በወልቂጤ ከተማ ሰልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ በተከፈተ ተኩስ ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናገሩ

ለሰልፍ የወጡ ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, welkite fm

በደቡብ ክልል፣ ጉራጌ ዞን፣ ወልቂጤ ከተማ ለወራት ላጋጠመ የውሃ ችግር ምላሽ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ሰልፍ በወጡ ሰዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ የሰዎች ሕይወት ማለፉን እና የአካል ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በከተማዋ ያጋጠመው የውሃ ችግር ለረጅም ጊዜም በመቆየቱ ነዋሪዎች ብሶታቸውን ለማሰማት ዛሬ ረቡዕ የካቲት 08/2015 ዓ.ም. ጠዋት ወደ ከተማዋ የውሃ ልማት አስተዳደር ቢሮ ባቀኑበትም ወቅት ነው የፀጥታ ኃይሎች ተኩስ እርምጃ የወሰዱት።

በዚህም እስከ ሦስት የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸውን ቢቢሲ ያናገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸው፣ ሌሎች አምስት ወጣቶችም ጉዳት ደርሶባቸው በአስጊ ሁኔታ ላይ ናቸው ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ‘ውሃ ይሰጠን’ በሚል በወልቂጤ ከተማ የውሃ ልማት አስተዳደር ቢሮ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን እያሰሙ እንደነበር ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እና በሰልፉ ላይ የነበሩ ነዋሪ ገልጸዋል።

ሰልፉ ሰላማዊ እንደነበር የጠቀሱት ግለሰቧ መሃል ላይ ባላወቁት ምክንያት “በፀጥታ ኃይሎች ተኩስ ተከፈተብን” ብለዋል።

“ተኩሱ ለምን እንደተጀመረ ይሄ ነው ማለት አልችልም” በርካቶች ለተባባሰው የውሃ ችግር እልባት ይሰጠን በሚል ባዶ ጀሪካን ብቻ ይዘው በሰላም እየጠየቁ ነበር ብለዋል።

ተኩሱ ሲጀመር ነዋሪው ቢሸሽም የተጎዱ እና የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን ነዋሪዋ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በፀጥታ ኃይሎች ጥይት ተመትተው ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በከተማዋ ወደ ሚገኘው የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል መወሰዳቸው የተነገረ ሲሆን ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ በክሊኒኮች መታከማቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በወልቂጤ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ሐኪም የሆኑት ዶክተር በኃይሉ ደጉ፣ ደረታቸውን እና ጭንቅላታቸውን በጥይት ተመተው የሞቱ የሁለት ሰዎች አስከሬን ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

እንዲሁም አምስት ሰዎች ክፉኛ ቆስለው በአስጊ ሁኔታ ወደ ሆስፒታሉ እንደመጡ እና ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ ከባድ ነገር ግን አስጊ ባይሆንም ተጎድተው ወደ ሆስፒታሉ መግባታቸውን ዶክተር በኃይሉ ገልጸዋል።

አንድ የከተዋው ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ሰው ላይ ነው የተተኮሰው። ያየናቸው አሉ በጥይት የተመቱ” ባላቸው መረጃም ሦስት ሰዎች እንደሞቱ፣ ነገር ግን ምን ያህል እንደቆሰሉ እንደማያውቁም አስረድተዋል።

ሆኖም እሳቸው እንደሚሉት በጥይት ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የፀጥታ ኃይሎች ለሰልፍ በወጡት ሰዎች ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል።

ወደ ሥራ እያመሩ በነበሩበት ወቅት ሰልፉን እንደተቀላቀሉ የሚናገሩት እኚህ ነዋሪ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ውሃ ካገኙ ወራት እንደሆናቸውና የውሃ ችግሩ ከተከሰተም አንድ ዓመት እንደተጠጋው ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ውሃ እየገዙ እንደሚጠቀሙ እና በጀሪካንም እስከ ሃያ ብር እንደሚጠየቁ የሚናገሩት ነዋሪዋ፣ መንግሥት ለዚህ ችግር ምላሽ ሊሰጣቸው እንዳልቻለም ወቀሳቸውን አቅርበዋል።

“ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እስከ ዛሬ ረጅም ጊዜ ቆይተናል። ዛሬም የወጣነው በሰላም መልስ እናገኛለን ብለን ነበር። ሁኔታው ወደ ጥይትና ደም ማፍሰስ ነው የተቀየረው” ብለዋል።

ውሃ ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ ወራትን እንዳስቆጠረ የሚናገሩት ሌላኛው ነዋሪ፣ ከዚያ በፊት በነበረውም ወቅት በአስራ አምስት ቀን አንድ ጊዜ ወይም በወር አንድ ጊዜ ቢመጣም፣ ውሃው ንጹህ እንዳልነበረ እና ችግሩም ስር የሰደደም ነው ብለዋል።

እኚህ ነዋሪ ውሃ ለመቅዳት በጥዋት ወጥተው ወረፋ ሲጠብቁ የነበሩ እና የውሃ መታጣት ያማረራቸው እናቶች ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ ዛሬ ጠዋት ወደ አስተዳዳሪው ቢሮ ማቅናታቸውን ተናግረዋል።

በዚህ ወቅትም በስፍራው አድማ በታኞች አስለቃሽ ጭስ በሰልፈኞቹ ላይ ሲተኩሱ ወጣቱ ደንግጦ በሚወጣበት ወቅት ተኩስ እንደተከፈተ እና የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን በበኩላቸው አስረድተዋል።

በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ አምስት ሰዎች እንዳሉ እንዲሁም በርካቶችም የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ነዋሪው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ሰልፉ የተለየ አጀንዳ አልነበረውም” የሚሉት ግለሰቡ ለውሃ ችግር ምላሽ እንዲገኝ ለመጠየቅ እንደነበር ያስረዳሉ።

ከጉራጌ ክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ሰልፎች እና የሥራ ማቆም አድማ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተደረገ ቢሆንም፣ አሁን የተከሰተው ግን ቀደም ካሉት ሁኔታዎች ጋር በፍጹም አይገናኝም ሲሉ ሁለቱ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ሕዝቡ ውሃ እና ውሃ ብቻ ነው የጠየቀው፤ እናቶች የውሃ ችግሩ ሲመራቸው እንጠይቅ ብለው ወጡ ከሰሞኑ የታሰበ፣ የተጠራም ሰልፍ የለም” ብለዋል።

“በአካባቢው የነበረው ልዩ ኃይልም ሆነ የከተማው አስተዳደር ይሄንን ጉዳይ ሰላማዊ ማድረግ ይችሉ ነበር። ሕዝቡ እንዳይጎዳ፣ የተጠየቀውን ነገር በአግባቡ መመለስ እና ማወያየት ይቻል ነበር” ሲሉም ተናግረዋል።

ቢቢሲ በወልቂጤ ከተማ ስለተከሰተው ሁኔታ እና በሰው ላይ ስለደረሰው ጉዳት ከደቡብ ክልል እና ከጉራጌ ዞን አስተዳደር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ትናንት የካቲት 07/2015 ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ጉባኤ በከተማዋ ያለው አንገብጋቢ የውሃ ችግር መፍትሄ መሰጠት እንዳለበት መወያየቱን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

አስተዳደሩ የውሃ ችግሩን ለመቅረፍ ቅድሚያ በመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልጾ፣ነገር ግን ሥራዎቹ በሚፈለገው ፍጥነት ውጤት አላመጡም ብሏል።

ሆኖም ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት ያሉ አማራጮችን ሁሉ ተጠቅሞ ለማቃለል ይሰራል በማለት ከንቲባ አቶ አበበ አሰፋ መናገራቸው ሰፍሯል።