በታላቁ ቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ወድድር የሚሰጠው ማሊያ ትርጉሙ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰኔ 22 አስከ ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም. ለሦስት ሳምንታት ያህል በ21 ደረጃዎች ሲካሄድ የቆየው በዓለም ዋነኛ የሆነው ቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ውድድር በታሪኩ ትልቅ የሚባል አዲስ ምዕራፍ ተመዝግቦበታል።
በውድድሩ የ120 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ለ111ኛ ጊዜ የተካሄደው የዘንድዎው ቱ ቱር ደ ፍራንስ ላይ ኤርትራዊው የኢንተርማርች ክለብ ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛ ቢንያም የአረንጓዴ ማሊያ አሸናፊ በመሆን የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆኗል።
ቢኒያም በዚህ ዓመት በተደረገው የቱር ደ ፍራንስ ውድድር ታሪክ ሦስት ደረጃዎችን በማሸነፍ ነው የመጀመሪያው አፍሪካዊ ለመሆን የበቃው።
ሌላው አዲስ ክብረ ወሰን የተመዘገበው በካዛኪስታናዊው ማርክ ካቫናግ ነው። ብስክሌተኛው በዘንድሮው የቱር ደ ፍራንስ ላይ ያገኘውን ብቸኛ ድል ተከትሎ 35 ጊዜ የውድድሩን ድል የተጎናጸፈ ብቸኛ ተወዳዳሪ ለመሆን በቅቷል።
ቀደም ብሎ በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ እና 1970ዎቹ የተወዳደረው ቤልጄየማዊው ማርከስ ኤዲ በቱር ደ ፍራንስ 34 የውድድሩን ድሎች አስመዝግቦ ነበር።
በ2024ቱ ቱር ደ ፍራንስ በቢጫ ማሊያ አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀው የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ስሎቬኒያዊ ታደይ ፖጋቻ ሲሆን፤ ዴንማርካዊ ጆናስ ቪንጋርድ እና ቤልጄየማዊው ሬምኮ ኢቭንፖኤል ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።
በአረንጓዴው ማሊያ ኤርትራዊው ቢኒያም ግርማይ በ387 ነጥብ አንደኛ፣ ቤልጄየማዊው ጃስፐር ፊሊፕሰን በ354 ነጥብ ሁለተኛ እና ፈረንሳዊው ብሪያን ኮካርድ በ208 ነጥብ ሦስተኛ ሆነዋል።
በዳገት ላይ ለሚደረገው ውድድር አሸናፊ የሚሰጠው ባለ ቀይ ነጠብጣብ ማልያን ደግሞ ኢኳዶርያዊው ሪቻርድ ካራፓዝ በ127 ነጥብ አንደኛ እንዲሁም ታደይ ፖጋቻ እና ዮናስ ቪንጌጋርድን ተከታትለው ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።
በነጩ ማሊያ ቤልጄየማዊው ሬምኮ ኢቨንፖኤል አንደኛ፣ ካርሎስ ሮድሪገዝ ሁለተኛ እና ማቲው ዮርገንሰን ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
አሸናፊዎች የሚሸለሙት ማልያ ትርጉሙ ምንድን ነው?
የቱር ደ ፍራንስ ውድድር በ1903 የተጀመረ ሲሆን፣ በአንደኛው እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ለአስር ዓመታት ከመቋረጡ በስተቀር ዘንድሮ ለ111ኛ ጊዜ ነው የተካሄደው።
የዘንድሮው የቱር ደ ፍራንስ ተወዳዳሪዎች በ21 ቀናት ውስጥ በአጠቃላይ ወደ 3,500 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ርቀት ተጉዘዋል።
ይህንን 3,500 ኪሎ ሜትር ርቀትን በአጭር ጊዜ ላጠናቀቀው ተወዳዳሪ ቢጫ ማሊያ ይሰጣል።
ዘንድሮ በቢጫ ማሊያ አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ታደይ ፖጋቻ 3,500 ኪ.ሜ ርቀቱን በ83 ሰዓት ከ38 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ አጠናቋል።
በቢጫ ማሊያ 2ኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ዮናስ ቪንጌጋርድ 6 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ዘግይቶ ሆኖ አጠናቋል።
ኤርትራዊው ቢኒያም ግርማይ ዘንድሮ ያሸነፈው አረንጓዴ ማሊያ በፈጣን በውድድሮች መካከል ነጥብ የሚያሰጠውን መስመር በማለፍ ከፍተኛ ነጥብ ለሰበሰበ የሚሰጥ ማልያ ነው።
በዚህ መስፈርት ቢኒያም ግርማይ ሦስት ጊዜ አንደኛ፣ ሁለት ጊዜ ሁለተኛ፣ አንድ ጊዜ አራተኛ እንዲሁም አንድ ጊዜ ዘጠነኛ ሆኖ በማጠናቀቅ በውድድር መካከል ደግሞ ነጥብ የሚያሰጠውን 148 ነጥብ በመሰብሰብ በድምሩ 387 ነጥብ በመያዝ የአረንጓዴ ማሊያ ተሸላሚ ሊሆን ችሏል።
ቢንያምን ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው የ2023 አረንጓዴ ማሊያ አሸናፊ የነበረው ቤልጄየማዊው ጃስፐር ፍሊፕሰን ከቢንያም በ33 ነጥብ ዝቅ ብሎ በ354 ነጥብ ውድድሩን አጠናቋል።
ባለ ቀይ ነጠብጣብ ማልያ ዳገት በመውጣት የበለጠ ነጥብ ለሰበሰበ የሚሰጥ ሲሆን፣ በ21 መድረኮች በተዘረጉ የዳገት ላይ ውድድሮች ከፍተኛ ነጥብ የሰበሰበ ተወዳዳሪ ይህ “ኪነግ ኦፍ ማውንቴን” በሚል የሚጠራ ማልያ ይሰጠዋል።
በዚህ መስፈርት ኢኳዶራዊው ሪቻርድ ካራፓዝ በ127 ነጥብ አንደኛ፣ ታደይ ፖጋቻ በ102 ነጥብ ሁለተኛ እና ዮናስ ቪንጋርድ በ70 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
በውድድሩ ነጭ ማሊያ ለወጣት ተወዳዳሪ የሚሰጥ ነው። ከዚህ ቀደም ውድድሩን ያላሸነፉ እና ከ26 ዓመት በታች ለሆኑ ተወዳዳሪዎች ይሰጣል።
በዚህም 3,500 ኪሎ ሜትር ርቀቱን በ21 ቀናት ውስጥ 3500 ኪሎሜተር በአነስተኛ ጊዜ ላጠናቀቀ ተወዳዳሪ ይሰጠዋል።
በቢጫ ማሊያ ሦስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው እና የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ቤልጄየማዊው ሬምኮ ኤቨንፓል በ83 ሰዓት ከ48 ደቂቃ እና 15 ሰከንድ በማጠናቀቅ የነጩን ማሊያ አሸናፊ ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቱር ደ ፍራንስ አሸናፊ ሽልማት ምን ያህል ነው?
የዘንድሮው ቱር ደ ፍራንስ ቢጫ ማልያ በ2020 እና 2021 ያሸነፈው ስሎቬኒዊያ ታደይ ፖጋቻ ነው።
ፖጋቻ በዓመቱ በአምስት ደረጃዎች አንደኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ከሁሉም ተወዳዳሪዎች መላቅ ችሏል።
ቢንያም አረንጓዴውን ማሊያ ሲያሸንፍ ኢኳዶርያዊው ሪቻርድ ካራፓዝ የዳገት አንበሳ ማሊያ ተቀብሏል።
ቤልጄማዊው ሬምኮ ኤቨንፖኤል ደግሞ ለወጣቶች የሚሰጠውን ነጭ ማሊያ ተሸልሟል።
የብስክሌት ውድድር እግር ኳስን ከመሳሳሉ የስፖርት ውድድሮች ጋር ሲነጻጸር በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም የሚሰጠው ሽልማት ግን አነስተኛ ነው።
በዚህ ውድድር ለሽልማት የተዘጋጀው አጠቃላይ ገንዘብ 2.3 ሚሊዮን ዩሮ ነው። ከዚህ ውስጥ 20 በመቶው ወይም ግማሽ ሚሊዮን ዩሮ ለቢጫ ማሊያ አሸናፊ ይሰጣል።
በቢጫ ማሊያ ለአንደኛ ግማሽ ሚልዮን ዩሮ፣ ለሁለተኛ 200,000 ዩሮ፣ ለሦስተኛ 100,000 ዩሮ፣ ለአራተኛ 70,000 ዩሮ፣ ለአምስተኛ 50,000 ዩሮ፣ ለስድስተኛ 23,000 ዩሮ፣ ለሰባተኛ 11,500 ዩሮ፣ ለስምንተኛ 7600፣ ለዘጠነኛ 4,500 እና ለአስረኛ 3,800 ዩሮ እያለ 20ኛ ላጠናቀቀው 1,000 ዩሮ ይሰጣል።
ሁሉም እነዚህን 21 መድረኮች ያጠናቀቁ ተወዳዳሪዎች እያንዳንዳቸው 1,000 ዩሮ ሽልማት አላቸው።
የዙር አሸናፊዎች ደግሞ ለአንደኛ 11,000 ዩሮ፣ ለሁለተኛ ደረጃ 5,500 ዩሮ፣ ለሦስተኛ 2,800 ዩሮ፣ ለአራተኛ 1,500 ዩሮ እና ለአምስተኛ ደረጃ 830 ዩሮ እያለ እስከ 20ኛ ላጠናቀቁ ለእያንዳንዳቸው 300 ዩሮ ይሰጣቸዋል።
የአረንጓዴው ማሊያ እና የዳገት አንበሳ አሸናፊዎች፣ 21ዱን ዙሮች ላጠናቀቁ ተወዳዳሪዎች እያንዳንዳቸው የ25 ሺ ዩሮ ይሸለማሉ።
በሁለቱም ማሊያ ለሁለተኛ ደረጃ 15,000 ዩሮ፣ ለሦስተኛው 10,000 ዩሮ፣ ለአራተኛ 4,000 ዩሮ፣ ለአምስተኛ 3,500 ዩሮ፣ ለስድስተኛ 3,000 ዩሮ፣ ለሰባተኛ 2,500 ዩሮ እና ለስምንተኛ ደግሞ 2000 ዩሮ ይሰጣል።
በወጣቶች ነጭ ማሊያ በሰፊ ልዩነት አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ቤልጄየማዊው ሬምኮ ኤቨንፖኤል 20,000 ዩሮ ሲሸለም ሁለተኛው 15,000 ዩሮ፣ ሦስተኛው 10,000 ዩሮ እና አራተኛው 5,000 ዩሮ ተሸልመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በእያንዳንዱ መድረክ የበለጠ ፉክክር ላደረገ ተወዳዳሪ 2000 ዩሮ ይሸለማል፤ በአጠቃላይ ውድድሩ የበለጠ ተፎካካሪ ሆኖ ላጠናቀቀ ደግሞ 20 ሺ ዩሮ ይሰጣል።
በቡድን አንደኛ የወጣው ክለብ የ50,000 ዩሮ ይሸለማል። ይህንም የቡዱኑ ተወዳዳሪዎች ይከፋፈሉታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የብስክሌት ውድድሮች ደረጃቸው በምን ይለያያል?
ፊፋ የእግር ኳስ ውድድርን እንደሚቆጣጠር ሁሉ የብስክሌት ውድድርን የሚቆጣጠረው ዓለም አቀፉ የብስክሌተኞች ማኅበር (ዩሲአይ) የውድድሮችን ደረጃ የሚያወጣበት የራሱ አሰራር አለው።
የብስክሌት ውድድሮች በተለያዩ ደረጃዎች እና ዙሮች የሚካሄዱ ሲሆን፣ በአንድ ቀን የሚካሄዱ ውድድሮች እንዳሉ ሁሉ በተለያዩ ዙሮች በበርካታ ቀናት የሚደረጉመ አሉ።
የብስክሌት ውድድር ደረጃዎች የየራሳቸው መለያ አላቸው፤ ይህንንም ለመግለጽ ደግሞ ዎርልድ ቱር. ፕሮ 2.1 እንዲሁም 2.2 እያለ ከከፍተኛ ወደ ዝቅተኛ ደረጃው ይለያል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ሦስት ውድድሮች ብቻ ናቸው፤ የፈረንሳይ ቱር ዴ ፍራንስ፣ የስፔኑ ቮልታ ስፓኛ እና የጣልያኑ ጂሮ ዲ ኢታሊያ እያንዳንዳቸው 21 ደረጃዎች አሏቸው።
1 ፕሮ ተብሎ የሚጠራው የአንድ ቀን ውድድር ሲሆን፣ ዩሲአይ የዝግጅቱን ጥራት እና ዓይነት በመገምገም የሚሰጠው ደረጃ ነው።
2.1 ተብሎ የሚጠራው እስከ ስምንት መድረኮችን ያካተተ ውድድር ነው። አፍሪካ ውስጥ በዚህ ደረጃ የሚካሄዱ ውድድሮች ሁለት ብቻ ናቸው። እነሱም ቱር ሩዋንዳ እና የጋቦኑ ላ ትሮፒካለ አሚሳ ባንጎ ናቸው።
2.2 ተብሎ የሚጠራው ከ2.1 ዝቅ ያለ ደረጃ ያለው ውድድር ሲሆን በአምስት መድረኮች ይካሄዳል።












