የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ዕይታ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ነሐሴ 01/2015 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሰኔ መሠረት የተለያዩ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረጉን በቅርቡ አስታውቋል።

እነዚህ ማሻሻያዎች የዋጋ ንረትን በወሳኝ እና ተከታታይ በሆነ ሂደት ለመቀነስ ያለመ መሆኑን የባንኩ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ባለፈው ሳምንት ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ኮቪድ፣ ጦርነት እና ድርቅ፣ የመንግሥት ገቢ ማነስ፣ የወጪ ጫና መብዛት እና በመሳሰሉት ምክንያቶች የተነሳ የአገሪቱ የገንዘብ ችግሮች ሰፍተው እና ጎልተው መታየታቸውን የባንኩ ገዢ ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት የመንግሥት የበጀት ጉድለት መጨመሩ እንዲሁም የውጭ ብድር እና እርዳታ ውስን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አብዛኛውን የበጀት ጉድለት ከአገር ውስጥ የገንዘብ ምንጮች በሚገኝ ብድር ለመሸፈን ግዴታ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።

በብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ መሠረት በሚቀጥለው በ2016 ዓ.ም. የበጀት ዓመት መጨረሻ የአገር ውስጥ የብድር ዕድገት በ14 በመቶ እንዲገደብ ተወስኗል።

የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አብዱልመናን መሐመድ “የአቅርቦት፣ የመዋቅር እና የፊስካል ችግርን” ለአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ምክንያት ብሎ ብሔራዊ ባንክ ማቅረቡን ገልጸዋል።

በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ ገበያው ከሚችለው በላይ የገንዘብ ስርጭት መኖሩ እንደ አንድ ምክንያት የተጠቀሰ ሲሆን፣ ለዚህም “ኢኮኖሚው ውስጥ ገንዘብ የሚበዛው ባንኮች በሚሰጡት ብድር ነው። ብሔራዊ ባንክ ይህንን መቆጣጠር ይገባዋል” ይላሉ ባለሙያው።

ባንኩ የአገር ውስጥ ብድር ዕድገትን በ14 በመቶ መገደቡ ቀጥተኛ (ቀጥተኛ ያልሆኑ መቆጣጠሪያዎችም አሉ) የሚባለው መቆጣጠሪያ ዘዴ መሆኑን አንስተዋል። ይህም በቀጥታ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ለመቆጣጠር የብድር መጠንን መገደብ እንደሆነ ገልጸዋል። “ዓላማውም የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በኩዌት ኢንስቲትዩት ፎር ሳይንቲፊክ ሪሰርች የኢኮኖሚ አጥኚ የሆኑት አየለ ገላን፣ ባለፈው ዓመት የባንኮች አማካኝ የብድር ዕድገት 30 በመቶ እንደነበር ያስታውሳሉ።

አክለውም ከዚህ ውስጥ የግል ባንኮች የብድር እድገት 16 በመቶ ሲሆን የመንግሥት ባንኮች ደግሞ 53 በመቶ እንደነበር ጠቅሰው፣ “በዋጋ ግሽበት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ የሚገኘው የመንግሥት ባንኮች የሚሰጡት ብድር ነው” ይላሉ።

ያደጉ አገራት የዋጋ ግሽበት ሲጨምር ባንኮች እንዳያበድሩ ያደርጋሉ። ምክንያቱም የተበደረ ሰው አዲስ ምርት ለገበያ ያቀርባል ተብሎ ስለማይጠበቅ መሆኑን በመግለጽ፣ ብድር እና የዋጋ ግሽበት የሚያያዘው ባደጉ አገራት መሆኑን የብራራሉ።

የሥራ አጥ ቁጥሩ ከ30 አስከ 40 በመቶ በሆነባት ኢትዮጵያ ብድር በመስጠት ሥራ አጦች ሥራ እንዲፈጥሩ፣ እንዲያመርቱ ማድረግ ሲገባ ብድርን በመቆጣጠር ዋጋ ግሽበትን እንከላከላለን ማለት “እሳት ላይ ነዳጅ” እንደመጨመር ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ምክንያቱም የዋጋ ግሽበቱ የመጣው ገበያ ላይ ምርት በመታጣቱ ነው በማለት በምሳሌነት የሚያነሱት የእንቁላልን ዋጋ ነው። የእንቁላል ዋጋ እየጨመረ ያለው በቂ ምርት ባለመኖሩ ነው ይላሉ።

“ብሔራዊ ባንክም የመግዛት አቅም ላይ ሳይሆን፣ አቅርቦት ላይ ችግር እንዳለ አምኗል” የሚሉት አየለ፣ የዋጋ ግሽበቱን ብድርን በመቆጣጠር ነው የምንወጣው ማለታቸው ግን “ከራሳቸው ሃሳብ ጋር የተቃረነ” መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ባለፈው ዓመት 428 ቢሊዮን ብር ብድር መሰጠቱን የሚጠቅሱት እኚህ ምሁር ከዚህ ውስጥ ለግብርና፣ ለኢንደስትሪ እና ለማኑፋክቸሪንግ የደረሰው ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ገበያ ላይ የሚፈለጉ የግብርና እና የኢንደስትሪ ምርቶች ተገቢውን ብድር አላገኙም ማለት መሆኑን ያብራራሉ።

“አብዛኛውን ብድር ያገኙት የወጭ ገቢ ንግድ ላይ ያሉት ናቸው። እነዚህ ዘርፎች ያገኙት ብድር ካለፈው ዓመት 400 በመቶ ጨምሯል” ብለዋል።

ብሔራዊ ባንክ ብድር መገደቡን ትቶ ይልቁንም መጨመር አለበት በማለት “ብድሩ የሚሰጠውም ምርት ለሚያመርቱ ቢሆን ጥሩ ነው” ሲሉም አቶ አየለ ይከራከራሉ።

ምጣኔ ሀብት ባለሙያው አብዱልመናን ግን ከጥቂት ዓመታት በፊት ተመሳሳይ እርምጃ ተወስዶ የዋጋ ግሽበትን ወደ አንድ አሃዝ ለማውረድ ተችሎ እንደነበር ያስታውሳሉ።

አክለውም የአሁኑ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ “ውጤት አለው” ቢሉም አሉታዊ ውጤት ሊኖረውም እንደሚችል ግን አልሸሸጉም።

የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ በ30 በመቶ ገደማ እያደገ የነበረውን የባንኮች ዓመታዊ ብድር “በ14 በመቶ መገደብ ከግማሽ በታች ማውረድ ማለት ነው” ብለዋል አብዱል መናን።

ለዚህም ምሳሌ ሲጠቅሱ አንድ መኪና እየተጓዘ ከነበረበት ከፍተኛ ፍጥነት ወዲያውኑ በግማሽ እንዲቀንስ ቢደረግ መገልበጥ ሊያስከትል ይችላል ይላሉ።

ጨምረውም ውሳኔው ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መቀነስ ሊያስከትል እንደሚችልም ስጋታቸውን በመጥቀስ፣ በብድር የሚንቀሳቀሰው የግንባታው ዘርፍ፤ ብድር የማጣት እና የንብረት ዋጋ መቀነስ ሊከሰትበት ይችላል።

የሁለቱ ድምር የተበዳሪዎችን የመክፈል አቅም አዳክሞ “በዋስትና የተያዙ ንብረቶችን ዋጋ በመቀነስ ባንኮች ላይ ችግር ሊያመጣ ይችላል” ብለዋል።

ውሳኔው የባንኮችን የማበደር አቅም ስለሚገድብ “ባንኮች ተበዳሪዎችን መምረጥ እና ‘ሬሽን’ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል። እንዲሁም ባንኮች የሚያበድሩት ገንዘብ ስለሚቀነስ ወደ ሙስና ሊያመራ ይችላል” ሲሉ ይሰጋሉ።

ባንኮች የማበደሪያ ወለዳቸውን ሊጨምሩ እንደሚችሉም አንስተዋል።

“ዋጋ ቢያረጋጋም የባንክ ሴክተሩ እንዳይረጋጋ ሊያደርግ ይችላል። የተበላሸ ብድርም ሊጨምር ይችላል። የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ደግሞ የብድር መክፍል አቅምን ሊቀንስ ይችላል” ብለዋል።

የመንግሥት ብድር ይቀንስ የሚል እምነት የሌላቸው አቶ አየለ፣ ብሔራዊ ባንክ መንግሥት የሚወስደውን ብድር መገደቡን በተመለከተ የተለየ ሃሳብ አላቸው።

“መንግሥት ያንን ሁሉ መበደር አለበት ብዬ ስለማምን ሳይሆን፣ አገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ [በጦርነት እና በሌሎች ነገሮች] ለአሁኑ መታገስ ያስፈልጋል ብዬ ስለማምን ነው። መቀነስ ትክክል ነው፤ ግን አሁን አይደለም” ብለዋል።

ብሔራዊ ባንክ ባንኮች በሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ ብድር ላይ የሚከፍሉት የወለድ መጠንም ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲልም አድርጓል።

አቶ አየለ ይህንንም አይስማሙበትም። “የብድር ዕድገቱ በ14 በመቶ መቀነሱ ትክልል ቢሆን ኖሮ ይህም ትክክል ይሆን ነበር” ይላሉ።

ባንኮች ቢዝነስ እና ኢንቨስትመንትን ለማበረታት የሚሰጡት የብድር ወለድ ከ5 በመቶ መብለጥ እንደሌለበትም ያነሳሉ።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ባንኮች በ18 እና 20 በመቶ ወለድ እያበደሩ ነው። አንዳንድ ማይክሮ ፋይናንሶች ደግሞ እስከ 29 በመቶ በሚደርስ ወለድ እንደሚያበድሩ እሰማለሁ። አሁን ያለው ሁኔታ አራጣ ይመስላል። ይህ ትልቅ የኢኮኖሚ ወንጀል ነው” ይላሉ።

መደረግ ያለበት የብድር አቀርቦትን በማብዛት ወለድን በመቀነስ ደሃው ራሱንም ቀይሮ አገሩንም እንዲቀይር ማገዝ አስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ።

ብሔራዊ ባንክ የብድር ወለዱን 18 በመቶ ካደረገ ባንኮች ደግሞ 22 በመቶ እንዲያሳድጉት ይገደዳሉ በማለት “ይህ የኢኮኖሚ ችግሩን ከመሠረቱ ከመፍታት ይልቅ የሚያባብሰው ነው። ምን እያሰቡ እንደሆነ አላውቅም” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች ከተቀማጭ ገንዘባቸው ሰባት በመቶውን ብሔራዊ ባንክ በካሽ መልኩ ያስቀምጣሉ። ባንኮቹ ለእርስ በእርስ ለክፍያም የሚሆን አካውንት አላቸው። በዚህ ሂደትም ባንኮች ብዙ ብድር ሲሰጡ የገንዘብ እጥረት ያጋጥማቸዋል።

ከሰሞኑ በተደጋጋሚ ባንኮች የሊኩውዲቲ (የገንዘብ እጥረት) ችግር እንዳለባቸው የሚነሳው ከዚህ የመነጨ መሆኑን የሚጠቅሱት አብዱልመናን፣ ይህ ሲሆን “ባንኮቹ ለሕብረተሰቡም ሆነ እርስ በእርስ ለመከፋፍል ይቸገራሉ” ብለዋል።

እንዲህ ያለው የገንዘብ እጥረት በሚገጥማቸው ወቅት ባንኮቹ ፊታቸውን ወደ ብሔራዊ ባንክ ያዞራሉ። ብሔራዊ ባንክ ቀደም ሲል በ16 በመቶ ወለድ ይሰጥ የነበረውን ይህንን ብድር ነው ወደ 18 በመቶ ያሳደገው።

“ዓላማው ባንኮቹን ሥርዓት ማስያዝ ነው። ...ብሔራዊ ባንክ ብድር የምትፈልጉ ከሆነ ብዙ ወለድ ነው የማስከፍላችሁ እያለ ቆንጠጥ እያደረጋቸው ነው።”

ውሳኔውን አዎንታዊ ነው የሚሉት አብዱልመናን፣ ገንዘብ እጥረት ተፈጥሮ ሳይሆን ባንኮቹ በርካታ ብድር በመስጠታቸው ባንኮቹን ሥርዓት ማስያዝ ለብሔራዊ ባንክ ተገቢ እና አስፈላጊም መሆኑን በመጥቀስ ነው።

“ባንኮቹ ሊኩውዲቲ አስተዳደር ላይ ቆፍጠን ማለት አለባቸው። ካልሆነ እና ወደ ብሔራዊ ባንክ ለብድር ከመጡ ከፍተኛ ወለድ ያስከፍላቸዋል ማለት ነው” ብለዋል።

ብሔራዊ ባንክ የላኪዎችን የውጭ ምንዛሪ የማስተላለፍ ግዴታም ከ70/30 ወደ 50/50 ቀመር እንዲሻሻል አድርጓል።

ይህንን የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ አብዱልመናን “በጣም ትልቅ እና ባንኩን የሚያስመሰግነው ነው” ብለዋል።

ቀደም ሲል ላኪዎች ኤክስፖርት ሲያደርጉ ብሔራዊ ባንክ 70 በመቶ፣ ባንኮች 10 በመቶ እና ላኪዎቹ ደግሞ 20 በመቶ ይከፋፈሉ ነበር።

70/30 ከሁለት ዓመት ገደማ አካባቢ መተግበር የጀመረ ነው። በአገሪቱ የነበረው ጦርነት እና ሌሎች ችግሮችም የመንግሥትን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት በማሳደጉ የተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ የክፍፍል ቀመር “የወጭ ንግድን አያበረታታም” ያሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ ብዙ ላኪዎች ደግሞ አስመጪዎች ጭምር በመሆናቸው፣ ልከው ባገኙት ገንዘብ ያስመጡበታል ይላሉ።

ለዚህ ነው ቀድሞውን ውሳኔ “የውጭ ንግዱን በጣም የሚጎዳ ውሳኔ ነበር” የሚሉት።

“ውሳኔው ተስፋ ሰጪ እና የወጭ ንግድን የሚያበረታታ ነው። ወደፊት ከዚህ የበለጠ ቢሻሻልላቸው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የወጭ ንግድ በጣም ወሳኝ ነው” ብለዋል።

“የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ ትልቅ ችግር ነው። ይህ ችግር በእኛ ዕድሜ ላይፈታ ይችላል። [ውሳኔው] ግን አንድ ጥሩ እርምጃ ነው። እንደዚህ ዓይነት እርምጃዎች በጎ ተጽዕኖ አላቸው” ብለው ያምናሉ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ በተቃራኒ የሚሄድ ይመስላል የሚሉት ደግሞ አየለ ናቸው።

አንድ ኤክስፖርተር ከአገር ውስጥ ምርት ወደ ውጭ ልኮ ዶላር ሲያገኝ ዶላሩ ለአገሪቱ እንደገባ እንደሚቆጠር ይገልጻሉ።

“አንድ ነጋዴ አገር ውስጥ በብር ገዝቶ በዶላር ከሸጠ በኋላ አገር ውስጥ ዶላሩን ወደ ብር ይቀየራል። ብሩን ተጠቅሞ ደግሞ መልሶ ይገዛል። ይህ ዑደት ይቀጥላል። አሁን ግን ቡና ሸጦ ዶላሩን ባንክ ያስቀምጣል። ሌላ ብር ስለሌለው ከመንግሥት ይበደራል።”

ዶላሩን በባንክ አስቀምጦ መንካት ያልፈለገው ነጋዴ ለመበደር ቅድሚያ ሲሰጠው አርሶ አደሩ ግን መበደር አልቻለም ይላሉ። “የአገሪቱ የባንክ ሥርዓት እንደዚህ በተቃራኒ ነው የሚሠራው ማለት ነው” ይላሉ።

ነጋዴው ያገኘውን ዶላር በባንክ ወደ ብር ቀይሮ በብሩ መልሶ መሥራት ነበረበት የሚሉት አየለ፣ ብሔራዊ ባንክ ይፋ ባደረገው ለውጥ መሠረት በማምረቻ ዘርፍ ጥሬ ዕቃ ከውጭ ለሚገዙ ዶላር ማስቀመጣቸው ትክክል መሆኑን ይናገራሉ።

“ዶላሩን ውጭ አገር ለሚጠቀሙት ለውጡ ጥሩ ነው። ከዚያ ውጭ ሁሉንም ኤክስፖርተር እንደ አንድ ማየት ዶላር እንዲያስቀምጡ እና የብድር ገበያውን እንዲያጨናንቁ ማድረግ የማይሆን ነገር ነው። የማያስፈልግ መብት ነው የሚሰጣቸው። ለአገር ውስጥ አምራቾች ቅደሚያ መስጠት ሲገባው ኤክስፖርተሮችን መንከባከብ ተገቢ አይደለም” ብለዋል።

የብሔራዊ ባንክ እርምጃ በሕዝቡ ኑሮ ላይ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል? የዋጋ ንረትን በማርገብ ረገድስ ምን ያህል ጠቀሜታ ይኖረዋል? በሚል የተጠየቁት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ ምላሻቸው የተደባለቀ ነው።

አብዱልመናን ‘ከፖሊሲው አንጻር’ እንደባለሙያ ጥሩ እርምጃ ነው ከማለት ባለፈ የዋጋ ንረት በጣም ይረጋል የሚል እምነት አላቸው።

“ብሔራዊ ባንክ ተጨባጩን ሁኔታ ያገናዘበ [ፕራግማቲክ] መሆን አለበት። ችግሮች ሲፈጠሩ ደግሞ እንደዚህ ከሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ [ፍሌክሰብል] እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ለውጡ የዋጋ ንረትን ስለማረጋጋቱ “ምንም ጥርጥር የለኝም” ቢሉም የተቀመጠው ቁጥር ላይ ይደረሳል የሚል እምነት ግን የላቸውም።

“ጠበቅ ያለ ሞኒታሪ ፖሊሲ የተከተሉ እንደሆነ ዋጋ ግሽበት ይቀንሳል የሚል እምነት አለኝ። ለኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት የገንዘብ መብዛት ነው ትልቁ ምክንያት። መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ እበደራለሁ የሚለውን እቀንሳለሁ ብሏል። በጣም ጥሩ እርምጃ ነው” ብለዋል።

ቢዝነስ የሚጀመረው በብድር ነው የሚሉት አየለ ብድሩ የሥራ ዕድል ስለሚፈጥር፣ በሚወሰደው የለውጥ እርምጃ ምክንያት የብርድር አቅርቦት ላይ ጫና ስለሚፈጠር በዋጋ ግሽበት ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ይኖራል ብለው አያሳቡም።

“ሥራ ሲኖር፣ ምርትም ይኖራል። ምርት ደግሞ ለገበያ ይቀርባል። ይህ ደግሞ የምርቱ ዋጋ እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርጋል። በአጠቃላይ የሁሉንም ሰው ቤት ይነካል። ስለዚህ ፖሊሲው ዋጋ ግሽበትን ይቀንሳል ብዬ አላምንም” ብለዋል።