ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ ከግጭቶች የተረፉ ሕጻናት ያሳለፉትን በሥዕል ይናገራሉ
ኢዮብ መርጊያ ይባላል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ግጭቶች ምክንያት ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያ ካምፖች ውስጥ ያሉ ሕጻናት “ቤታችን የት ነው?” በሚል ትውስታቸውን እንዲነግሩት ጠይቋል።
ለጥያቄው ምላሽ ሲጠይቅ ግን ቃላቸውን ከመቀበል ባሻገር በሥዕል መልሳቸውን እንዲያስቀምጡ አድርጓል።
ባለፉት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የእርስ በእርስ ጦርነት ጨምሮ፣ በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ዘግናኝ ድርጊቶች ተፈጽመዋል።
እነዚህን ኢ-ሰብአዊ ተግባራት የሚያሳዩ ምስሎች እና ቪዲዮዎችን መመልከትም እንግዳ መሆኑ አብቅቷል።
ኑሮውን በአሜሪካ ካደረገ 25 ዓመታትን ያስቆጠረው ኢዮብ እንደሚለው፣ በእነዚህ ግጭቶች ሰለባ የሆኑት ሕጻናት ጦርነቱን የሚመለከቱበት ዕይታ “ለልብ የሚናገሩ እና አሰቃቂ ምስሎችን ከመመልከት ይልቅ በርካቶች ሊመለከቷቸው የሚፈቅዱት” ነው።
“ቤታችን የት ነው?” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ ፕሮጀክት ከ900 በላይ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ያሉ ሕጻናት የሳሏቸው ሥዕሎችን የያዘ ነው።
በደብረ ብርሃን ከተማ ባሉ የመጠለያ ጣቢያዎች ካሉ ሕጻናት የተሰበሰቡት እነዚህ ምስሎች ኢዮብ ለሚያካሂዳቸው ሰፊ ጥናቶች ግብዓት ይሆናሉ።
ኢዮብ ይህንን ርዕስ ሲሰጠው ሕጻናቱን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሰው “ሰላም አግኝተን የምንኖርበት ቤታችን የት ነው?” ብሎ መጠየቅ ፈልጎ መሆኑን ያናገራል።
ለኢዮብ ምላሻቸውን በሥዕል ካሰፈሩ ሕጻናት መካከል አንዱ የሳለው የታጠቁ ሰዎች እናታቸውን ሲገድሉ፣ የሚመለከቱ ሕጻናትን ያሳያል።
እዚሁ ሥዕል ላይ ጥግ ላይ ቆሞ የሚመለከት ሰው ብሎም የቤት እንስሳ ሰፍሯል።
ቤታችን የት ነው? ለሚለው ጥያቄ በጨቅላ ብዕራቸው መልስ የሰጡት ሕጻናቱ “ቤት” የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ወድሞባቸዋል።
በዚህ ፕሮጀክት ከተሳተፉት ሕጻናት ውሰጥ 90 በመቶው ከወለጋ ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን የሚገኙ ናቸው።
ኢዮብ በተመሳሳይ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን የእርስ በእርስ ጦርነት የተመለከተ ተመሳሳይ ፕሮጀክት አዘጋጅቶ ነበር።
“እነዚህ ሕጻናት ቤታቸው ሲቃጠል፣ ወላጆቻቸው፣ ዘመዶቻቸው ወይም ጎረቤቶቻቸው ሲገደሉ፣ እንዲሁም ሲራቡ እና ከቀያቸው ሲፈናቀሉ የተመለከቱ ናቸው” ሲል ኢዮብ ይናገራል።
ሕጻናት ሃሳባቸውን በሥዕል እንዲገልጹ መደረጉ ስሜታቸውን ብሎም በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ደግሞ ስለቤታችው ያላቸውን የመጨረሻ ትዝታ እንዲገልጹ ያገዘ ነበር።
“የሕጻናቱ ሥዕል ቋንቋን፣ ፖለቲካን፣ ማኅበራዊ ብሎም ባሕላዊ ገደቦችን የሚያልፍ ነው። ይህ የሕጻናቱ ሥራ ወደ ራሳችን እንድንመለስ ዕድል ይሰጠናል ብዬ አስባለሁ” ሲልም ኢዮብ ይናገራል።
ሕጻናቱ በሳሏቸው ሥዕሎች መደነቁን የሚናገረው ኢዮብ ነገሮችን የማስታወስ ችሎታቸው ከፍተኛ ሆኖ ማግኘቱንም አስተውሏል።
ሕጻናቱ ቤታቸው ሲቃጠል፣ ሞተው መሬት ላይ የወደቁ ሰዎችን፣ የሚቃጠሉ ቤተ ዕምነቶችን ብሎም ቤተሰቦቻቸው ላይ መሳሪያ የደቀኑ ሰዎችን የሚያሳዩ ምስሎችን ስለዋል።
አንዳንዱ ሥዕል “ለቅጽበት ራሳችንን በልጆቹ ቦታ ሆነን እንድናስብ የሚያደርግ ነው” ሲልም ኢዮብ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ትውልድ እና እድገቱ በደብረ ብርሃን ከተማ የሆነው ኢዮብ በእነዚህ ካምፖች በነበረው ቆይታ ተፈናቃዮች የሚገኙበት ሁኔታ እጅግ እንዳሳዘነውም ይናገራል።
ይህንንም ለማገዝ እንዲያስችለው የተያዩ ድጋፎችን አድርጓል።
እርሱ በተመለከታቸው ካምፖች የነበሩ ከ45 ሺህ በላይ ሰዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ሕክምና ብሎም በአጠቃላይ መሠረታዊ አቅርቦቶች እንደሌላቸው ይናገራል።
ሕጻናቱ ትራኮማ ብሎም መሰል ሕመሞች እያሰቃያቸው መመለከቱንም ያክላል።
ይህንንም ተከተሎ ኢዮብ ከወዳጆቹ እና ከቤተሰቦቹ በተሰበሰበ መዋጮ የቻለውን ያህል ድጋፍ ማድረጉን ይናገራል።
ነገር ግን እስካሁን ያሉበት ሁኔታ ባለመሻሻሉ በርካታ ድጋፍ የሚፈልጉ ተፈናቀዮች ይደውሉለታል።
ሕጻናቱ “በተበላሸ የፖለቲካ ስሌት እና በሙስና ምክንያት እራሳቸው እና ቤተሰቦቻቸው የሚያልፉበትን ውጣ ውረድ በሥዕላቸው ቁልጭ አድርገው ለማሳየት ሞክረዋል” ይላል ኢዮብ።
ጨምሮም ለመፍትሔው “እኛ አዋቂዎች፣ ውሳኔ ሰጪዎች እና መሪዎች ይህንን አዙሪት ለመስበር ከሕጻናቱ መማር ይጠበቅብናል።”
የጦርነት ሥነ ጥበብ፣ ግለሰቦች በጦርነት ውስጥ በሚያልፉበት ወቅት የሚያሳልፉትን ውጣ ውረድ የሚገልጹበት መንገድ ነው።
በእርግጥ የሥነ ጥበብ ሰዎች ለጦርነት በተለየ መልኩ ምላሽ ይሰጣሉ።
በርካቶች የጦርነት ፕሮፓጋንዳን በጥበባቸው ሲነዙ በመላው ዓለም ታይተው አልፈዋል። ሌሎች ሰላምን ሲሰብኩ፣ አንዳንዶች ደግሞ ያዩትን የሰሙትን ከስሜታቸው ጋር አጋምደው ከትበዋል።
በዚህ ሁሉ የሰው እውቀት ገና ያልተበረዙት ሕጻናት ደግሞ የተመለከተቱን እና ድርጊቱ የፈጠረባቸውን ስሜት በቀጥታ በጥበብ ውስጥ ያስቀምጣሉ።
ኢዮብ እነዚህን የሰበሰባቸውን ሕጻናቱ የሠሯቸው ሥዕሎችን በላስ ቬጋስ እና ቀጥሎም በአዲስ አበባ ለሕዝብ ዕይታ ለማቅረብ እየተሰናዳ ይገኛል።
እንዲሁም ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለሂውማን ራይትስ ዋች እንዲሁም ለኢትዮጵያ መንግሥት በጳጉሜ ወር ውስጥ ይህንን ፕሮጀክቱን የሚመለከት ዘጋቢ ፊልምን ጨምሮ ግኝቶቹን እንደሚያቀርብም ኢዮብ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ይህ የሥነ ጥበብ ሥራው በተለይም ጦርነት በመጪው ትውልድ ውስጥ ጥሎት ስለሚያልፈው ጠባሳ ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ ለማድረግ ያቅዳል።
እንዲሁም ሰዎች ስለሰላም መነጋገር እንዲጀምሩ ማድረግ እና ብሎም የጥበብ ሰዎች ጦርነትን ከማስተጋባት ይልቅ ስለሰላም እንዲሰሩ ማድረግ ማስቻል አላማው እንደሆነ ያክላል።