ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዚደንት ባይደንን በወሲባዊ ጥቃት የከሰሰችው አሜሪካዊት የሩሲያ ዜግነት ጠየቀች
የአሜሪካውን ፕሬዚደንት ጆ ባይደንን በወሲባዊ ጥቃት የከሰሰችው አሜሪካዊት ወደ ሞስኮ በመሄድ የሩሲያ ዜግነት እንዲሰጣት ጠየቀች።
የ59 ዓመቷ ታራ ሬድ በሩሲያ ውስጥ ደኅንነት እንደተሰማትና እዚያ መቆየት እንደምትፈልግ በመንግሥት ለሚተዳደረው የሩሲያ የዜና አውታር ተናግራለች።
ሬድ እንደ አውሮፓውያኑ 1993 በኮንግረንስ ቢሮ ስትሰራ በነበረበት ወቅት በባይደን ጥቃት ተፈፅሞብኛል ብላለች።
ፕሬዚደንት ባይደን ግን “ በጭራሽ አልሆነም” ሲሉ የቀረበባቸውን ክስ አጥብቀው ተቃውመዋል።
ሬድ፣ ባይደን በደላዌር ሴናተር በነበሩበት ወቅት ረዳታቸው ሆና ሠርታለች።
በአውሮፓውያኑ 2020 ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ዘመቻ በተካሄደበት ወቅትም፣ ሬድ የ29 ዓመት ወጣት ሳለች በካፒቶል ሂል መተላለፊያ ላይ በፕሬዚደንቱ ጥቃት እንደተፈፀመባት መናገሯን ተከትሎ ጉዳዩ የመገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ወደ ግድግዳው አስገድደው በማስጠጋት እጃቸውን በሸሚዟ እና በቀሚሷ ውስጥ በመክተት ጥቃት እንደፈፀሙባት በመግለጽ ባይደንን ከሳለች።
“ በረጅም ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሞስኮ ደርሸ ከአውሮፕላን ስወርድ ደኅንነት ተሰማኝ። እንደምሰማና እንደምከበር ተሰማኝ” ስትል ሬድ ለሩሲያው መገናኛ ብዙኃን ስፑትኒክ መናገሯን ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።
ሬድ አሜሪካን ለቃ የወጣችው የሪፐብሊካን ፖለቲከኛ አደጋ ላይ እንደሆነች ከነገራት በኋላ እንደሆነም ገልጻለች።
“ ከሩሲያ ፌደሬሽን ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያን ዜግነት ለማግኘት ማመልከት እፈልጋለሁ።ጥሩ ዜጋ ለመሆንም ቃል እገባለሁ” ያለች ሲሆን የአሜሪካ ዜግነቷንም እንደምትጠብቅ ተስፋ እንደምታደርግ ተናግራለች።
በ2019 እና በ2020 ፕሬዚደንት ባይደንን አላስፈላጊ በሆነ መንካት ፣ ማቀፍ እና መሳም ፊት ለፊት ወጥተው ከከሰሱ በርካታ ሴቶች መካካል ሬድ አንዷ ነበረች።
ምንም እንኳን የተመዘገበ ነገር ባይገኝም እንዲሁም ቅሬታዋ ላይ ምርመራ መደረግ አለመደረጉ ግልጽ ባይሆንም ሬድ ቅሬታዋን ማቅረቧን ገልጻለች።
የባይደን ቃል አቀባይ በበኩላቸው ሴቶች የመሰማት መብት እንዳላቸው እንደሚያምኑ ገልጸው፣ የቀረበው ክስ ግን "በፍጹም አልተከሰተም" ብለዋል።