ ኢን ዳታ ድረ ገጽ ይጠቁማል።

ከዚህ ውስጥ 350 ሚሊዮን ቶን ፕላስቲክ ተረፈ ምርት ነው የሚሆነው። ግማሹ ቆሻሻ መጣያ ቦታ ሲወድቅ፣ 19% ይወገዳል፤ 10% መልሶ ጥቅም ላይ ይውላል።

አፍሪካ ከዓለም 5% ብቻ ፕላስቲክ ብታመርትም በአካባቢ ብክለት ከዓለም ሁለተኛዋ አህጉር ናት።

ለዚህ ምክንያት ከሆኑ መካከል አንዴ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮች ናቸው። መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ከፍተኛ ክፍተት አለ።

የፕላስቲክ ተረፈ ምርት ከሚጣልባቸው 50 አገራት 19 የሚገኙት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ነው።

ለምግብ ማቆያ፣ ዕቃ ለማሸግ ወይም ለሌላ አገልግሎትም ስታይሮፎም የፕላስቲክ ዓይነት ጥቅም ላይ ይውላል።

በጣም ውድ ከመሆኑ ባሻገር መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ከሚከብዱትም አንዱ ነው።

ከቆሻሻ ክምሮች አንድ ሦስተኛው ስታይሮፎም ነው።

ፕላስቲክን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ታዋቂ የሆነው ሚስተር ግሪን አፍሪካ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ይገኛል።

በየወሩ 200 ቶን ፕላስቲክ መልሶ ጥቅም ላይ ይውላል።

አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮች በዋናነት ይጠቀሳሉ።

"ብዙ የፕላስቲክ ተረፈ ምርት ነው የምናብላላው። ስታይሮፎም ግን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል እያደረግን አይደለም። ያንን ለማድረግ አቅሙና ቴክኖሎጂው የለንም" ትላለች የተቋሙ ዋና አስተባባሪ ቤኒታ ኦዲምቦ።

ነፍሳቶቹ መፍትሔ ያመጣሉ?

የኬንያው ምርምር ቡድን ተስፋ ሰጭ ውጤት ነው ያገኘው። ሆኖም ግን ነፍሳት ለፕላስቲክ ዘላቂ መፍትሔ ናቸው? የሚለው አጠያያቂ ነው።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነፍሳት ማምጣት የግብርና አካባቢን ሊበክል ይችላል።

ዶ/ር አንጃ በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ጥናት ስትሠራ "በአንድ ቀን ውስጥ የተጣለ የፕላስቲክ ተረፈ ምርትን ለማብላላት 1,000,000 ቢሊዮን ነፍሳት ያስፈልግ ነበር" ትላለች።

ነፍሳት ከሚበሉት ፕላስቲክ ከፊሉን ነው የሚያብላሉት።

"በአካባቢው ጥቃትን የፕላስቲክ ስብርባሪ (ማይክሮፕላስቲክ) እንዲበራት ሊያደርግ ይችላል። ጉዳት ልናደርስ እንችላለን" ትላለች።

ነፍሳት ፕላስቲክ ማብላላት ቢችሉም ብክለቱን ማጥፋት አይችሉም።

"የኛ ውቅያኖስ ነው በዋነኛነት በፕላስቲክ ብክለት የተጎዳው። ከፍተኛ ብክለት በገጠመው በዚህ ውቅያኖስ ውስጥ ደግሞ እነዚህ ነፍሳት ወይም ባክቴሪያዎች የሉም" ትላለች ዶ/ር አንጃ።

ሌላው ጉዳይ ፕላስቲክ በነፍሳት ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ነው።

ነፍሳቱን የሚመገቡ እንሰሳት ላይ የሚያሳድረው ጫናም አሳሳቢ ይሆናል።

የአካባቢ ጥበቃ ሳይንቲስት ጄንሬስ ሙታል "ፕላስቲክ ለመሥራት ከ16,000 በላይ ኬሚካል ጥቅም ላይ ይውላል። እነዚህ ኬሚካሎች እንዴት የነፍሳቱ ሕይወትና የሕይወት ሰንሰለት ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ ጥናት ያስፈልጋል" ይላል።

ነፍሳት የፕላስቲክ ችግርን ይፈታሉ ብሎ ከመጠበቅ የሚጣለውን ፕላስቲክ መቆጣጠር ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሆን ያስረዳል።

"ፕላስቲክ አምራቾች ይህንን ጥናት እንደ ሰበብ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ፕላስቲክን ለማብላላት ተፈጥሯዊ መንገድ አለ ሊሉም ይችላሉ። ይህ ግን ተፈጥሯዊ መንገድ አይደለም። ነፍሳቱ በተፈጥሯቸው የማይበሉትን ፕላስቲክ እየመገብናቸው ነው" ሲል ያክላል።

ዶ/ር አንጃም ነፍሳትን እንደ መፍትሔ መውሰድ ጥንቃቄ ያሻዋል ትላለች።

"አንድ ነፍሳት ወይም ባክቴሪያ ሊያብላላ የሚችለው አንድ ዓይነት ፕላስቲክ ብቻ ነው። አብዛኞቹ ዓለም ላይ የምንጠቀምባቸው ፕላስቲኮች አሁንም መልሰው ጥቅም ላይ አልዋሉም። ስለዚህ የፕላስቲክ ብክለት አካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመግታት ስልታዊ አካሄድ ያስፈልጋል።"

ለአሁኑ ግን የዶ/ር ፋቲያ የጥናት ቡድን ወደቀጣዩ የምርምር ደረጃ ተሸጋግሯል። የነፍሳቱን ምግብ የማብላላት ሂደት እየፈተሹ ነው።

"ሰውነታቸው ውስጥ የሚፈጠውን ኢንዛየም በመውሰድ ለኛ በሚጠቅም መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል እንፈልጋለን" ትላለች።

ነፍሳቱን በቀጥታ ወደአካባቢ ከመልቀቅ ይልቅ ሰውነታቸው ውስጥ ያለውን ኢንዛየም ወይም ባክቴሪያ አስመስሎ ማምረት የተሻለ እንደሆነ ትመክራለች።

በዚህ መንገድ የፕላስቲክ ተረፈ ምርትን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል አንድ አካል ለመሆን የኬንያው ቡድን ተስፋ ሰንቋል።