ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኡጋንዳ እና ሆንዱራንስ ከአሜሪካ የሚባረሩ ስደተኞችን ለመቀበል ተስማሙ
አሜሪካ ሕገ ወጥ ስደቶችን ወደ ኡጋንዳ እና ሆንዱራንስ ለመላክ የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ መድረሷን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ያገኘው መረጃ አመለከተ።
ኡጋንዳ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ ያልተገለፀ በሜክሲኮ ድንበር ጥገኝነት የጠየቁትን የአፍሪካ እና የእስያ ስደተኞችን ለመቀበል የተስማማች ሲሆን፣ ሆንዱራስ ደግሞ ከስፓኒሽ ተናጋሪ አገራት የመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን እንደምትቀበል ሲቢኤስ ዘግቧል።
እርምጃው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ብዙ አገራት ከአሜሪካ የሚባረሩ የራሳቸው ዜጋ ያልሆኑ ስደተኞችን እንዲቀበሉ ለማድረግ የሚያደርገው ሙከራ አካል ነው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ፖሊሲውን አውግዘው፣ ስደተኞች ጉዳት ሊደርስባቸው ወደሚችልባቸው አገራት የመላክ ስጋት አለባቸው ብለዋል።
በስምምነቱ መሠረት ኡጋንዳ የተባረሩት ስደተኞች የወንጀል ታሪክ እስከሌላቸው ድረስ ለመቀበል የተስማማች ሲሆን ምን ያህል ስደተኞችን እንደምትቀበል ግን ግልፅ አይደለም ሲል ሲቢኤስ ዘግቧል።
ሆንዱራስ ከልጆች ጋር የሚጓዙ ቤተሰቦችን ጨምሮ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ስደተኞችን ለመቀበል የተስማማች ሲሆን ሲቢኤስ የተመለከተው ሰነድ ግን ለረዥም ዓመት ልትቀበል እንደምትችል ይጠቁማል።
ሁለቱም ስምምነቶች የትራምፕ አስተዳደር በተለያዩ አህጉራት ከሚገኙ አገራት ጋር፣ አከራካሪ የሆኑ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ያላቸውን ጨምሮ፣ ከአሜሪካ የሚባረሩ ስደተኞችን እንዲቀበሉ የሚያደርጉት ጥረት አካል ነው።
እስካሁን ድረስ በርካታ አገራት ከሌላ አገር የሚባረሩ ስደተኞችን ለመቀበል ተስማምተዋል።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፓራጓይ ጋር "ሕገወጥ ስደትን የመቆጣጠር ሸክሙን ለመጋራት" በሚል "ደህንነቱ የተጠበቀ ሦስተኛ አገር" ስምምነት መፈራረሙን አስታውቋል።
ዋይት ሐውስ ከበርካታ የአፍሪካ አገራት ጋር በቅርበት እየሰራ ሲሆን ሩዋንዳ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከአሜሪካ እስከ 250 ስደተኞችን እንደምትወስድ ተናግራለች።
በስምምነቱ ቅድመ ሁኔታ መሠረት ሩዋንዳ "ለመልሶ ማቋቋም የሚቀረበውን እያንዳንዱን ግለሰብ የማጽደቅ መብት እንዳላት" የመንግሥት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሩዋንዳ ቀደም ሲል ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የሚላኩ ዳግም ችግር ሊገጥማቸው ወደሚችልባቸው አገራት ሊባረሩ ይችላሉ የሚለውን ስጋት ጨምሮ በሰብዓዊ መብት አያያዝዋ ትወቀሳለች።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ፓናማ እና ኮስታሪካ በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን እና እስያውያን ስደተኞችን ከአሜሪካ ለመውሰድ ተስማምተዋል።
የትራምፕ አስተዳደር የተባረሩ ስደተኞችን እንደ ኢኳዶር እና ስፔን ያሉ አገራት እንዲቀበሉ ማነጋገሩን ሲቢኤስ ዘግቧል።
ትራምፕ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቃል በገቡት መሠረት ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞችን ከአገር ለማስወጣት ሰፊ ጥረቶችን ጀምሯል።
በሰኔ ወር የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስደተኞች ሊገጥማቸው የሚችሉ የደህንነት ስጋቶችን ከግምት ሳያስገባ ዶናልድ ትራምፕ ከትውልድ አገራቸው ውጭ ወደሌሎች አገራት ማባረራቸውን እንዲቀጥሉ ፈቃድ ሰጥቷል።
በወቅቱ ዳኛ ሶንያ ሶቶማዮር፣ ኤሌና ካጋን እና ኬታንጂ ብራውን ጃክሰን ውሳኔውን "ከባድ በደል" በማለት የአብላጫውን ውሳኔ ተቃወመዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የመብት ባለሙያዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ስደተኞቹ የትውልድ ቦታቸው ባልሆነ አገር መውሰድ ዓለም አቀፍ ሕግን ሊጥስ ይችላል ሲሉ ተከራክረዋል ።