አልጄሪያ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ወንጀል ነው የሚል ሕግ አወጣች

የአልጄሪያ ፓርላማ የፈረንሳይ ቅኝት ግዛት ወንጀል ነው የሚል ሕግ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።

ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር በፈረንሳይ ቅኝ መገዛቷ ወንጀል ነው ያለው ፓርላማው ኦፊሴላዊ ይቅርታ እና ካሳ እንደሚገባ በይኗል።

የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው ሕጉ ቅኝ ግዛት ማንቆለጳጰስም ወንጀል ነው ይላል።

አዲሱ ሕግ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ መምጣቱን የሚያሳይ ሲሆን ተንታኞች አልጄሪያ ከ63 ዓመታት በፊት ነፃነቷን ካገኘች በኋላ መሰል መካረር ታይቶ አይታወቅም ይላሉ።

ፈረንሳይ ከአውሮፓውያኑ 1830 እስከ 1962 ነው አልጄሪያን ቅኝ የገዛችው። በቅኝ ግዛቱ ወቅት ጅምላ ግድያዎች እና ከፍተኛ መፈናቀሎች ተፈፅመዋል። ለነፃነት የተደረገው ጦርነትም ከባድ የደም መፋሰስ አስከትሏል።

አልጄሪያ በወቅቱ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል ስትል የፈረንሳይ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ቁጥሩን ዝቅ ያደርጉታል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ከዚህ ቀደም የአልጄሪያ ቅኝ ግዛት "በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው" ቢሉም ይቅርታ አልጠየቁም።

የአልጄሪያ ባንዲራ ያለበት ማቀለሚያ ያደረጉ የፓርላማ አባላት "ረዥም ዕድሜ ለአልጄሪያ" የሚል ሕብረ ዝማሬ በማሰማት በደማቅ ጭብጨባ ሕጉን ማፅደቃቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ሕጉ፤ ፈረንሳይ "ላደረሰችው ጥፋት ሙሉ እና ፍትሐዊ" ካሳ የመክፈል "ሕጋዊ ኃላፊነት" አለባት ብሎ ይህ ደግሞ "የአልጄሪያ መንግሥት እና ሕዝብ የማይገፈፍ መብት ነው" መሆኑን ያሰምራል።

ፈረንሳይ እስካሁን በሕጉ ላይ አስተያየት አልሰጠችም።

ምዕራባዊያን አገራት በባርያ ንግድ እና ቅኝ ግዛት ወቅት ላደረሱት ጥፋት ካሳ መክፈል አለባቸው አልፎም የዘረፏቸውንና በሙዚየም ያስቀመጧቸውን ቅርሳቅርስ ሊመልሱ ይገባል የሚል ጫና እያደረደባቸው ይገኛል።

የአልረጄሪያ ሕግ አውጭዎች ፈረንሳይ ባባ ሜርዙግ አሊያም "የተባረከ አባት" የተሰኘ ስም ያለውን የ16ኛው ክፍለ ዘመን የብር መድፍ እንድትመልስ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ይህ መድፍ አሁን የአልጄሪያ ዋና ከተማ የሆነችው አልጄርስ ጠባቂ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።

ፈረንሳይ በአውሮፓውያኑ 1830 ነው ከተማዋን በሶስተኛ ሙከራ በቁጥጥር ሥር በማዋል መድፉን ያስወገደችው። መድፉ በአሁኑ ወቅት በሰሜን ዕምራብ ፈረንሳይዋ ብረስት ከተማ ይገኛል።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ኃይሎችን ሲዋደቁ የወደቁ 24 አልጄሪያዊያን ቅሪት በ2020 መመለሱ ይታወሳል።

ባለፈው ወር አልጄሪያ ፍትሕ እና ካሳ ሊመጣ ይገባል የሚሉ የአፍሪካ ሀገራት ኮንፈረንስ አዘጋጅታለች።

የአልጄሪያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ ካሳ "ስጦታ ነው ወይስ ውለታ" የሚለውን ሕጋዊ ማዕቀፍ ይወስነዋል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ማክሮን ፈረንሳይ ምዕራባዊ ሰሀራ የሞሮኮ ግዛት ስለመሆኗ እውቅና ትሰጣለች ማለታቸውን ተከትሎ ነው በአልጀርስና ፓሪስ መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ የሻከረው።

ምዕራባዊ ሰሀራ ከሞሮኮ፣ አልጄሪያ እና ሞሪታኒያ ጋር የሚዋሰን አሁንም በርካታ ውዝግብ ያለበት ስፍራ ነው።