ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግሽበት፡ "ሁሉም ነገር እየጨመረ ነው፤ ከወራት በፊት 5 ብር የነበረው የዳቦ ዋጋ 10 ብር ገብቷል"
ክብረአብ ምስግና ለሁለት ዓመት በዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት በተቀዛቀዘችው መቀለ ነዋሪ ነው።
ደመወዝና መንግሥታዊ አገልግሎት ባልነበረበት፣ ለረዥም ወራት ከባድ ህይወት አሳልፈዋል።
ከፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት በኋላ ኑሮ የተሻለ እንደሆነ ቢገልጽም የሸቀጦች ዋጋ ግን በየቀኑ የተለያየ ሆኗል።
“በጦርነቱ ጊዜ የከፋ ችግር ስላሳለፍን አሁን የተሻለ ይኹን እንጂ ኑሮ በጣም ውድ ነው። ብዙ ሰው ደመወዝ እየተከፈለው አይደለም” ይላል።
“ለምሳሌ የጤፍ ዋጋ በየቀኑ ይቀያየራል። ባለፈው በአማራ ክልል ግጭት መቀስቀሱ ሲነገር በጣም ጨምሮ ነበር። አሁን ትንሽ መሻሻል አሳይቷል” ይላል።
በአብዛኛው ለሚደረጉት የዋጋ ጭማሪዎች ወደ ክልሉ የሚያስገቡ መንገዶች መዘጋታቸው እንደ ምክንያት ይቀርባል።
ከሸቀጦች ዋጋ መጨመር ባለፈ በከተማው የሚታየው የቤት ኪራይ መወደድ የሕዝቡን ሕይወት እየተፈታተነ ይገኛል።
“ደህና ቤት ብትጠይቅ ሃያ እና ሰላሳ ሺህ ነው የሚጠሩልህ። የቤት ኪራይ የሚቀመስ አይደለም” ብሏል ክብረአብ።
“በገቢያችን እና በወጪያችን መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ”
ያለፉትን አስር ዓመታት በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሠማራው ኤቢሣ ነዋሪነቱ በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን ባለትዳር እና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነው።
በኮንስትራክሽን ዕቃዎች መወደድ ምክንያት ሥራ ካቆመ ሦስት ወራት ተቆጥረዋል።
ሥራው ለመጀመር በጉጉት እየጠበቀ ነው።
ኤቢሣ የሸቀጦች ዋጋ መጨመር ከገቢ ማጣቱ ጋር ተዳምሮ ኑሮውን ከድጡ ወደ ማጡ ከቶታል።
“ሁሉም ነገር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው። ከወራት በፊት 5 ብር የነበረው የዳቦ ዋጋ 10 ብር ገብቷል። 10 ብር የነበረው ደግሞ 15 ሆኗል። አስገራሚው ነገር ዋጋው መጨመሩ ብቻ ሳይሆን የዳቦው ግራም መቀነሱ ነው” ብሏል።
“ሁሉም ነገር ለምን እንደተወደደ ማንም አይነግርህም። ለምን ተወደደ ስንል የአቅርቦት ችግር መኖሩ ይነገረናል። ማንን መጠየቅ እንዳለብንም አናውቅም” ሲል ገልጿል።
8000 ወርሃዊ ደመወዝ ቢኖረውም ከገቢው አንጻር የዋጋ ውድነቱን መቋቋም ያልቻለው ኤቢሣ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በተመሳሳይ እየተፈተኑ መሆኑን ታዝቧል።
“አንድ ክፍል ቤት በ3 ሺህ500 ብር ተከራይቻለሁ። ልጄን ትምህርት ቤት ለማድረስ እና ለመመለስ በቀን 25 ብር አውጣለሁ። ስለዚህ ወርሃዊ ወጪዬን ማሰብ ይቻላል” ብሏል።
“5 ሊትር ዘይት 1100 ብር እንገዛለን። ጤፍ እንደደረጃው በኪሎ ከ100 እስከ 150 ብር ደርሷል። እንደ ቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና ምስር ያሉት ዋጋቸው ከሰሞኑ በእጥፍ ጨምሯል። በገቢያችን እና በወጪያችን መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። ለማን አቤት እንደሚባል አላውቅም” ሲል ገልጿል።
“በዓል ሆነም አልሆነም ዋጋ ይጨምራል”
ሌላው የአዲስ አበባ ነዋሪ ቶሎሣ ሌሊሳ ከሁለት ልጆቹ እና ከባለቤቱ ጋር አንድ ክፍል ቤት ተከራይቶ ይኖራል።
በኮንስትራክሽን ዘርፍ ተሠማርቶ በወር ከ8ሺህ 500 ብር በላይ ያገኛል። ገቢውና ወጪው ግን እንደማይመጣጠን ያስረዳል።
“ጥሩ ጤፍ በኪሎ ከ100-130 ብር ነው። ዳቦ ደግሞ ግራሙ ቀንሶ ዋጋው ጨምሮ እየተሸጠ ነው” ሲል በከተማዋ ያለውን የኑሮ ውድነት እያማረረ ገልጿል።
በፊት በበዓላት ወቅት የዋጋ ጭማሪ መኖሩና በዓል ሲያልፍ ዋጋ መቀነሱ የተለመደ መሆኑን በማስታወስ “አሁን ግን በዓል ሆነም አልሆነም ዋጋ ይጨምራል” ብሏል።
ነጋዴዎች ሸቀጦችን ከገበያ እስኪጠፋ ደብቀው ያስቀምጣሉ የሚለው ቶሎሳ፣ “ማንም ስለማይቆጣጠረው እየተጎዳን ነው። ባለስልጣናት ችግሩን የነጋዴዎች ነው ይላሉ። ነጋዴዎች ደግሞ መንግሥትን ይወቅሳሉ” በማለት ያለውን ሁኔታ ጠቅሷል።
“ሰዎች በልተው ማደር የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል”
ገበያ ላይ ባሉ በምግብ ነክና ምግብ ነክ ባልሆኑ ላይ ከፍተኛ ዋጋ መከሰቱን የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ጥላሁን ግርማም ይገልጻሉ።
አቶ ጥላሁን የቢዝነስ አማካሪ እና የምጣኔ ኃብት ባለሙያ ናቸው።
በአዲስ አበባ እየታየ ያለውን የዋጋ መጨመር ‘አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሊቋቋሙ የማይችሉት ዓይነት ነው’ ብለውታል።
“ጤፍን ጨምሮ መሠረታዊ ምግብ ነክ እህሎች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አለ። በቀንና በማታ እንኳን ዋጋ ይጨምራል” ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ ምግብ ነክ ያልሆኑ እንደ ሲሚንቶና ብረት ያሉትም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያሳዩ ነው።
“ለመግለጽ የሚከብድ ሰዎች በልተው ማደር የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል” ሲሉ ገልጸውታል።
ጤፍ ከፍተኛ ጭማሪ ከማሳየቱም በላይ በሚቀጥለው ዓመትም ይጨምራል የሚል ስጋትም ተፈጥሯል።
ምግብ ቤቶች በየዕለቱ ዋጋ እንደሚጨምሩ እና ጭማሪው ባለመቆሙ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ለችግር የተጋለጡበት ነው።
መንግሥት የዋጋ ንረቱ 30 በመቶ ደርሷል ቢልም ከ 50 በመቶ በላይ ስለመድረሱ የሚያሳዩ ምልክቶች መኖራቸውን ጥላሁን ጠቁመዋል።
ለገጽታ ግንባታ ሲባል መንግሥት ያለ ዕቅድ ገባበት ያሉት የስንዴ ኤክስፖርት ደግሞ ቀዳሚው ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።
በዓለም አቀፍ ገበያ የስንዴ ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ ኤክስፖርቱን ለማሳካት መንግሥት የስንዴ ዋጋ ላይ ተመን ከመፍጠር ባለፈ ኬላዎችን ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የመንግሥት ዋጋ ያላስደሰታቸው ደግሞ የተቋቋሙ ኬላዎችን ለማለፍ ሲሉ የስንዴ ኮንትሮባንድ ውስጥ ገብተዋል።
በዚህ ምክንያትም ስንዴ ዋጋ በመጨመሩ ከፍተኛ የስንዴ እጥረት ተፈጥሯል።
“ብዙ ፋብሪካዎች የመዘጋት አደጋ ተፈጥሮባቸዋል። የመጨረሻ ዕዳው ሸማቹ ላይ እንዲወድቅ ሆኗል” ብለዋል።
ከጤፍ ጋር ተያይዞ ማዳበሪያ በወቅቱ አለመቅረቡ ስጋት መፍጠሩን እና ለከርሞም ዋጋው ይወደዳል በሚል ገዝተው የሚያስቀምጡም መኖራቸውን ተናግረዋል።
“ይህ ሁሉ የመንግሥት ድክመት ነው። በአማራና በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት የተነሳ ዋጋው በሚቀጥለው ዓመትም ይጨመራል ተብሏል” ብለዋል።
በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም ስንዴ እና የዘይት ዋጋ መጨመርም ሌላው ለአገር ውስጥ የዋጋ መጨመር እንደ ምክንያት ይቀርባል።
“የነዳጅ ዋጋም በጦርነቱ ምክንያት ጨምሯል። መንግሥት በተደጋጋሚ የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ አድርጓል። (ከሰሞኑ በነዳጅ ዋጋ ላይ ከተደረገው የዋጋ ጭማሪ በፊት ነው ይህ ቃለ መጠይቅ የተከናወነው)። ይህ ደግሞ እያንዳንዱ ሸቀጥ ላይ እሳት ለኩሷል። ኢትዮጵያ ውስጥ ነዳጅ ከጨመረ (ከነዳጅ ጋር የማይገናኘውም) ተያይዞ ይጨምራል። የሚደረገው ጭማሪውም ከነዳጅ ጭማሪዊ የበለጠ ነው” ብለዋል።
ሌላው ያነሱት ተግዳሮት ደግሞ ዘመናዊ የገበያ ትስስር አለመኖርን ነው።
በአምራቾች እና በሸማቾች መካከል በርካታ ደላላዎች መኖራቸውንም እንደ ችግር አንስተዋል። በእያንዳንዱ ግለሰብ እጅ ሲያልፍ ዋጋው ይጨምራል።
ከፍተኛ ገንዘብ ፍሰት መኖሩንም ሌላኛው ባለሙያው ያስቀመጡት ምክንያት ነው።
“ብዙ ገንዘብ ሰው እጅ ካለና ምርት አነስተኛ ከሆነ ለዋጋ ንረት መባባስ ምክንያት ይሆናል” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከውጭ የሚገባውም ሆነ አገር ውስጥ የሚመረተው ሸቀጥ እጥረት አለ።
በአገር ውስጥ ያሉ አለመረጋጋቶች፣ የሠላም ሁኔታ፣ ሰዎችን እና ምርቶችን ለመጓጓዝ አዳጋች ሁኔታዎች መፈጠራቸው፣ ኬላዎች በየቦታው መቋቋማቸው. . . ገበያ ላይ ያለውን አቅርቦት ዝቅተኛ አድርገውታል።
“ወደ ማህበራዊ ግጭትና ቀውስ ሊያመራ ይችላል”
አቶ ጥላሁን ግማሹ በልቶ ግማሹ በማይበላባት አገር ላይ ወንጀሎች እንደሚስፋፉና የማህበራዊ ቀውስ እንደሚፈጠር ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
“አንዳንድ ቦታ ገብተህ ሙስና መስጠት ግዴታ ሆኗል። አሁን የተለመደ እየሆነ ነው። ምክንያቱም ደመወዛቸው አያኖራቸውም።”
“በጊዜ ማሻሻያ ካልተደረገ ነገ ወደ ማህበራዊ ግጭት፣ ቀውስና ተቃውሞ ሊያመራ ይችላል” ሲሉ ሙያዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።
እንደ ሱዳን ባሉ አገራት የዳቦ ዋጋ በሳንቲም መጨመሩ ቀውስ ውስጥ እንደከተታቸው እያየን ነው የሚሉት ጥላሁን “እንደውም [ኢትዮጵያ ውስጥ] ሰዉ ስለሚረዳዳ ነው። የማህበራዊ እና ቤተሰብ ትስስር ስላለው ነው። ያላቸው ሰዎች ወደ ተረጂነት ሲገቡ ቀውስ ያመጣል” ብለዋል።
አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በየትራፊክ መብራቱ ላይ ማየት መለመዱን አንስተው “አንዳንዶች ቤተሰቦች ናቸው። በአዲስ አበባ በዓመታት ታሪክ እንዲህ አይነት ነገር ታይቶ አያውቅም” ብለዋል።
“ለመንግሥትም ከባድ ነው የሚሆነው። ወደ ጎዳና የሚወጣው ሰው በጨመረ ቁጥር ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል። ነገ ከነገ ወዲያ ለሠላም እጦት እና እርስ በእርስ ግጭት ምክንያት ስለሚሆን በጊዜ መላ ሊባል ይገባል።”
“ሠላሙ መረጋገጥ ቢችል ብዙ ነገር ይረጋጋል”
ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ለመንግሥት የሚሰጠውን የቀጥታ የብድር መጠንን መገደብን ጨምሮ የዋጋ ንረቱን ሊያረጋጉ የሚችሉ ያላቸውን የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ መወሰኑን አስታወቋል።
የመንግሥት ወጪ ዕድገት እንዲገደብ፣ የበጀት ጉድለቱን ከጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት አኳያ እንዲቀንስ ተደርጓል።
ይህ እርምጃም መንግሥት ከአገር ውስጥ ባንኮች በተለይም ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደውን የብድር መጠን እንዲቀንስ እንደሚያደርገው ነው የባንኩ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ያስረዱት።
በ2016 በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ የአገር ውስጥ ብድር እድገት በ14 በመቶ ጣሪያ ይገደባል። ሁሉም ንግድ ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸውን በዚህ የብድር ጣሪያ መሠረት እንዲያስተካክሉ ይደረጋልም ተብሏል።
የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው ከብሔራዊ ባንክ በሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ ብድር ላይ የሚከፍሉት የወለድ መጠንም ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል ይደረጋል።
ፖሊሲው በወጪ ንግድ ላይ በመሳተፍ የውጭ ምንዛሪ በሚያስገኙ ዘርፎች ላይ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
“የብድር ገደቡ የተወሰኑ ዘርፎችን ባይመለከት ብዬ አስባለሁ” የሚሉት ጥላሁን “ባንኮች አዲስ ብድራቸውን 14 በመቶ ብቻ እንዲያሳድጉ መደረጉ ብዙ ገንዘብ ሰው እጅ እንዳይገባ ያደርጋል። ብዙ ገንዘብ ይዘው መጋዘን ውስጥ ምርት የሚያከማቹትን ይይዛል። ዋናውን የዋጋ ንረትን ይቆጣጠራል” ብለዋል።
ፖሊሲው ምን ለውጥ ያመጣል የሚለውን ለመገምገም ሁለት ወር ሦስት ወር መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
ችግሩ ግን ከብሔራዊ ባንክ ድንበር ውጭ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተውታል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ የሠላም፣ የአቅርቦት እና የፍላጎት ጉዳዮችን ደግሞ አንስተዋል።
“ዜጎች የሚታፈኑበት፤ ከዋና ከተማ መውጣት በሚፈራበት አገር ላይ ፖሊሲው ብቻ ችግሩን አይመልሰውም” ብለዋል።
“ሠላሙ መረጋገጥ ቢችል ብዙ ነገር ይረጋጋል። የጤፍ አዝመራ አለፈብን ብለው ሰልፍ የወጡ ብዙ ናቸው። አንዳንድ ይቅርታ ቢጠየቅም ሃገሩ ኢትጵያ ስለሆነ ነው እንጂ ሚኒስትሮች ስልጣን የሚለቁበት ጉዳይ መሆን ነበረበት።”
መንግሥት ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት ማድረግ፤ የገበያ አቅርቦት እንዲኖር አምራች እና ሸማቾችን ማስተሳሰርና ደላሎችን መቀነስ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
“የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መንግሥት አንደኛ እና ዋነኛ ተግዳሮት የሆኑ ኮንትሮባንዲስቶች ናቸው።”
“ሠላም የነበረው የሲሚንቶ ንግድ የኮንትሮባንዲስቶች ሆኖ አረፈው ይህ ሲነካ ሰው እስከ መግደል ተደረሰ። ግንባታ ላይ ለመጣው መበጥበጥ ኮንትሮባንዲስቶች ዋነኛው ምክንያት ናቸው። ማዳበሪያም በኮንትሮባንዲስቶች መሸጥ ጀምሯል። እያንዳንዱን ነገር ኮንትሮባንድ የመሆኑ ነገር እንዴት መጣ የሚለው መታየት አለበት። የማያወላውል እርምጃ መወሰድ አለበት። የሚሰማው የሚያም ነው። ታጣቂዎችም አሉበት ይባላል። ማዳበሪያ በውድ የገዛ ገበሬ ዋጋ ቀንሶ አይሸጥም” ብለዋል።
መንግሥት መሰረታዊ ሸቀጦችን እየገዛ በአምራቾች ህብረት ስራ በኩል በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ማቅረብ እንዳለበት ጠቅሰው “የመንግሥት ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። ኮንትሮባንዲስቶች ከአቅርቦት አንጻር ትልቅ ነገር ማድረግ አለበት ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።