ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት በኋላ የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ደቡብ አፍሪካ ገቡ
የሩሲያውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጉብኝትን ተከትለው የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ጃኔት ዬለን ደቡብ አፍሪካ ገቡ።
በአፍሪካ ለአስር ቀናት በሦስት አገራት ውስጥ ያደረጉትን ቆይታ በደቡብ አፍሪካ የሚያሳርጉት የኃያሏ አገር የግምጃ ቤት ኃላፊ ከፕሬዝዳንቱ እና ከሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይነጋገራሉ ተብሏል።
ከሌሎች አገራት የገንዘብ ሚኒስትር ሥልጣን ጋር አቻ የሆነው የግምጃ ቤት ኃላፊዋ ጃኔት ዬለን አሜሪካ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት ለመጠናከር ነው ባለፈው ሳምንት ጉብኝት የጀመሩት።
ጃኔት ዬለን በጉብኝታቸው ወደ ሴኔጋል እና ዛምቢያ በቀዳሚነት ያቀኑ ሲሆን አሁን ደቡብ አፍሪካ ይገኛሉ። የባለሥልጣኗ ጉብኝት የተካሄደው ኃላያኑ ሩሲያ እና ቻይና በአፍሪካ ውስጥ ከአሜሪካ አንጻር እያደረጉት ያለው ፉክክር የተጠናከረ ባለበት ጊዜ ነው።
ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ውስጥ የግዙፍ ምጣኔ ሃብት ባለቤት ስትሆን ከፍተኛ ተሰሚነትም አላት። በተጨማሪም የምዕራባውያኑ ተገዳዳሪ እየሆነ የመጣው ያደጉ አገራት ስብብስብ የሆነው ብሪክስ በመባል የሚታወቀው የአገራት ማኅበር ሊቀመንበር ናት።
ብሪክስ የሚባለው ስብስብ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድ እና ደቡብ አፍሪካን የያዘ ሲሆን፣ የምዕራባውያኑን ዓለም አቀፍ የበላይነትን ለመገዳደር የተቋቋመ ነው።
አሜሪካዊቷ ባለሥልጣን በደቡብ አፍሪካ በሚኖራቸው ቆይታ ከአገሪቲ ፕሬዝዳንት ጋር የሚገናኙ ሲሆን፣ ሲሪል ራማፎሳ አገራቸው በድንጋይ ከሰል ላይ ካላት ጥገኝነት ቀስ በቀስ በመላቀቅ በካይ ወዳልሆነ የኃይል ምንጭ እንድትሻጋገር ግፊት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከጃኔት ዬለን በተጨማሪ ደቡብ አፍሪካ በዚህ ሳምንት የሩሲያውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭን አስተናግዳለች። ላቭሮቭ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መገናኘታቸውም ተዘግቧል።
ደቡብ አፍሪካ ከሩሲያ እና ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት እያጠናከረች ሲሆን፣ በቀጣይ የካቲት ወር ደግሞ ከሁለቱ አገራት ጋር በባሕር ዳርቻዋ ላይ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እንደምታደርግ አስታውቃለች።
በተለይ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ድርጊቱን በማውገዝ ከጎናቸው እንድትቆም ምዕራባውያን ደቡብ አፍሪካን ቢያግባቡም ሳይሳካላቸው በገለልተኛነት ለመጽናት ወስናለች።
በዚህም ሳቢያ ሩሲያ የምትሳተፍበት የጦር ልምምድ ትችት እንዲሰነዘርባት ቢያደርግም የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን ደቡብ አፍሪካ ከማን ጋር ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ እንዳለባት ሌሎች ሊመርጡላት አይገባም ሲሉ ተቃውመዋል።
የሩሲያ እጅግ ዘመናዊ የሆነ የጦር መርከብ ይሳተፍበታል በተባለው የጦር ልምምድን በተመለከተ፣ የደቡብ አፍሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ከቻይና እና ከሩሲያ ጋር የሚደረገው ወታደራዊ ልምምድ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ከፈረንሳይ፣ ከአሜሪካ እና ከሌሎች የኔቶ አገራት ጋር ካደረግነው የተለየ አይደለም ብሏል።