ካረን ማክዱገል፡ ከትራምፕ ጉዳይ ጋር የተያያዘችው ሁለተኛዋ ሴት ማን ናት?

የዶናልድ ትራምፕ የክስ መዝገብ ትኩረቱን ያደረገው ለወሲብ ፊልም ተዋንያኗ ስቶርሚ ዳንኤልስ ከተከፈለ ክፍያ ጋር ነው። ዐቃቤ ሕግ ግን የሌላ ሴትንም ስም አንስቷል።

ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ትራምፕ ካረን ማክዱገል ለተባለች የቀድሞ ሞዴል ክፍያ ፈጽመዋል።

ማክዱገል በወንዶች የሕይወት ዘዬ ላይ በሚያተኩረው 'ፕሌይቦይ' የመዝናኛ መጽሔት ላይ ሞዴል ነበረች። ከትራምፕ ጋር ግንኙነት እንዳላት ገልጻ ነበር።

ስለ ማክዱገል የምናውቀውንና በዚሀ ጉዳይ ላይ የተካተተችበትን መንገድ እንቃኛለን።

የተወለደችው በጋሪ ኢንዲያና ቢሆንም በኋላ ላይ ወደ ሚቺጋን አቅንታለች። ማክዱገል ወደ ሞዴሊንግ ሙያ የገባችው የዋና ልብሶችን ለማስተዋወቅ በተወዳደረችበት ወቅት ነበር።

በኋላም የስፖርት ሞዴል ለመሆን በቅታለች። እአአ በ1999 ወንዶች ላይ ትኩረት በሚያደርገው 'ፊትነስ ማጋዚን' የፊት ገጽ ላይ በመውጣት የመጀመሪያዋ ሴት ሆናለች። በቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ላይም ተሳትፋለች። ቻርሊስ ኤንጅልስን ጨምሮ ፊልሞች ላይ አነስተኛ ሚና ተሰጥቷት ተጫውታለች።

ኒው ዮርክ እአአ በ2006 እንደዘገበው ሎስ አንጀለስ ውስጥ ቀረጻ ላይ ሆና ነበር ከትራምፕ ጋር የተገናኘችው።

በወቅቱ ባለትዳር የነበሩት ትራምፕ “በፍጥነት እንደወደዱኝ፣ ምን ያህል ቆንጆ እንደሆንኩ . . . ያወሩኝ ጀመር” ስትል ትገልጻለች።

ከትራምፕ ጋርም ለ10 ወራት የዘለቀ ግንኙነት እንደነበራት ገልጻለች። በወር ውስጥ “በትንሹ አምስት ጊዜ እንደሚገናኙ” እና ግንኙነቱ በፍቅር እና በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ለሲኤንኤን ተናግራለች።

ማክዱገል የ2016 ምርጫ በተቃረበበት ወቅት 150 ሺህ ዶላር ያስገኘላትን ስምምነት ከናሽናል ኢንኳረር ጋር በመፈራረም ታሪኳን ለጋዜጣው ብቻ ለመናገር ተስማማች።

ስምምነቱ ስለግንኙነታቸው በአደባባይ በይፋ እንዳትናገር አገዳት።

ታሪኳ ሳይታተም ከመቅረቱም በላይ ማክዱገል ስል ግንኙነቱ ተታላ ዝም እንድትል መደረጉን አስታወቀች።

አንድን ታሪክ ገዝቶ እያወቁ እንዳይወጣ ማድረግ "catch and kill" (ይዞ ማፈን) ይባላል።

ናሽናል ኢንኳረር ይህንን ያደረገው በትራምፕ ዙሪያ የሚሰራጩ አፍራሽ መረጃዎችን ለማፈን ነው።

የምርጫ ዘመቻ የፋይናንስ ጉዳዮችን የሚከታተለው የአሜሪካ ፌደራል የምርጫ ኮሚሽን ኢንኳረር የምርጫ ህግን በመጻረር የማክዱገልን ታሪክ ገዝቶ አፍኖታል በሚል በ2021 አስታውቋል።

ለማክዱገል የተከፈለው ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ ለምርጫ ዘመቻ የዋለ መሆኑን ጠቅሷል። ናሽናል ኢንኳረርም 187500 ዶላር ቅጣት ተከናንቧል።

እንደ ድረ ገጿ ከሆነ ማክዱገል ራሷን ሞዴል፣ አምደኛ እና ተሟጋች ስትል ትገልጻለች።

በ2018 የትራምፕ ሚስት ሜላኒያን “ይቅርታ። እኔ ላይ እንዳይደረግብኝ የምፈልገው ነው” ሰትል በይፋ ይቅርታ ጠይቃለች።

“ወደ ኋላ ስመለከተው የነበርኩበት ስህተት እንደነበር አውቃለሁ። በጣም ይቅርታ። መደረግ የሌለበት እንደሆነ አውቃለሁ’ ብላለች።

ትራምፕ ከማክዱገል ጋር ግንኙነት ነበራቸው መባሉን አይቀበሉትም።

ትራምፕ የሚጠየቁበት ብቸኛው ጉዳይ ስቶርሚ ዳንኤልስ ዝም እንድትል ክፍያ ፈጽመዋል በሚል ነው።

ዓቃቤ ህግ የማክዱገልን ጉዳይ የያዘው ለስቶርሚ ዳንኤልስ መዝገብ በተጨማሪ ማስረጃነት ነው።

ትራምፕ የቀረባበቸው ክሶች በሙሉ አልፈጸምኩም ሲሉ ተከተራክረዋል።