ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሙሴቬኒ ልጅ የሆኑት የኡጋንዳ ጦር ከፍተኛ መኮንን አዲስ አበባ ገቡ
የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ የሆኑት የአገሪቱ ጦር ከፍተኛ የጦር መኮንን ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ አዲስ አበባ ገቡ።
የኡጋንዳ የምድር ጦር አዛዥ የሆኑት ጄኔራል ሙሆዚ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ መግባታቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጄኔራሉ አዲስ አበባ ሲደርሱ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ ተመስገን ጥሩነህ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ከጄኔራሉ በተጨማሪ የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኦኬሎ ኦሪየም እና ሌሎች የደኅንነትና ወታደራዊ ከፍተኛ አመራሮች አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
የኡጋንዳ መገናኛ ብዙኃን ጄኔራሉ ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቀረበላቸውን ግብዣ ተከትሎ ነው ሲሉ ዘግበዋል።
ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንደሚገናኙም በስፋት ተዘግቧል።
ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው የኢትዮጵያ እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ በሚለጥፏቸው ጽሑፎች ብዙ አነጋጋሪ ናቸው።
አባታቸውን ሊተኩ ይችላሉ የሚባሉት የ48 ዓመቱ ጎልማሳ፣ በአንድ ወቅት ጡረታ ልወጣ ነው ካሉ በኋላ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆነው ነበር።
ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው አገራት ሲሆኑ በተለይ ከአባይ ወንዝ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ ኢትዮጵያ በውሃው የመጠቀም መብቷን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በይፋ ድጋፋቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም።
ባለፈው ሳምንትም ታንዛኒያ ውስጥ በተካሄደው የአባይ ተፋሰስ አገራት የውሃ ሚንስትሮች ስብሰባ ላይ ሱዳንና ግብፅ እስካሁን ያልፈረሙትን የተፋሰሱ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በቶሎ እንዲያጸድቅ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ጥሪ ማድጋቸው ተዘግቧል።
ጄኔራል ሙሆዚ ከዚህ ቀደም ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ውስጥ ያሉትን የትግራይ ኃይሎች በመደገፍ በትዊተር ገጻቸው ላይ መልዕክታቸውን ማስቀመጣቸው ብዙዎችን አነጋግሮ ነበር።
ጄኔራሉ የኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት አንድ ዓመት በደፈነበት ጥቅምት 2014 ዓ.ም. ላይ የትግራይ ኃይሎችን ደግፈው ትዊት አድርገው ነበር።
“የትግራይ መከላከያ ኃይሎች . . . የቆማችሁበትን ዓላማ እደግፋለሁ። የትግራይ እህቶቻችንን የደፈሩ እና ወንድሞቻችንን የገደሉ መቀጣት አለባቸው” ሲሉ ጽፈው ነበር።
ይህን የጀነራል ሙሆዚ ትዊት ተከትሎ የኡጋንዳ መንግሥት አስተያየቱ የጄኔራሉ እንጂ የጦሩን አቋም አይወክልም የሚል ማስተባበያን ሰጥቶ ነበር።
የኡጋንዳ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ብሪክ ፌሊክስ ኩላይግዬ የጄኔራሉ ትዊት የኡጋንዳ ሕዝቦች መከላከያ ኃይሎችን አይወክልም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ቃል አቀባዩ አክለውም፣ አስተያየቱ የተሰጠው ከጄኔራሉ እንጂ ከአገሪቱ ጦር ስላልሆነ የአገሪቱን አቋም አያንጸባርቅም ብለዋል።
ምንም እንኳ የኡጋንዳ ጦር ይህ አመለካከት የጄኔራሉ እንጂ ጦሩ አይደለም ይበል እንጂ፣ ጄኔራሉ የትግራይ ኃይሎችን ደግፈው ያኖሩት ልጥፍ ለውጥ ሳይደረግበት አሁን ድረስ በገጻቸው እንዳለ ይገኛል።
ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ ለትግራይ ኃይሎች ድጋፋቸውን ሰጥተው ይጻፉ እንጂ በሌላ ወቅት ደግሞ ‘ከወንድሜ’ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ችግር የለብኝም ብለው ጽፈዋል።
“ከወንድሜ የተከበሩ ዐቢይ አሕመድ ጋር ችግር ኖሮኝ አያውቅም፤ እንደውም አከብራቸዋለሁ። የምንፈልገው በኢትዮጵያ ሰላም እንዲኖር ነው” በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፎቶግራፍ አያይዘው ትዊት አድርገው ነበር።
በኡጋንዳ ላይ ቀርቦ የነበረ ክስ
በቅርቡም አንድ ሪፖርትን ተክትሎ የኡጋንዳ ሠራዊት የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አባላትን በማሰልጠን ኢትዮጵያን ለማናጋት እየሰራ ነው የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር።
ነገር ግን የኡጋንዳ ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ፌሌክስ ኩላዬጊዬ ከጥቂት ሳምንት በፊት በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ፣ ኡጋንዳ የኢትዮጵያን ሰላም ለማናጋት ጥረት እያደረገች ነው የሚለው ክስ ፍጽም ፈጠራ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
ይህንን ክስ የተመለከተው ዝርዝር ጽሁፉ መቀመጫው ኒውዚላንድ በሆነ የበይነ መረብ ገጽ ላይ የወጣ ሲሆን፣ ጽሁፉ ህወሓትን በተመለከተ የሚካሄደውን ሥራ የሚያስተባብሩ ናቸው የተባሉ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና ሌሎች የደኅንነት ኃይሎች አባላትን ስም ዝርዝር ይዟል።
በዘገባው ላይ ስማቸው ከተጠቀሱት የኡጋንዳ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መካከልም የፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ እና የአገሪቱ የምድር ጦር ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ ይገኙበታል።
የወጣው ሰነድ ጨምሮ እንደሚያመለክተው ከ4,000 በላይ የህወሓት ተዋጊዎች ኡጋንዳ ውስጥ በሚገኙ በአራት የማሰልጠኛ ጣቢያዎች ውስጥ ለወታደራዊ ሥልጠና መግባታቸውን አመልክቶ ነበር።
የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ፌሌክስ ኩላዬጊዬ፣ በዚህ ጉዳይ ውስጥ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን በጋራ እየሰሩ ነው የሚለው ክስም ሐሰት ነው ብለዋል።
ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ
ጄኔራል ሙሆዚ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ወደ ጎረቤት አገራት በአባታቸው ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ይላካሉ።
ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ለሦስት ዓመታት ድንበራቸውን እንዲዘጉ ያስገደዳቸውን አለመግባባት ለመፍታት ወደ ኪጋሊ የተጓዘውን ልዑክ ጄኔራሉ መርተውት ነበር።
እንዲሁም ለኬንያው ተሰናባች ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ልዩ መልዕክት ለማድረስ በሙሴቪኒ ወደ ናይሮቢ ተልከው ነበር።
በኡጋንዳ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑት ጄኔራሉ አገሪቷን ወክለው ወደ ጎረቤት አገራት ለዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች መጓዛቸውን እና በፍጥነት የሚያገኟቸውን እድገቶች ከግምት በማስገባት፤ ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ልጃቸውን ለመንበረ ሥልጣን እያዘጋጁ መሆኑን ያሳያል የሚሉ በርካቶች ናቸው።
የ48 ዓመቱ ጀነራል የተወለዱት ከሙሴቬኒ እና ከእአአ 2016 ዓ.ም. የትምህርት ሚኒስትር ከሆኑት እናታቸው ጃኔት ሙሴቬኒ ነው።
እአአ 1974 በታንዛኒያ የተወለዱት ሙሆዚ፤ ፖለቲካ ሳይንስ የናይትድ ኪንግደም ውስጥ የተማሩ ሲሆን እአአ 1999 ላይ የአገሪቱን ጦር ተቀላቅለዋል።