ከሰሞኑ የታሰሩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና የቀረቡባቸው ክሶች

በቅርቡ የፌደራል መንግሥት እና የአማራ ክልል እያካሄድን ያሉትን 'የሕግ ማስከበር ዘመቻ' ተከትሎ የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር ከ16 በላይ ሆኗል።
ከእነዚህም መካከል በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ውስጥ በጋዜጠኝነት ሥራቸው የሚታወቁት ተመስገን ደሳለኝ፣ ያየሰው ሽመልስ፣ መዓዛ መሐመድ እና በቃሉ አላምረው የሚገኙበት ሲሆን አብዛኞቹ ሁከትና ብጥብጥ ማነሳሳት በሚል ክስ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ከሰሞኑ በርካታ ጋዜጠኞች ለእስር መዳረጋቸውን ተከትሎ የሚዲያ ባለሙያዎች እስር እንዳሳሰባቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የአሜሪካ መንግሥት እና የጋዜጠኖች መብት ተከራካሪ ድርጅቶች መግለጫ አውጥተው ነበር።
ተመስገን ደሳለኝ- በቅርቡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ጋር 'የጄኔራሉ ምስጢሮች' በሚል ቃለ መጠይቅ አድርጎ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በቁጥጥር ስር የዋለው ግንቦት 18/2014 ዓ.ም ነበር።
የፍትህ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተርና መስራች 'ገንዘብ ተከፍሎት ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት' ተጠርጥሮ ግንቦት 19/2014 ዓ.ም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ ነበር።
ጋዜጠኛው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሕዝቡ ዘንድ አመኔታ እንዲያጣ አድርጓል የሚል ክስም የቀረበበት ሲሆን፣ የጋዜጠኛው ጠበቃ የደንበኛው ጉዳይ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ወይም በሚዲያ ሕጉ መሰረት እንዲታይላቸውና ዋስትና እንዲፈቀድለት ጠይቀው ነበር።
ተመስገን ሰኞ ዕለት በድጋሚ ችሎት ፊት የቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱ የ10 ቀናት የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ በጠበቃው በኩል የቀረበ የዋስትና ጥያቄን ውድቅ አድርጎታል።
በተጨማሪም በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ይታይ የሚለው ጉዳይ ላይ ምርመራው ገና የተጀመረ በመሆኑ ሰኞው ዕለት መወሰን እንደማይቻል ገልጿል።
አነጋጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመፃፍ የሚታወቀው ተመስገን፤ ገዢውን ፓርቲ፣ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናትን የሚተቹ ጽሁፎችን በማውጣት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
በተለይም የፍትህ መጽሔት መከላከያን አስመልክቶ ምስጢራዊ ሰነድ አትሟል በሚል ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ይታወሳል።
ተመስገን ደሳለኝ ጥቅምት 4/2013 ዓ.ም ሐሰተኛ ወሬ በማሰራጨት በሚል ክስ ለእስር ተዳርጎ የነበረ ሲሆን ከአንድ ቀን ቆይታ በኋላ ተፈትቷል።
ተመስገን ደሳለኝ በሚጽፋቸው ፅሁፎች ለሦስት ዓመታት ያህል ታስሮ ከዝዋይ ማረሚያ ቤት የወጣው ጥቅምት 2010 ዓ.ም ነበር። በሃገሪቷ መንግሥት እና ህገ መንግሥታዊ ስርዓት ላይ አመፅ በማነሳሳት፣ የመንግሥት ስም በማጥፋትና፣ በሃሰተኛ ዜናዎችን በማሰራጨት በሚል ክስም ነው የታሰረው።
ተመስገን በእስር በነበረበት ወቅት "ጊዜ ለኩሉ" የሚል መፅሃፍ የጻፈ ሲሆን ከመፈታቱ በፊትም ለህትመት በቅቷል። ከዚህ መፅሃፍ በተጨማሪ “የፈራ ይመለስ” እንዲሁም “የመለስ አምልኮ” የሚሉ መፅሃፍቶችን ለንባብ አብቅቷል ።
ከፍትህ በተጨማሪ አዲስ ታይምስ፣ ልዕልና እንዲሁም ፋክት መጽሄት የሰራባቸው መጽሄቶች ናቸው።
ያየሰው ሽመልስ፡ ኢትዮ-ፎረም የተባለ የዩቲዩብ ሚዲያ መስራች የሆነው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በቁጥጥር ስር የዋለው ግንቦት 18/2014 ዓ.ም ነበር።
ያየሰው ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት፣ ሕዝብ በፌደራል መንግሥት ላይ እንዲያምፅ በመቀስቀስ እና ሃይማኖት ከሃይማኖት ጋር በማጋጨት፣ አገር እንዳይረጋጋ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው በሚል የተከሰሰ ሲሆን፣ ለዚህም ተግባሩ ገንዘብ ተከፍሎታል ሲል ፖሊስ ከሶታል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ግንቦት 19/2014 ዓ.ም በዋለው ችሎትም ለፖሊስ 10 የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል። በዚህ ችሎት ላይ የሚዲያ እና የኢኮኖሚ ጦርነት እንደታወጀና ይህንንም ስውር ቡድን የሚመራው ተጠርጣሪው ያለበት ኃይል ነው ብለዋል መርማሪ ፖሊሶች።
ጋዜጠኛ ያየሰው ከዚህ ቀደምም ሁለት ጊዜ ለእስር ተዳርጎ የነበረ ሲሆን የሽብር ክስም ቀርቦበት ነበር። መጋቢት 2012 ዓ.ም ለእስር ተዳርጎ የነበረው ያየሰው በትግራይ ቴሌቪዥን ሳምንታዊ የፖለቲካ ፕሮግራም አዘጋጅ እንዲሁም በፍትህ መጽሔትም ሳምንታዊ አምድ ነበረው።
በወቅቱም የቀረበበት ክስ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዙሪያ ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት በሕዝብ ላይ ድንጋጤ ፈጥሯል የሚል ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የፀረ- ሽብር ሕጉን በመጣስ ወንጀል ፖሊስ ከሶት የነበረ ቢሆንም ለአንድ ወር ገደማም ታስሮ ሚያዝያ አጋማሽ ላይ ተፈትቷል።
ለሁለተኛ ጊዜም ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር ታስሮ የነበረ ሲሆን፣ የተጠረጠሩበትም ወንጀል “ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሳዋል” በሚል ነበር።
ያየሰው በአፋር ክልል በአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ለ49 ቀናትም ከታሰረ በኋላ በዋስትና ከእስር ወጥቷል።
በቃሉ አላምረው- አልፋ ቴሌቪዥን የተሰኘ የዩቲዩብ ሚዲያ መስራች እና ባለቤት የሆነው በቃሉ አላምረው ግንቦት 19/ 2014 ዓ.ም በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን በነገታውም ፍርድ ቤት ቀርቧል።
ጋዜጠኛው ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል ተጠርጥሮ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረበ ሲሆን የ12 ቀናት ምርመራ ቀጠሮም ለፖሊስ ተሰጥቷል።
መንግሥት እንዲጠላና ሃይማኖታዊ ግጭቶች እንዲፈጠሩ እየሰራ ነው ሲል ፖሊስ ወንጅሎታል።
በቃሉ ከዚህ ቀደም ጥቅምት 2013 ዓ.ም ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት እና የመንግሥትን ስም በማጥፋት ወንጀል ለ16 ቀናት ታስሮ በዋስ ተፈትቷል።
በወቅቱ አውሎ ሚዲያ የተሰኘ የዩቲዩብ ሚዲያ የነበረው በቃሉ እንደገና ከሌሎች የኢትዮ ፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞች ጋር ለእስር ተዳርጓል።
በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ በሚገኝ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ለ49 ቀናት በአስእር ላይ ቆይቶም ነሐሴ 12/2013 ዓ.ም በዋስ መፈታቱ ይታወሳል።
ከእስር ከተፈታም በኋላ አልፋ ሚዲያ በሚል አቋቁሞ ከሰሞኑ ብልጽግና ተከፋፍሏል፣ የብልጽግና ዘመን የጨለማ ዘመን ነው፣ የኃይል አፈና እርምጃዎች ሊቆም ይገባል የሚሉ ፕሮግራሞችን ሰርቷል።
መስከረም አበራ፡ ኢትዮ ንቃት የተሰኘ የዩቲዩብ ሚዲያ መስራችና ባለቤት የሆነቸው መስከረም አበራ በቁጥጥር ስር የዋለችው ግንቦት 13/2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ነበር።
በባሕር ዳር የነበረ አንድ ጉባኤን ተሳትፋ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ስር የዋለችው መስከረም ግንቦት 16/2014 ዓ.ም. ሕዝባዊ አመፅ በመቀስቀስ ወንጀል ፍርድ ቤት የቀረበች ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 29/2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።
ፖሊስ የአማራ ክልል ከፌደራል መንግሥቱ እንዲነጠል እና ፋኖ እና የፌደራል መንግሥቱ እንዲጋጭ በሚዲያዋ ቀስቅሳለች የሚል ክስ አሰምቷል።
በቅርቡ በሚዲያዋ ከተሰሩ ፕሮግራሞች መካከል ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ያሳሰረው ደምባደምብ፣ መልዕክት ለጄኔራል አበባው ታደሰ፣ ጎንደር ለምን ለቀውስ ተመረጠች? አፈንጋጩ የአማራ ብልጽግና ባለሥልጣናትን እንዴት እንያቸው የሚሉ ይገኙበታል።
መስከረም በሐዋሳ ዩኒቨርስቲና በዲላ ዩኒቨርስቲ የታሪክና ሥነ ዜጋ መምህርት የነበረች ሲሆን፣ ከዚህ ቀደምም ስለ ሥልጣኔ እና የዘውግ ፖለቲካ ስረ መሰረቶች የተባሉ መጻህፍትንም አሳትማ ለንባብ አብቅታለች።
መስከረም አበራ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተለይም “አባይ ሚዲያ” እና “የኔታ ቲዩብ” በተባሉ የዩቲዩብ ሚዲያዎች ላይ በወቅታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሰላ ትችት በመስጠት ትታወቃለች።
መዓዛ መሐመድ
ሮሃ ሚዲያ የተሰኘወ የዩቲዩብ ሚዲያ መስራች የሆነችው መዓዛ መሃመድ በቁጥጥር ስር የዋለችው ግንቦት 20/2014 ዓ.ም ነበር ።
መዓዛ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርባ በሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል ክስ ሰኞ ግንቦት 22/2014 ዓ.ም ፍርድ ቤት የቀረበች ሲሆን ፍርድ ቤቱም ሰባት የምርመራ ቀናትን ፈቅዷል።
ጋዜጠኛዋ ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲያጣ እና አገር እንዳይረጋጋ ገንዘብ ተከፍሏት እየሰራች እንደሆነ ጠርጥሬያታለሁ ብሏል ፖሊስ።
ከዚህ ቀደም ታኅሣሥ 2/2014 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውላ የነበረችው መዓዛ ከሳምንታት እስር በኋላም መፈታቷ ይታወሳል።
መዓዛ ከዚህ ቀደም አባይ ሚዲያ በተሰኘ የዩትዩብ ገጽ ብሎም በቅርቡ ራሷ ባዋቀረችው 'ሮሃ' የተሰኘ የዩትዩብ መድረክ ላይ በወቅታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዝግጅቶችን ስታቀርብ ቆይታለች።
በሮሃ ላይ ከሰሞኑ ከተሰሩ ፕሮግራሞች መካከል "ከህወሓት ይልቅ ብልጽግናን እጸየፈዋለሁ"፣ ከኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ፣ የጎበዜ ሲሳይ ያልተሰሙ የዘጠኝ ቀናት ሚስጥሮች፣ እስርና አፈረናው ተባብሶ ቀጥሏል፣ የአቶ ክርስቲያን ደሳለኝ ሕዝባዊ ጥሪ የሚሉ ይገኙበታል።
ሰለሞን ሹምዬ- በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን የእርስ በርስ ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ በመቃወምና ጦሱ ያመጣውን ጫና ላይ በመናገር የሚታወቀው የገበያኑ ሚዲያ መስራች ሰለሞን ሹምዬ በቁጥጥር ስር የዋለው ግንቦት 12/2014 ዓ.ም ነው።
ሰለሞን በሁከትና ብጥብጥ ወንጀል ሁለት ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሰኞ ግንቦት 22/2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ሰባት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቅዷል።
ሰለሞን ሰላምን በተመለከተ አማራጭ በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን በቅርቡም ሰላም ያጣነው ለምን እና በማን ምክንያት ነው? ፈላጭ ቆራጭነት ወይስ? የጦርነቱ ዓላማ ምንድን ነው? የአዲስ አበባ ካቢኔ ተጠሪነቱ ለማን ነው? ስንት ሰው መሞት አለበት? የሚሉ ፐሮግራሞችን ሰርቷል።
ሰለሞን ሹምዬ ከዚህ ቀደም ሻይ ቡና የተሰኘና በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን ሻይ ቡና የተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ነበረው።
ከእነዚህ ጋዜጠኞችም በተጨማሪ ግንቦት 11/2014 ዓ.ም አሻራ የተሰኘ የዩቲዩብ ቻናል አምስት ባልደረቦች እንዲሁም አራት የንስር ኢንተርናሽናል ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኞች ታስረዋል።
አሻራ ሚዲያ በቅርቡ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች ላይ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ፣ የመንግሥት ተቺዎች እስርና የመኖሪያ ቤት ጉዳዮችን አስመልክቶ የነበረውን ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ዘግቦ እንደነበር የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ የሲፒጄ የሰሞኑ ግምገማ ያመለክታል።
ሦስት ጋዜጠኞችና ሁለት የካሜራ ባለሙያዎች ግንቦት 11/2014 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከባህር ዳር 185 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ንፋስ መውጫ ከተማ እስር ቤት ተዘዋውረው ቤተሰቦቻቸውንም ሆነ ጠበቆቻቸውንም እንዳላገኙ ሲፒጄ ጠቅሷል።
የንስር አራት ጋዜጠኞችና ሠራተኞች ግንቦት 12/2014 ዓ.ም. ባህር ዳር ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ ሁለቱ በከተማው በሚገኝ እስር ቤት ሁለቱ ደግሞ በንፋስ መውጫ እንደሚገኙም ሲፒጄ አስፍሯል።
ንስርም በተመሳሳይ መልኩ በፋኖ ታጣቂዎች ላይ መንግሥት እየወሰደው ያለውን እርምጃ እንዲሁም የዘ ኢኮኖሚስት የኢትዮጵያ ዘጋቢ ቶም ጋርድነር ፈቃድ መሰረዝን አስመልክቶ ዘገባዎች እንደሰራ ሲፒጄ አይቷል።
"የጋዜጠኞቹ እስር ለኢትዮጵያ አንድ እርምጃ ወደፊት፣ ሦስት እርምጃ ወደኋላ የሚመልስ ነው። መንግሥት ለፕሬስ ነፃነት እንዲሁም ዜጎች ከተለያዩ ምንጮች መረጃ የማግኘት መብት ግድ እንደሌለው የሚያሳይ ነው" በማለት የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ አንጀላ ኪውንታል ተናግረዋል።
አስተባባሪዋ አክለውም ባለሥልጣናቱ ሁሉንም ጋዜጠኞች በአፋጣኝ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
"ባለሥልጣናቱ ጋዜጠኞቹን ያለምንም ክስ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የዘፈቀደ እስራት፣ ጭቆና እና ሳንሱር ሳይፈሩ ሪፖርት እንዲያደርጉ መንግሥት ማረጋገጥ አለበት" ብለዋል።
እነዚህ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በፀጥታ ኃይሎች የተያዙት ግለሰቦችን በተመለከተ ከመንግሥት በኩል የታሰሩት ጋዜጠኞች ሳይሆኑ በተለያየ በሕገወጥ ድርጊት ላይ የተገኙ ናቸው ብሏል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ ታሳሪዎቹን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በማለት እስሩ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ሲፒጄ አስሩን በተመለከተ ማብራሪያ የጠየቃቸው የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ በሰጡት ምላሽ “ከሙያቸው ጋር በተያያዘ የታሰሩ ጋዜጠኞች የሉም” በማለት፣ ጋዜጠኞቹ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎቹ “ፖሊስ ወንጀል ስለመፈፀማቸው መረጃ ስላለው” በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ገልጸዋል።












