ለእርዳታ በጠራችው ፖሊስ በጥይት የተገደለችው ጥቁር አሜሪካዊት ቪዲዮ ይፋ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, CBS
በአሜሪካዋ ኢሊኖይስ ግዛት ለእርዳታ በጠራችው ፖሊስ በጥይት የተገደለችው ጥቁር አሜሪካዊት ቪዲዮ ይፋ ሆነ።
ቤቴን ሰብሮ የገባ ሰው ሳይኖር አይቀርም በሚል በድንገተኛ ጥሪ 911 በመደወሏ ነበር ፖሊሶች ቤቷ የተገኙት።
መኖሪያ ቤቷ ከደረሱት የፖሊስ መኮንኖች አንደኛው የ36 ዓመቷ ሶኒያ ማሴን በመግደል ወንጀል ክስ የተመሰረተበት ሲሆን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አውግዘውታል።
የሳንጋሞን ግዛት ምክትል ኃላፊ የሆነው ሾን ግሬሰን ከስራው የተባረረ ሲሆን በግድያ ወንጀል እና በስነ ምግባር ጉድለት ክስ ቀርቦበታል።
ግለሰቡ በቀረቡበት ክሶች ላይ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል።
ፖሊሶች ቤቷ ከገቡ በኋላ ሽጉጣቸውን በሷ ላይ ደግነው ሶኒያን እያፈላችው የነበረውን ውሃ እንድታስቀምጥ ሲጮሁ የሚያሳይ በሰውነታቸው ላይ የተገጠመው ካሜራ የቀረጸው ቪዲዮ ያሳያል።
ግለሰቧ ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር ስፕሪንግፊልድ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ አንድ ግለሰብ ሰብሮ ሳይገባ አይቀርም በሚል ነበር ለፖሊስ የደወለችው።
ግለሰቧ ወደ ቤቷ ስትገባ እነዚህ ፖሊሶች አብረው የገቡ ሲሆን መታወቂያዋን እንድታሳይ ጠይቀዋት እሱንም ስትፈልግ እየተመለከቱዋት ነበር።
ቪዲዮው እንደሚያሳየው አንድ ድስት በምድጃ ላይ ተጥዶ ያየው ፖሊስ ወደ እሱ በምልክት “እዚህ እሳት አያስፈልግም” በማለት እንድታጠፋው ሲጠይቃት ይደመጣል።
እሷም ድስቱን ለማውረድ ወደ ምድጃው ስትሄድ ትታያለች። ከፖሊሱም ጋር “የሚፈላ ውሃ እያሉ እየተሳሳቁ የሚሰሙ ሲሆን “እሷም እንደ ጸበል በማስመሰል በቀልድ መልክ “በእየሱስ ስም እገስጽሃለሁ” ስትል ይሰማል።
ከዚያም ፖሊሱ “በአምላክ ስም እምላለሁ። ፊትሽ ላይ ነው የምተኩስብሽ “ እያለ የሚጮህባት ሲሆን ድስቱን እንድታስቀምጥ እየጮኸም ተኮሰባት።
እሷም “ይቅርታ” በማለት ስትጎነበስ ትታያለች።
ነገር ግን ግለሰቡ ድጋሚ ከተኮሰባት በኋላ ህይወቷ አልፏል።
ሰኞ እለት የሳንጋሞን ግዛት አቃቤ ህግ ፖሊሱ በሶኒያ ላይ የወሰደው የኃይል እርምጃ ምንም ምክንያታዊ አይደለም ብሏል።
ፕሬዚዳንት ባይደን አሟሟቷን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ለቤተሰቧ “ልቤ ተሰብሯል” ብለዋል።
“ሶንያ ማሴይ ተወዳጅ እናት፣ ጓደኛ፣ ልጅ እና ወጣት ጥቁር ሴት ዛሬ በህይወት ልትኖር ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም “ ሶንያ ለእርዳታ በጠራችው ፖሊስ እጅ መሞቷ በርካታ ጥቁር አሜሪካውያን ለደህንነታቸው ሁልጊዜም እንደሚፈሩ እና እኛ የሌለብን ስጋት ያሳየ ነው” ሲሉም ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት
የሶንያ ጠበቆች በበኩላቸው አቃብያነ ህግ በፖሊሱ ላይ ለወሰዱት ፈጣን እርምጃ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ጠበቃው ቤንጃሚን ክሩምፕ እንደተናገሩት ቪዲዮው “ የመላው አሜሪካውያንን ህሊና የሚያስደነግጥ ነው” ብለዋል።
አክለውም “ይህ ትርጉም የለሽ፣ አላስፈላጊ፣ ፍትሃዊ ያልሆነ እና ኢ-ህገ መንግሥታዊ ነው” ሲሉም አውግዘዋል።












