ታጣቂ ወሮበሎች 4,000 አስረኞች ባስመለጡባት ሄይቲ የአስቸኳይ ጊዜ ታወጀ

የታጠቁ ወሮበሎች በሄይቲ በዋና ከተማዋ ፖርት ኦው ፕሪንስ የሚገኝን ዋነኛ እስር ቤት ወረው 12 ሰዎች ከተገደሉ እና 4,000 የሚሆኑ እስረኞችን ካመለጡ በኋላ ለ72 ሰዓታት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአገሪቱ ታወጀ።

የታጣቂ ወሮበላ ቡድኖች መሪዎች ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለጉብኝት ወደ ኬንያ የተጓዙት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪየል ሄንሪ ሥልጣን እንዲለቁ ለማስገደድ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሄይቲ መንግሥት ከእሁድ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይፋ ባድረገበት መግለጫው፣ በዋና ከተማዋ ፖርት ኦው ፕሪንስ እና በአቅራቢያዋ በምትገኝ ሌላ ከተማ የሚገኙ እስር ቤቶች በታጣቂዎች መወረራቸውን አስታውቋል።

ጨምሮም “ለሕግ ተገዢ ያለመሆን” ድርጊት ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት መሆኑን አመልክቶ፣ ከሰኞ ጀምሮ ከምሽት ሁለት ሰዓት አንስቶ የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን አሳውቋል።

ከአውሮፓውያኑ 2020 አንስቶ በታጣቂ ወሮበበላ ቡድኖች አማካይነት በሚካሄዱ ግጭቶች በአገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

በአገሪቱ የሚገኝ አንድ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ እንደተናገረው በእስር ቤቱ ውስጥ ከነበሩ 4,000 ወንድ ታሳሪዎች መካከል አብዛኞቹ አምልጠው ወጥተዋል።

ታስረው ከነበሩት ውስጥም ከሦስት ዓመት በፊት ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆቪኔል ሞይስ ግድያ ጋር በተያያዘ የተከሰሱ የወሮበላ ቡድን አባላት ይገኙበታል።

በአህጉረ አሜሪካ ውስጥ በእጅጉ ድሃዋ አገር በሆነችው ሄይቲ በታጣቂ ቡድኖች አማካይነት የሚፈጸመው ጥቃት ከቅርብ አመታት ወዲህ ተባብሷል።

የዋና ከተማዋ ፖርት ኦው ፕሪንስን 80 በመቶ ክፍል የተቆጣጠሩት የታጠቁ ወሮበሎች ጠቅላይ ሚኒስትር አሪየል ሄንሪን ከሥልጣን ለማስወገድ ፍላጎት አላቸው፥

በአገሪቱ አዲስ ብጥብጥ የተቀሰቀሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሄይቲ ይሰማራል የተባለውን በኬንያ የሚመራ የበርካታ አገራት የፀጥታ ኃይል ስምሪትን በተመለከተ ለመወያየት ባለፈው ሐሙስ ወደ ናይሮቢ በተጓዙበት ጊዜ ነው።

በቅጽል ስሙ “ባርቢኪው” የተባለው የወሮበሎች ቡድን መሪው ጂሚ ቼርዤር የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከሥልጣን ለማስወገድ የተቀናጀ ጥቃት መከፈቱን ገልጿል።

የቀድሞው የፖሊስ መኮንን እና በዋና ከተማዋ ከተፈጸሙ በርካታ ጭፍጨፋዎች ጀርባ አለበት የሚባለው ይህ የወሮበሎች ቡድን መሪ “በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እና በዋና ከተማዋ ፖርት ኦው ፕሪንስ የምንገኝ ታጣቂ ቡድኖች አንድነት ፈጥረናል” ብሏል።

ታጣቂ ቡድኖቹ በእስር ቤቱ ላይ በፈጸሙት ጥቃት አራት ፖሊሶችን ገድለው አምስት አቁስለዋል። በዋና ከተማዋ ያለው የፈረንሳይ ኤምባሲ ዜጎቹን በከተማዋ ውስጥ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ መክሯል።

የሄይቲ ፖሊሶች ማኅበር የእስር ቤቱን ጥበቃ ለማጠናከር የአገሪቱ ሠራዊት ድጋፍ እንዲያደርግለት ከጠየቀ በኋላ ነበር ቅዳሜ ዕለት የወሮበሎቹ ቡድን እስር ቤቱን የወረረው።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ከጥቃቱ በኋላ እሁድ እስር ቤቱ ክፍት የነበረ ሲሆን፣ በስፍራውም ጠባቂ ፖሊሶች አልነበሩም። ሪፖርቱ ጨምሮም ለማምለጥ የሞከሩ የሦስት እስረኞች አስከሬን በግቢው ውስጥ መውደቁን አመልክቷል።

አንድ በእስር ቤቱ በበጎ ፈቃደኝነት የሚሠራ ግለሰብ ለዜና ወኪሉ እንደተናገረው፣ በቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ግድያ የታሰሩ የቀድሞ የኮሎምቢያ ወታደሮችን ጨምሮ 99 እስረኞች፣ በተኩስ ልውውጡ መካከል እንገደላለን ብለው በመፍራት በእስር ክፍላቸው ውስጥ ተገኝተዋል።

ከፕሬዝዳንት ሞይስ ግድያ በኋላ በሄይቲ ውስጥ የሚካሄደው ግጭት ተባብሷል። በአገሪቱ ከአውሮፓውያኑ 2016 ወዲህ ምርጫ ተካሂዶ የማያውቅ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ ከተገደሉ በኋላ በቦታቸው ሌላ ሰው አልተተካም።

በአገሪቱ ፖለቲከኞች መካከል ተደርሶ በነበረ ስምምነት መሠረት በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ምርጫ እንደሚካድ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን እንደሚለቁ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም።

ጥር ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳለው ግድያዎችን፣ የአካል ጉዳትን እና እገታን ጨምሮ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በሄይቲ ውስጥ በተፈጸሙ የታጣቂ ወሮበሎች ጥቃቶች ምክንያት 8,400 ሰዎች ሰለባ ሆነዋል። ይህም ቀደም ካለው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።