ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ምክር ቤት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ አፈ ጉባኤውን ከኃላፊነት አነሳ
የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ አፈ ጉባኤውን የመተማመኛ ድምጽ በመንፈግ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ አደረገ።
የአፈ ጉባኤነት መንበሩን ከተረከቡ አንድ ዓመት ያልሞላቸው የካሊፎርኒያ ተወካይ የምክር ቤት አባል ኬቭን ማካርቲ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ምክር ቤቱ የወሰነው 216 ለ 210 በሆነ የድምጽ ብልጫ ነው።
ሪፐብሊካኑ አፈ ጉባኤ ማካርቲ እንዲነሱ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲዘጉ ሊያደርግ የነበረውን የበጀት ጉዳይ ለማስተካከል ከዲሞክራቶች ጋር ስምምነት በመድረሳቸው ነው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አጋር የሆኑት የፍሎሪዳው እንደራሴ ማት ጊትዝ ናቸው አፈጉባኤው እንዲነሱ ያደረገውን የምክር ቤቱን የአሰራር ሂደት ሰኞ ዕለት እንዲጀመር ያስደረጉት።
አፈ ጉባኤው የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት በከፊል እንዲዘጉ ሊያደርግ የሚችለውን የበጀት እክል ለማስቀረት ድርድር በሚደረግበት ጊዜ በምስጢር ከዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት ጋር ለዩክሬን የሚደረገው ድጋፍ እንዲቀጥል ተስማምተዋል በሚል ነው የተከሰሱት። ኬቭን ማካርቲ ግን ይህንን ያስተባብላሉ።
ማካርቲ ክሱን ያቀረቡባቸው ተቀናቃኛቸውን ማት ጊትዝን “ትኩረትን የሚሻ” ሲሉ ውረፏቸው ሲሆን፣ ክሱ በእሳቸው ላይ ያነጣጠረ ግለሰባዊ እንጂ “ከመንግሥት ውጪ ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም” ብለዋል።
ኬቭን ማካርቲ በአሜሪካ መንግሥት ውስጥ ከፕሬዝዳንቱ እና ከምክትላቸው ቀጥሎ ትልቁ ሥልጣን የሆነውን የምክር ቤት አፈ ጉባኤነት ቦታ የያዙት ከተደጋጋሚ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በኋላ ባለፈው ዓመት ጥር ላይ ነበር።
የአፈ ጉባኤውን ከሥልጣን መነሳት ተከትሎ ከዋይት ሐውስ የወጣው መግለጫ እንዳለው፣ “አገራችን የገጠሟት ተግዳሮቶች ጊዜ የሚሰጣቸው ባለመሆናቸው” ምክር ቤቱ በአስቸኳይ አዲስ አፈ ጉባኤ ይመርጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናግረዋል።
ማካርቲን ከመንበራቸው ያስነሳቸው የምክር ቤቱ የአሰራር ደንብ ባለፉት ዘመናት በአፈጉባኤ ላይ ተግባራዊ የተደረገው ለሁለት ጊዜ ሲሆን፣ ነገርግን አፈ ጉባኤዎቹን ለማንሳት በቂ ድጋፍ ባለማግኘታቸው የተሳኩ አልነበረም።
አሁን ግን በአሜሪካ የአፈ ጉባኤነት መንበር ላይ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ የቆዩትን ኬቭን ማካርቲን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማስነሳት አስችሏል።
ተሰናባቹን አፈ ጉባኤን በመተካት ምክር ቤቱን ማን ሊመራ ይችላል የሚለውን በተመለከተ ግልጽ የሆነ ወይም ተገማች ዕጩ አስካሁን አልታወቀም።