ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ማዕከል ውስጥ መኖር ምን ይመስላል? ሕዋ ላይ ምን ዓይነት ጠረን አለ?
ባለፈው ሰኔ ነበር ሁለት አሜሪካዊያን ጠፈርተኞች በስምንት ቀናት ወደ ዓለም አቀፉ የጠፈር ምርምር ተቋም ደርሰው ለመመለስ ምድርን ለቀው የሄዱት።
ጠፈርተኞቹ ወደ ሕዋ የተጓዙት በቦይንግ ስታርላይነር መንኩራኩር ነው። ሆኖም ናሳ ይህ መንኩራኩር ጠፈርተኞቹን ይዞ ለመመለስ ብቁ አይደለም አለ።
በዚህም ምክንያት ለስምንት ቀናት የመጠቁት ሱኒ ዊሊያምስ እና ቡች ዊልሞር እስከ አውሮፓውያኑ 2025 ድረስ ሕዋ ላይ ለመቆየት ይገደዳሉ።
ዓለም አቀፉ የሕዋ ምርምር ተቋም (አይኤስኤስ) ስድስት የአልጋ ክፍሎች ያሉት ቤት ያክል ነው ስፋቱ። ከሁለቱ እንግዳ ጠፈርተኞች በተጨማሪ ዘጠኝ ሰዎች በውስጡ ይኖራሉ።
ሱኒ ተቋሙን “ደስተኛ ቦታ” ስትል ትገልፀዋለች።ዊልሞር ደግሞ ሕዋ ላይ በመገኘቱ “ምስጋና” ያቀርባል።
ከምድር 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተንሳፎ መኖር ምን ይመስላል? ልብስ ማጠብስ ይቻላል? ምግብ ከየት ይመጣል? ከሁሉ በላይ ደግሞ “የሕዋ ሽታ” ምን ምን ይላል?
ቢቢሲ ከጠፈርተኞች የሰማውን እንዲህ ያቀርባል።
የጠፈርተኞች የቀን ከቀን ውሎ በአምስት ደቂቃዎች ተከፋፍሎ ምድር ላይ በሚገኝ መቆጣጠሪያ ነው የሚለካው።
በንጋት ነው የሚነቁት።ጠዋት 12፡30 ሀርመኒ ከተባለው የኤቲኤም ማሽን መከለያ ሳጥን ከሚያክል የአልጋ ክፍላቸው ይነቃሉ።
“በጣም ድንቅ አልጋ ነው” ትላለች በአውሮፓውያኑ 2009 እና 2011 ሁለት ጊዜ ወደ ሕዋ ተጉዛ 104 ቀናት አሳልፋ የመጣችው ጠፈርተኛ ኒኮል ስኮት።
እነዚህ የአልጋ ክፍሎች ጠፈርተኞች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚያወሩባቸው ላፕቶፖች ተገጥሞላቸዋል።የግል መገልገያ ዕቃዎች የሚቀመጡበት ኮሮጆም አለው።
ጠፈርተኞች ሽንት ቤት መጎብኘት ካስፈለጋቸው ደግሞ መምጠጫ የተዘጋጀለት ቴክኖሎጂ አለላቸው። ለወትሮው ላብ እና ውሀ ሽንት ተጠራቅሞ ይጣራና የመጠጥ ውሀ ይሆናል።ነገር ግን አሁን ላይ ተቋሙ ባጋጠመው ችግር ምክንያት ሽንት ማጠራቀም ብቻ ነው የሚችሉት።
ቀጥሎ ጠፈርተኞች ወደ ሥራቸው ይገባሉ።ጥገና እና ሳይንሳዊ ሙከራዎች በአብዛኛው በተቋሙ የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው።አይኤስኤስ ስፋቱ እንደ ባኪንግሀም ቤተ-መንግሥት አሊያም እንደ አንድ የአሜሪካ የእግር ኳስ ሜዳ ይሆናል።
“ውስጡ ልክ በርካታ አውቶቡሶች ተገጣጥመው የተሠራ ነው የሚመስለው።ግማሽ ቀን ሙሉ አንድም ሰው ሳናይ ልንቆይ እንችላለን” ይላል ካናዳዊው ጠፈርተኛ ክሪስ ሀድፊልድ።
“ማንም ተነስቶ እንደፈቀደው የሚንሳፈፍበት እና የሚንፈላሰስበት አይደለም።በጣም ትልቅ እና ሰላማዊ ነው።”
አይኤስኤስ ስድስት ቤተ-ሙከራዎች አሉት። ጠፈርተኞች የልብ፣ የአእምሮ አሊያም የደም መለኪያ መሣሪያ ያጠልቃሉ።ይህን የሚያደርጉት ከባድ የሰውነት እንቅስቃሴ የሚጠይቀውን ሁኔታ ለመቆጣጠር ነው።
“የቤተ-ሙከራ እንስሳት ነን ማለት ይቻላል” ትላለች ኒኮል። “ሕዋ ማለት አጥንት እና ጡንቻችን ለፈጣን የእርጅና ሒደት የሚዳርግ ነው።ሳይንቲስቶች ከዚህ ብዙ መማር ይችላሉ።”
ጠፈርተኞቹ ከቻሉ ምድር ያለው መቆጣጠሪያ ከሰጣቸው ጊዜ ቀድመው ሥራቸውን ያጠናቅቃሉ።
ሀድፊልድ እንደሚለው “ግባችን አምስት ነፃ ደቂቃዎች ማግኘት ነው። ይህ ደቂቃ ከተገኘ መስኮት አካባቢ እየተንሳፈፍኩ የሆነ ነገር ሲያልፍ አያለሁ። ወይም ሙዚቃ መፃፍ፣ ፎቶግራፍ ማንሳት እና ለልጆቼ የሆነ ነገር መፃፍ ያስደስተኛል።”
ዕድለኞች ‘ስፔስዎክ’ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ።ይህ ማለት ከተቋሙ ወጥተው በውጭኛው ክፍል መንሳፈፍ ማለት ነው።
ሀድፊልድ ሁለት ጊዜ ሕዋ ላይ ተራምዷል። “በእነዚህ 15 ሰዓታት በኔና በተቀረው አፅናፈ ዓለም (ዩኒቨርስ) መካከል ምንም ነገር አልነበረም።በሕይወቴ እንዲህ ያለ በቃላት ለመግለፅ የሚከብድ አስደናቂ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም።” ይላል።
ነገር ግን ‘ስፔስዎክ’ ያደረጉ ጠፈርተኞች አንዳች ዓይነት ሽታ ይዘው ነው ወደ ተቋሙ የሚመለሱት።
“ምድር ላይ የተለያዩ ሽታዎች አሉን። ሕዋ ላይ አንድ ዓይነት ሽታ ነው ያለው። ይህ ሽታ ይለመዳል” ትላለች በሶቪዬት የምርምር ተቋም ለስምንት ቀናት ሕዋ ላይ የቆየችው የመጀመሪያዋ እንግሊዛዊት ጠፈርተኛ ሄለን ሻርማን።
ጠፈርተኞቹ ወደ ውጭ ሲወጡ ልብሳቸው አሊያም ይዘው የወጡት መሣሪያ ለጨረር ይጋለጣል። ይህ ጨረር ተቋሙ ውስጥ ካለው ኦክሲጅን ጋር ሲጋጭ የሚፈጥረው አንዳች ዓይነት የብረት ሽታ አለው።
ሄለን ወደ ምድር ስትመለስ ነው የዝናብ እና የነፋስ ናፍቆት እንዳጠቃት የገባት። ሕዋ ዝናብም ነፋስም የለውም።ወደ ሕዋ ከሄደች ከ33 ዓመት በኋላ እንኳ የእነዚህ እጦት ምን ያህል ጎድቷት እንደነበር ትናገራለች።
ለረዥም ጊዜ ወደ ጠፈር ምርምር ተቋሙ የሚሄዱ ሰዎች በቀን ለሁለት ሰዓታት የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው። ዜሮ ግራቪቲ (የመሬት ስበት) ባለበት ሥፍራ መኖር አጥንት ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የተዘጋጁ ሦስት ማሽኖች አሉ።ጠፈርተኞች ራሳቸውን ከማሽኑ ጋር ጠፍረው ነው ስፖርት የሚሠሩት።
ኒኮል ስኮት እንደምትለው በጠፈር ምርምር ተቋሙ ያለው ከባድ ሥራ ለላብ ያጋልጣል። ይህ ማለት ልብስ ማጠብ ግድ ነው ማለት ነው። ነገር ግን ተቋሙ ውስጥ የልብስ ማጠቢያ ማሽን የለም።
ደግነቱ ብዙውን ጊዜ ልብሳቸው አይቆሽሽም።ይህ የሚሆነው የመሬት ስበት ባለመኖሩ ምክንያት ልብሳቸው ከገላቸው ስለማይነካካ ነው።ጠፈርተኞቹ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያደርጉት ምግብ ሲመገቡ ልብሳቸው ላይ እንዳይንጠባጠብ ነው።
አዳዲስ ጠፈርተኞች ወደ ተቋሙ ሲመጡ ምግብ፣ ልብስና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ይዘው ሊመጡ ይችላሉ።ናሳም በዓመት የተለያዩ ቁሳቁስ ጫኝ መንኩራኩሮችን ወደ ተቋሙ ይልካል።
ጠፈርተኞቹ ቀኑን ሲተጉ ከዋሉ በኋላ ለእራት አረፍ ይላሉ። ምግብ ብዙውን ጊዜ የሚቀርበው በቆርቆር ታሽጎ ነው።ከዚያ በአገራት ስም ዝርዝር ይከፋፈላል።
ልክ እንደ ወታደር ‘ራሽን’ ነው የምትለው ኒኮል በጣም ትወድ የነበረው ምግብ የጃፓን ከሪ አሊያም የሩሲያ ሾርባ እንደነበር ታወሳለች።አንዳንድ ጊዜ ቤተሰብ ከምድር ምግብ አሽጎ ይልካል።
አብዛኛውን ጊዜ ጠፈርተኞቹ ያላቸውን ምግብ ይጋራሉ።
ጠፈርተኞች ሲመረጡ ግላዊ ባሕርያቸው ጭምር ታይቶ ነው። ታጋሽ፣ ዘና እና ረጋ ያሉ እንዲሁም በቡድን መሥራት የሚችሉ ግለሰቦች ይመረጣሉ።ይህ የሚሆነው በጠፈርተኞች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር ነው።
እንቅልፍ ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም።እርግጥ ነው ለእንቅልፍ የተመደበው ሰዓት ስምንት ነው። ነገር ግን ካርበን ዳይኦክሳይድ የሚበትኑት ማሽኖች ሌሊቱን ሙሉ ድምፅ ያወጣሉ።
አብዛኛዎቹ ጠፈርተኞች እንቅልፍ እምቢ ሲላቸው በመስኮት በኩል ምድር የተባለችውን ቤታቸውን ከ400 ኪሎ ሜትር ርቀት እያማተሩ ማየትን ይመርጣሉ።
ወጣም ወረደ በስተመጨረሻ አይኤስኤስን ለቆ የመሄጃው ጊዜ ይደርሳል።ሆኖም ሁሉም ጠፈርተኞች ድጋሚ ዕድሉን ቢያገኙ ተመልሰው ለመሄድ አያመነቱም።