የዩክሬን ሚኒስትርን ጨምሮ 18 ሰዎች በሄሊኮፕተር አደጋ ሕይወታቸው አለፈ

የዩክሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ አስራ ስምንት ሰዎች በዋና ከተማዋ ኬዬቭ ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ በተከሰከሰ የሄሊኮፕተር አደጋ ሕይወታቸው አለፈ።
ሄሊኮፕተሩ በከተማዋ ዳርቻ ላይ ከሚገኝ አንድ የመዋዕለ ህጻናት ጎን የተከሰከሰ ሲሆን፣ በአደጋው ሦስት ህጻናት ሲሞቱ ሌሎች 15 በሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ነው።
የዩክሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኒስ ሞናስታይርስካይ አደጋው በደረሰበት ሄሊኮፕተር ውስጥ ከሌሎች ስምንት ሰዎች ጋር እየተጓዙ ነበር።
ብሮቫሪ በተባለው የዋና ከተማዋ ክፍል ላይ በደረሰው በዚህ አደጋ ከሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትላቸው እና የመንግሥት ዋና ጸሐፊ መሞታቸውን ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።
የአገሪቱ ብሔራዊ ፖሊስ ኃላፊ ኢሆር ክላይሜንኮ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት አደጋው የደረሰበት ሄሊኮፕተር የአገሪቱ መንግሥት የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ንበረት ነበረ።
ሄሊኮፕተሩ ወድቆ ከተከሰከሰ በኋላ ከመዋዕለ ህጻናቱ አቅራቢያ እሳት በመነሳቱ ህጻናት እና ሠራተኞች ከህንጻው እንዲወጡ ተደርጓል።
የሄሊኮፕተሩ ስብርባሪ በመንደድ ላይ ካለው ህንጻ ውጪ እንደሚታይ የዐይን እማኞች ተናግረዋል።
አደጋው በደረሰበት ጊዜ አካባቢው ጨለማ እና ጭጋጋማ የነበረ ሲሆን፣ በቀዳሚነት የወጡ ሪፖርቶች ሄሊኮፕተሩ ከመዋዕለ ህጻናቱ ጋር ተጋጭቶ ከአንድ የመኖሪያ ህንጻ አቅራቢያ ነው የወደቀው።
ከአደጋው ጋር በተያያዘ በርካታ ህጻናትን ጨምሮ ሃያ ሁለት ሰዎች ለህክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የአገሪቱ የፖሊስ ኃላፊ አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ ሞናስታይርስካይ ለረጅም ጊዜ የፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የፖለቲካ አማካሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ከሩሲያ ጋር የሚደረገው ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በአደጋ የሞቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ናቸው።
ሚኒስትሩ አደጋው በገጠማቸው ጊዜ ከፍተኛ ጦርነት ወደ ሚደረግበት ሥፍራ እየተጓዙ እንደነበር የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ተናግረዋል።
በዩክሬን ሰሜን ምሥራቅ ውስጥ የምትገኘው የኻርኪቭ ከተማ የፖሊስ ኃላፊ ቮሎድሚር ታይሞሼንኮ እንደተናገሩት፣ በሚኒስትሩ የሚመራው ቡድን እሳቸውን ለማግኘት እየተጓዙ እንደነበረ እና ማክሰኞ ዕለት ተነጋግረው እንደነበር ገልጸዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ በተለይ በጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ዩክሬን ወሳኝ ሚና ያለው ኃላፊነት ሲሆን፣ ሚኒስትሩ ወሳኝ የሆነውን የአገሪቱን ደኅንንት መጠበቅ እና የፖሊስ ሥራን መምራት ዋነኛ ሥራቸው ነበር።
የሚኒስትሩን ሞት የሰሙት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ አደጋው የአገራቸውን “እውነተኛ አርበኞችን” ሕይወት ቀጥፏል ሲሉ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
ዩክሬናውያን ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን ጨምሮ ከ15 በላይ ሰዎችን ሕይወት ለቀጠፈው አደጋ ሩሲያ በአገራቸው ላይ የምታካሂደውን ጦርነት ተጠያቂ አድርገዋል።
ቁልፍ የዩክሬን ባለሥልጣናት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ለደኅንነታቸው ሲባል ሄሊኮፕተሮቻቸው ዝቅ ባለ ከፍታ እንዲጓዙ የሚደረግ ሲሆን ይህም አደጋ አለው።












