ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ አንዲት ታዳጊን ያገተው ግለሰብ ገንዘብ ለመጠየቅ በላከው የማስታወሻ ወረቀት አማካይነት ተያዘ
አሜሪካ ውስጥ ገንዘብ ለማግኘት ታግታ የነበረችው ታዳጊ አጋቿ ለቤተሰቦቿ በላካው የገንዘብ መጠየቂያ ማስታወሻ ወረቀት አማካይነት ተይዞ ነጻ ወጣች።
የዘጠኝ ዓመቷ ታዳጊ ሻርለት ሴና ኒው ዮርክ ውስጥ ባለፈው ቅዳሜ ብስክሌቷን እየነዳች ሳለ በመሰወሯ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት ፍለጋ ለሁለት ቀናት ተደርጓል።
በኋላ ላይ ታዳጊዋን ያገተው ግለሰብ ልጅቷን ለመልቀቅ የሚያስፈልገውን ክፍያ የጠየቀበት የማስታወሻ ወረቀት ለቤተሰቦቿ ላከ። ፖሊስም ይህንን ወረቀት መሠረት አድርጎ ባካሄደው ምርመራ የተጠርጣሪውን የጣት አሻራ ለማግኘት ችሏል።
ፖሊስም የገኘውን አሻራ በመረጃ ቋቱ ውስጥ ካሉት አሻራዎች ጋር በሚያመሳክርበት ጊዜ ከ20 ዓመታት በፊት አልኮል ጠጥቶ በማሽከርከር ከተከሰሰ ግለሰብ ጋር አንድ አይነት ሆኖ አግኝቶታል።
ይህንንም ተከትሎ ባደረገው ክትትል ግልሰቡን በእናቱ ቤት ውስጥ ተደብቆ አግኝቶ በቁጥጥር ስር ለማዋል ችሏል።
የኒው ዮርክ አገረ ገዢ ኬቲ ሆቹል ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ተጠርጣሪው ላለመያዝ የተወሰነ ማንገራገር ቢያሳይም፣ በቁጥጥር ስር ውሎ እስር ቤት ገብቷል። ታዳጊዋንም በአንድ ቁምሳጥን ውስጥ ደብቋት ተገኝታለች” ብለዋል።
በታዳጊዋ ላይ እገታውን በመፈጸም የተጠረጠረው ክሬግ ኔልሰን ሮስ የተባለ የ47 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን፣ ለተጠረጠረበት ወንጀል የሚደረገው ምርመራ እንደቀጠለ ፖሊስ ገልጿል።
ታዳወጊዋ ሻርለት በብስክሌቷ ላይ ሆና ስትንሸራሸር ታግታ በተሰወረችበት ጊዜ ወላጆቿ በቤታቸው ውስጥ አልነበሩም።
ተጠርጣሪው ታዳጊዋን ካገተ ከሁለት ቀን በኋላ ገንዘብ የጠየቀበትን ማስታወሻ ወረቀት በወላጆቿ ቤት የፖስታ መልዕክት ማስቀመጫ ሳጥን በኩል እንዲደርሳቸው አድርጎ ነበር።
የጠፋችውን ታዳጊ ለማግኘት ምርመራ በማድረግ ላይ የነበረው ፖሊስ የማስታወሻ ወረቀቱን አግኝቶ፣ ባደረገው ማጣራት ነው የተጠርጣሪውን የጣት አሻራ በወረቀቱ ላይ ማግኘት የቻለው።
ታግታ የነበረችው ታዳጊ “ምንም ጉዳት ያልደረሰባት እና በመልካም ጤንነት ላይ ብትገኝም” ለጥንቃቄ ሲባል ነጻ ከወጣች በኋላ ወደ ሆስፒታል መወሰዷ ተነግሯል።
ታዳጊዋ ከተሰወረች በኋላ ኤፍቢአይ፣ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች የተካተቱበት 400 ያህል የፍለጋ እና የነፍስ አድን ሠራተኞች በፍለጋው ላይ መሳታፋቸውን ፖሊስ ገልጿል።
ጠፍታ የነበረችውን ሻርለት ለማግኘት ፍለጋው ከተሰወረችበት ስፍራ አስከ 80 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ርቀት ውስጥ ሲደረግ የነበረ ሲሆን፣ በአካባቢው የፍተሻ ኬላዎች በማቋቋም በአንዳንድ ተሽከርካሪዎች ላይ ፍተሻ ሲደረግ ነበር።