ሕንድ እና ፓኪስታን ከኒውክሌር ጦርነት አፋፍ ላይ ደርሰው ነበር ተባለ

ከሦስት ዓመት በፊት ሕንድ እና ፓኪስታን ከኒውክሌር ጦርነት አፋፍ ላይ ደርሰው እንደነበር የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ማይክ ፖምፒዮ ተናገሩ።

ፖምፒዮ ባሳተሙት የግል ማስታወሻቸው ላይ እንዳሉት እንደ አውሮፓውያኑ 2019 የካቲት ወር በወታደሮቿ ላይ ካሽሚር ውስጥ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በፓኪስታን ላይ በወሰደችው እርምጃ ምክንያት የኒውክሊየር ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደነበር አመልክተዋል።

በወቅቱ ፓኪስታን ሁለት የሕንድ ተዋጊ አውሮፕላኖችን መትታ በመጣል አንድ ፓይለት መማረኳን አስታውቃ ነበር።

ሕንድ እና ፓኪስታን አወዛጋቢዋ የካሽሚር ግዛትን ሙሉው የራሳቸው እንደሆነ የሚገልጹ ሲሆን፣ ነገር ግን አካባቢውን የሚቆጣጠሩት በከፊል ነው።

ሕንድ በካሽሚር ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ ተንጣይ ታጣቂዎችን ፓኪስታን ትረዳለች በማለት ስትከስ የቆየች ሲሆን ፓኪስታን ግን አትቀበለውም።

የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የታጠቁት ሁለቱ ጎረቤታሞች በ1947 (እአአ) ከብሪታኒያ ነጻ ከወጡ እና ሁለት አገር ከሆኑ በኋላ ሦስት ጦርነቶች ተዋግተዋል። ከአንዱ በስተቀር የሁለቱ ጦርነቶች ምክንያት በካሽሚር ግዛት ምክንያት ነው።

የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ፖምፒዮ በመጽሐፋቸው ላይ “በሕንድ እና በፓኪስታን የነበረው ጠላትነት በ2019 ወደ ኒውክሌር ጦርነት ሊሸጋገር እንደነበር ዓለም በትክክል አያውቅም” ብለዋል።

“ነገር ግን በትክክል ምን ሊሰከሰት እንደነበር አላውቅም፣ እውነታው ግን ወደ ኒውክሌር ጦርነት አፋፍ ላይ ደርሰው ነበር” ብለው ጽፈዋል።

ፖምፒዮ ቬትናም ሃኖይ ውስጥ “ከሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናት ጋር ስለኒውክሌር ጦር መሳሪያ እየተደራደርን በነበርንበት ጊዜ፤ ሕንድ እና ፓኪስታን አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ኒውክሊየር መሳሪያን እንደሚጠቀሙ” ሲዝቱ የነበረበትን ምሽት እንደማይረሱት ገልጸዋል።

“በእስላማዊ የሽብር ጥቃት. . . ምናልባትም በከፊል በፓኪስታን የላላ ፀረ ሽብር ፖሊሲ” የተከሰተ ነው ባሉት ጥቃት ምክንያት ከአርባ በላይ የሕንድ ወታደሮች ከተገደሉ በኋላ ሕንድ ከባድ እርምጃ ወስዳለች።

ሕንድ ወደ ፓኪስታን ግዛት ዘልቃ በመግባት የአየር ጥቃቶችን ስትፈጽም “ይህንንም ተከትሎ በጦር አውሮፕላኖች መካከል በተደረገ ውጊያ ፓኪስታን የህንድ አውሮፕላን መትታ በመጣል አንድ ፓይለት ማርካለች” ብለዋል ፖምፒዮ።

ፖምፒዮ ቬትናም እንዳሉ ስማቸው ካልተገለጸ የሕንድ “አቻቸው” ጥሪ እንደደረሳቸው እና “ባለሥልጣኑ ፓኪስታን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመጠቀም እየተዘጋጀች እንደሆነ እንደሚያምኑ፣ ሕንድም አጸፋውን እያሰበች መሆኑን ነገሩኝ” ብለው ጽፈዋል ፖምፒዮ።

“እኔም ምንም እንዳያደርጉ ጠይቄ፣ መፍትሔ ለመፈለግ ጊዜ እንዲሰጡኝ ጠየቅኩ።”

ከዚያም ፖምፒዮ አብረዋቸው ከነበሩት የወቅቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ጆን ቦልተን ጋር ካሉበት ሆቴል ውስጥ ሥራቸውን መጀመራቸውን ጽፈዋል።

ከፓኪስታን የጦር ሠራዊት አዛዥ ጄኔራል ቃማር ጃቪድ ባጅዋ ጋር በመገነኛትም “ሕንዶች ያሉኝን ነገር ነገርኩት” ጄኔራሉም የተባለው ሐሰት መሆኑን እና በተቃራኒው ሕንዶች የኒውክሌር ጦር መሳሪያቸውን እያዘጋጁ መሆኑን እንደተናገሩ ጽፈዋል።

ከዚያ በኋላም በዴልሂ እና ኢስላማባድ ያሉ ሠራተኞቻቸው ለሰዓታት ባደረጉት ጥረት ከሁለቱም አገራት ባለሥልጣናት ጋር በመገናኘት ሌላኛው አገር ኒውክሌር ለመጠቀም እየተዘጋጀ አለመሆኑን ለማሳመን መቻላቸውን አስፍረዋል።

“በዚያን ምሽት ከባድ ጉዳት የሚያስከትለውን ቀውስ ለማስወገድ አሜሪካ የሰራችውን ያህል ማንም ሊሰራ አይችልም ነበር” ብለዋል ፖምፒዮ።

ነገር ግን ፖምፒዮ ሊፈጠር ነበር ስላሉት የኒውክሌር ጦርነት ከሕንድም ሆነ ከፓኪስታን አስካሁን የተባለ ነገር የለም።

በዚያ ወቅት በሕንድ ወታደሮች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት መሠረቱን ፓኪስታን ያደረገው ጃይሽ-ኢ-ሞሐመድ የተባለው ቡድን ኃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን፣ ሕንድም እንደምትበቀል አሳውቃ ነበር።

ሕንድ ድንበር ተሻግራ ፓኪስታን ውስጥ በፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች በርካታ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎችን መግለደሏን የገለጸች ሲሆን፣ ፓኪስታን ግን እርምጃውን “ኃላፊነት የጎደለው” ብላዋለች።