ዩክሬንን ቀደም ብዬ መውረር ነበረብኝ - ቭላድሚር ፑቲን

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገራቸው ቀደም ብላ ዩክሬንን መውረር እና ለጦርነቱ የተሻለ ዝግጅት ማድረግ እንደነበረባት ገልጸዋል።

ሐሙስ ዕለት ባከናወኑት የዓመቱ የመጨረሻ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፑቲን እንደተናገሩት ከሆነ ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" በማለት ለሚጠሩት የ2022ቱ ወረራ "ጥንቅቅ ያለ ዝግጅት" መደረግ ነበረበት።

ሩሲያ እአአ በ2014 ክሬሚያን ከዩክሬን ነጥቃ ስትቆጣጠር የሩሲያ ደጋፊ ኃይሎች ደግሞ በምስራቃዊ ዩክሬን ግጭት ጀምረዋል። ፑቲን ኪየቭን ለመያዝ የሞከሩት ግን ከስምንት ዓመታት በኋላ ነበር።

አራት ሰዓታት በፈጀ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ፑቲን ከስልጣን ስለተነሱት የሶሪያው መሪ፣ ስለአዲሱ የኒውክሌር መመሪያ እና እንደ ምግብ ቅቤ ዋጋ ያሉ የአገር ውስጥ ጉዳዮችን ዳሰዋል።

"የዓመቱ ውጤቶች ከቭላድሚር ፑቲን ጋር" ተብሎ የተሰየመው ዝግጅት ሐሙስ ዕለት በዋናው የመንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በቀጥታ ተላልፏል።

ፑቲን ጥያቄዎችን ከሕዝቡ፣ ከውጭ ጋዜጠኞች እና ከጡረተኞች ቢቀበሉም ዝግጅቱ ግን በከፍተኛ ደረጃ የተቀናጀ እና ጥብቅ ቁጥጥር የተደረገበት ነበር።

የቢቢሲ ሩሲያ አዘጋጅ ስቲቭ ሮዘንበርግ ከ25 ዓመታት በፊት የቀድሞ መሪ ቦሪስ የልሲን ከለቀቁበት ጊዜ የተሻለች ሩስያን መፍጠር ስለመቻላቸው ይሰማቸው እንደሆነ ላቀረበላቸው ጥያቄ ፑቲን አገራቸው "ሉዓላዊነቷን" መመለሷን ገልጸዋል።

"ከዚያ በፊት በሩሲያ ላይ እየደረሰ ባለው ነገር ሙሉ በሙሉ ሉዓላዊነታችን ወደ ማጣት እየሄድን ነበር።"

በሶሪያ ለዓመታት ወታደራዊ ድጋፍ ሲሰጡት የነበረው የአሳድ መንግስት ስለመውደቁ የተጠየቁት ፑቲን፣ ይህ ለክሬምሊን ሽንፈት እንዳልሆነ አጥብቀው ተናግረዋል። ገር ግን ሁኔታው ​​"ውስብስብ" መሆኑን አምነዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አማጺ ኃይሎች ወደ ደማስቆ ሲቃረቡ ወደ ሞስኮ የሸሹትን የቀድሞውን የሶሪያ መሪ ባያናግሩም በቅርቡ ለመገናኘት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

አክለውም ሩሲያ ከአዲሶቹ የሶሪያ ገዥዎች ጋር በሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ ላይ የሚገኙትን ሁለት ስትራቴጂካዊ የጦር ሰፈሮችን ለማቆየት እየተነጋገረች እንደሆነ እና ለሰብዓዊ አገልግሎት ልትጠቀምባቸው እንደምትችል አስረድተዋል።

ተመራጩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን በተመለከተ ደግሞ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ አለመነጋገራቸውን የጠቆሙት ፑቲን "[ትራምፕ] ከፈለጉ" ሊያገኟቸው ዝግጁ መሆናቸውን አክለዋል።

በጥር ወር ስልጣን ሊይዙ ከተዘጋጁት ትራምፕ ጋር ሲነጻጸሩ ደካማ አቋም ላይ ስለመሆናቸው ለቀረበላቸው ጥያቄ ደግሞ የአሜሪካዊው ጸሐፊ ማርክ ትዌይን "የመሞቴ ወሬ በጣም የተጋነነ ነው" የሚለውን ንግግር በማጣቀስ ፑቲን ሲመልሱ በስብሰባ አዳራሹ ብዙዎች ስቀዋል።

ቻይናን በተመለከተ ደግሞ ሩሲያ ከምስራቃዊ ጎረቤቷ ጋር ያላት ግንኙነት ከምንጊዜውም በላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን እና ሁለቱ አገራት በዓለም መድረክ ላይ እየተባበሩ መሆናቸውን ፑቲን ተናግረዋል።

"ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ [የሩሲያ-ቻይና] ግንኙነት ደረጃ እና ጥራት በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ደረጃ ላይ ደርሷል" ብለዋል።

ረዥሙን የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ጊዜ የተቆጣጠረው የዩክሬን ጦርነት ሲሆን ፑቲን ጦርነቱን ለማስቆም "ለመስማማት ክፍት ነን" ብለዋል። እንደዚህ አይነት ስምምነት ምን ሊያስከትል እንደሚችል ግን ግልጽ አይደለም።

የሩሲያ ኃይሎች በጦርነት ግንባር ላይ "በየቀኑ" ድል እያስመዘገቡ ነው ሲሉ ወታደሮቻቸውን "ጀግኖች" ሲሉ ገልጸዋል።

በአንድ አጋጣሚ በኩርስክ ክልል ውስጥ "ለእናት ሀገር" የሚዋጉ የሩስያ የባህር ኃይል አባላት ፊርማቸው ያረፈበት እና ሰጥተውኛል ያሉትን ባንዲራ በማቅረብ ሁለት ታዳሚዎች ለካሜራዎች እንዲያሳዩ አድርገዋል።

ከዩክሬን በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ላይ ስለሚገነቧቸው ፕሮጀክቶችም አስተያየት ሰጥተዋል። እአአ በ 2014 በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በዋለችው በዩክሬኗ ሉሃንስክ ክልል ውስጥ ያለው የመንገድ ደረጃ በጣም ተሻሽሏል ብለዋል።

ፑቲን በህዳር ወር ይፋ ያደረጉትን የሩስያ የኒውክሌር ዶክትሪን ለውጥ በተመለከተ ምዕራባውያን "መልዕክቱን አግኝተውት" እንደሆነ ከአንድ ታዳሚ ሲጠየቁ "እነሱን ጠይቁ" ሲሉ መልሰዋል።

አዲሱ የኒውክሌር ዶክትሪን በኒውክሌር ኃይል የምትደገፍ የትኛውም አገር ላይ ሩስያ የኒውክሌር ጥቃት እንድትፈጽም ይፈቅዳል።

ይህም ማለት ዩክሬን በሩስያ ላይ በሚሳኤል፣ በሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም በአውሮፕላኖች ላይ ትልቅ ጥቃት ብትሰነዝር ለኒውክሌር ምላሽ መስፈርቱን ሊያሟላ ይችላል። ይህ ተመሳሳይ ከለላ ለቤላሩስ የሚሰጥ እና በሩሲያ ሉዓላዊነት ላይ ለሚቃጣ ማንኛውም ወሳኝ አደጋ ምላሽ የሚሰጥ ነው።

ፑቲን በህዳር ወር በዩክሬን ላይ ጥቅም ላይ በዋለው አዲሱ የሩሲያ መካከለኛ ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤል ኦሬሽኒክ ያለውን አቅም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኃይሉን ለመፈተሽም ኦሬሽኒክን ወደ ዩክሬን መተኮስ እና የዩክሬን አየር መከላከያ (በአሜሪካ የሚቀርቡ ስርዓቶችን በመጠቀም ጭምር) ለማክሸፍ መሞከር ነው ሲሉ ሐሳብ አቅርበዋል።

ስለ "ኦሬሽኒክ" ስያሜ ሲመልሱ ደግሞ ፑቲን በፈገግታ ተሞልተው " ስለእውነት ምንም ሃሳብ የለኝም፥ ምንም ፍንጭ የለኝም" ብለዋል።

ኢኮኖሚው "የተረጋጋ ነው" ያሉ ሲሆን እንደ ጀርመን ካሉ አገራት ከፍ ያለ ዕድገት ቢያሳይም ግን 9.1 በመቶ የደረሰው የዋጋ ግሽበት "አስፈሪ ነው" ሲሉ አክለዋል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ኢኮኖሚው በጣም ሞቅ ያለ እና በወታደራዊ ምርት ላይ በጣም ጥገኛ ነው አንዳንድ ጊዜም "ወታደራዊ ኢንዱስትሪ" ተብሎ ይጠራል።

ፑቲንከስልክ አጭበርባሪዎች እስከ ወጣቶች ብድር ለማግኘት እስከሚገጥማቸው ችግሮች ያሉ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ ጭምር መልስ ሰጥተዋል።