ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቆሻሻ ዙሪያዋን የከበባት የዓለማችን ባለግዙፍ ምጣኔ ኃብት አገራት ጉባዔን የምታስተናግደው ጆሃንስበርግ
ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የዓለማችን ታላላቅ ኢኮኖሚ መሪዎች የደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ እምብርት በሆነችው ጆሃንስበርግ ለቡድን 20 አገራት የመሪዎች ጉባኤ ይሰባሰባሉ።
ነገር ግን ንፁህ ከሆነው እና ደህንነቱ እጅግ ከተጠበቀው መንገድ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የአገሪቱ ባለሥልጣናቱ ለማሻሻል እና ደህንነቱን ለመጠበቅ እየታገሉ ያሉት የከተማው ማዕከል ይገኛል።
ከ100 በላይ የቆሸሹ ሕንፃዎችን በማጽዳት ረገድ ትልቅ ፈተና ያጋጥማቸዋል። ብዙዎቹ በቆሻሻና ክፍት በሆኑ ፍሳሽ ማስወገጃዎች፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የወንጀለኛ ቡድኖች መኖሪያ ሆነዋል።
በጆውበርት ፓርክ ውስጥ የሚገኘው ኤምቢቪ1 ተብሎ የሚጠራው ሕንፃ ነዋሪ ኔልሰን ኬታኒ "ሽጉጥ አለ፤ ዕፅ አለ፣ ሴተኛ አዳሪዎች አሉ፣ እዚህ ሁሉም ነገር አለ" ይላል።
በቸልተኝነት የተተዉ እና በጥገና እጦት የተበላሹ የጋራ ማብሰያ ክፍሎች እቃዎቻቸው ተዘርፈዋል። ሞልቶ የሚፈስሰው የሽንት ቤት ቆሻሻ ደግሞ የልብስ ማጠቢያ ቦታ የነበረውን ክፍል ሸፍኗል።
ኬታኒ ለቢቢሲ አፍሪካ አይ እንደተናገረው በኤምቢቪ1 ውስጥ ያሉ ክፍሎች በተለያዩ ግለሰቦች የተያዙ ናቸው። የተወሰኑ ቦታዎች ወይም ሙሉ መኖሪያ ቤቶች በወንጀለኞች ተወስደዋል።
እነዚህ የወንጀል ቡድኖች ለራሳቸው ኪራይ ለመሰብሰብ እና በአንዳንድ ሁኔታዎች ለሕገ-ወጥ ተግባራት ጥቅም ላይ ያውሉታል።
ቢቢሲ በከተማዋ ውስጥ 102 የተዘረፉ ወይም የተተዉ ሕንፃዎች መኖራቸውን አረጋግጧል። እነዚህ ቤቶች 18 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ሲሆን ሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ግን ከዚህ ከፍ ያለ አሃዞችን ያስቀምጣሉ።
ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በኃይል የተወሰዱ ቤቶች ለሰው መኖሪያነት ብቁ ያልሆኑ ናቸው።
ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ለከተማው ምክር ቤት ስለ ቡድን 20 አገራት ጉባዔ ሲናገሩ ይህ የከተማዋ ሁኔታ በአእምሯቸው ውስጥ ነበር።
"ከተማዋ ቆሻሻ ሆኖ ነው ያገኘኋት" ነበር ያሉት።
"በመሃል ከተማው ውስጥ ማለፍ በጣም የሚያሳዝን ዕይታ ይፈጥራል...የተተዉ ሕንፃዎች፣ በጉልበት የተወሰዱ ሕንፃዎች፣ ኪራይ እና ግብሮችን የማይከፍሉ ሕንፃዎች አሏችሁ።"
የጆሃንስበርግ ከንቲባ ዳዳ ሞሬሮ በወቅቱ ከተማዋ "የቡድን 20 ጉባዔን ለማስተናገድ ዝግጁ ናት" ነበር ያሉት።
ባለፈው ወር፣ በመላ ጆሃንስበርግ በተካሄደው የ"ጽዳት" ዘመቻ የከተማው ምክር ቤት በከተማዋ ውስጥ "የተስፋፋው ሕግ አልባነት፣ ሕገ-ወጥ ተግባራት፣ በጉልበት የተወሰዱ ንብረቶች እና ወሳኝ የመተዳደሪያ ደንቦችን መጣስን ለማስወገድ ዓላማ ያደረገ ነው" ብሏል።
ነገር ግን ከዓለም አቀፉ ጉባዔ በፊት ያሉት ተግዳሮቶች ግዙፍ ናቸው።
ከሁለት ዓመት በፊት 76 ሰዎችን የገደለው ከነዚህ ከፈራረሱ ሕንፃዎች በአንዱ ላይ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ሰዎችን ወደ ተግባር ያነሳሳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ግን ብዙም የተለወጠ አይመስልም።
ቢቢሲ ሌላ የከተማዋ ሕንጻ ማለትም ቫኒን ኮርትን ጎብኝቷል። ክፍሎቹ በቆሻሻ የተሞሉ፣ በሕንፃው ውስጥ የሰው ዓይነምድር ሽታ ገንኖ ይሰማል።
በሕንጻው ላይ የሚኖረው ሲንቴምባ ማኮማ የከተማዋ ምክር ቤት ንብረት የሆነው ቫኒን ኮርት በጉልበት እንደተወሰደ እና የከተማው አስተዳደር ውሃውን ማቋረጡን ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ማዘጋጃ ቤቱ በዚህ ሕንፃ ውስጥ በተፈፀመ ወንጀል ተቆጥቷል...ለዚህም ነው ውሃውን የቆረጡት" ሲል ሌላው ነዋሪ ሲንቂሂዌ ጉድማን ሲትሆሌ ተናግሯል።
የጆሃንስበርግ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስለ ቫኒን ኮርት የውሃ አቅርቦት በተመለከተ ቢቢሲ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
በተጨማሪም የኤሌክትሪክ አቅርቦት የለም ያለው ማኮማ ብርሃን ለማግኘት ጋዝ እና የፀሐይ ብርሃን እንደሚጠቀሙ ተናግሯል።
የፍጆታ ዕቃዎች እጥረት ማለት ነዋሪዎች ምግቦቻቸውን ለማብሰል ተንቀሳቃሽ ጋዝ ይጠቀማሉ።
ነገር ግን በአቅራቢያቸው ውሃ ወይም የእሳት ማጥፊያ ከሌለ ለእሳት አደጋዎች በጣም የተጋለጡ ናቸው።
በሕንፃው ምድር ቤት ውስጥ የቆሙ መኪኖች ከፊሉ አካላቸው ከሽንት ቤት በሚወጣ ፍሳሽ ውስጥ ተውጦ ወደ አጎራባች ጎዳና እየፈሰሰ ነው። ቆሻሻ በዚህ ቀስ ብሎ በሚወርድ የፍሳሽ ቆሻሻ ላይ ሲንሳፈፍ ይታያል።
ማቆማ ለቢቢሲ አንድ ባልዲ ውሃ እንዳፈሰሰበት የሚናገረውን ጨለማ መጸዳጃ ቤት እና ንጽህና የጎደለው የመታጠቢያ ክፍል አሳይቷል።
"ወደ [መጸዳጃ ቤቱ] ውስጥ ውሃ ስትለቅ ወደ ምድር ቤት ያሄዳል" ብሏል።
የከተማዋ የመኖሪያ ቤት ችግር የቅርብ ጊዜ ክስተት አይደለም።
እአአ በ1994 የአፓርታይድ እና የነጭ ድሃጣን አገዛዝ ሲያበቃ፣ ብዙ ጥቁሮች እና ከነጭ የሚወለዱ ደቡብ አፍሪካውያን ለሥራ ቦታቸው ቅርብ ለመሆን ከከተማዋ ውጭ ካሉ አካባቢዎች ወደ መሃሉ በመምጣት መኖር ጀመሩ።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ፍልሰት በቂ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።
በርካታ ባለጸጎች አከራዮች ለቅቀው በመሄዳቸው እና በዘርፉ ላይ የሚፈስሰው መዋዕለ ነዋይ አነስተኛ መሆን ጋር ተያይዞ ብዙ ሕንፃዎች እንዲተዉ አድርጓቸዋል።
አንዳንዶች ደግሞ እንደ ጠለፋ ላሉ ሕገወጥ ተግባራት መሸሸጊያ ሆኑ።
ለደህንነቱ በሚል ስሙ የተቀየረው ዮሴፍ ከዚህ በፊት ሰዎችን በማገት ኑሮውን ይገፋ ነበር። በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ወንጀለኞች ሕንፃውን "በማጽዳት"፤ " ይከራያል የሚል ማስታወቂያ ለጥፍ" ብለው እንዳዘዙት ያስታውሳል።
ነገር ግን የቤት ኪራይ መሰብሰብ ዋናው ሥራው አልነበረም።
"የሕንፃው ዋና ሥራ አደንዛዥ ዕጾችን መቀመሚያ ማድረግ ነው" ብሏል። "ብዙ ሕንጻዎች እዚህ ጆበርግ ውስጥ በጉልበት ተይዘው ኒያኦፔን በጥንቃቄ ይዘጋጅባቸዋል።"
ኒያኦፔ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በጣም ሱስ የሚያስይዝ በየጎዳናው ላይ የሚሸጥ አደንዛዥ ዕፅ ነው።
ብዙ ጊዜ ዝቅተኛ መጠን ያለው ሄሮይን፣ ካናቢስ፣ ፀረ ኤችአይቪ መድሀኒቶች እና አንዳንድ ጊዜ የአይጥ መርዝ ይጨመርበታል። የሆድ ሕመም፣ የመተንፈስ ችግር እና የመንፈስ ጭንቀት ሊያስከትል ይችላል።
ጆሴፍ በሚሠራበት ቦታ በተፈጠረው ነገር ምክንያት ሊሰቃዩ በሚችሉ ሰዎች ሐሳብ ይጨነቅ እንደነበር ይናገራል።
"አንዳንድ ጊዜ ስተኛ ሰዎችን አያለሁ። ሰዎች ይታዩኛል፤ በእነዚህ ሕንፃዎች ውስጥ ሰዎች ሞተዋል፤ ሰዎች ጠፍተዋል፤ በሕይወቴ ስለሄድኩበት የተሳሳተ ጎዳና አዝናለሁ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ጆሴፍ ከወንበዴ ቡድኑ የወጣው ሌሎች ቡድኖች እርሱን ለመግደል እያሴሩ እንደሆነ ስላወቀ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ዛሬ የወንጀል ሕይወቱን በመተው እፎይታ እንደተሰማው ይናገራል።
ነገር ግን በጉልበት የተወሰዱት ሕንጻዎችን ባለሥልጣናት ማስመለስ ያልቻሉት ለምን እንደሆነ ፍንጭ ይሰጣል፤ ሙስና።
ጆሴፍ ሕንጻውን በሕገወጥ መንገድ የያዙት እንዲለቁ ማድረግ የቆመው "ከከተማው ማዘጋጃ ቤት እና ከፖሊስ ጋር ጥሩ ግንኙነት በመኖሩ ነው" ይህም "የገንዘብ ጉዳይ" ጉቦ እንደሆነ ተናግሯል።
የጆሃንስበርግ ከተማ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ንታቲሲ ሞዲንጎኔ ሕንጻዎቹን በጉልበት ከሚቆጣጠሩ ጋር ስላለው ግንኙነት የቀረበውን ውንጀላ በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ምክር ቤቱ "ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳለ" የሚጠቁሙ "የሰው" ወይም "የሰነድ መረጃ" የሉትም ብለዋል።
በጉልበት በተያዙ ሕጻዎች ውስጥ የወንጀል ድርጊቶችን መዋጋትን በተመለከተ ቃል አቀባዩ ሲናገሩ "አደንዛዥ ዕፅ የያዙ ... [እና] ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ያገኘንባቸው አጋጣሚዎች አሉ፤ እነዚያ ጉዳዮች በአሁኑ ጊዜ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ዘንድ ለተጨማሪ ምርመራ ተቀምጠዋል" ብለዋል።
ሞዲንጎኔ አክለውም ምክር ቤቱ በኃይል በተወሰዱ ሕንፃዎች ውስጥ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን የመዋጋት ሥራውን "አጠናክረን እንቀጥላለን" እና "ከተማዋን ማጽዳታችንን እናረጋግጣለን" ብለዋል።
የጆሃንስበርግ ፖሊስ ቢቢሲ ጉቦ እና ማስፈራራት ላይ ስለቀረበው ውንጀላ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
በእነዚህ በተተዉ እና በኃይል በተወሰዱ ሕንፃዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን ማስወጣት ለችግሩ ቀላል መልስ ይመስላል።
ያ ደግሞ እጅጉን አስፈላጊ ወደሆነው መልሶ ማልማት ያመራል። ነገር ግን በጣም ከባድ የሆነ ተግባር እና በሕግም ረገድ ፈታኝ ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት ሰዎችን የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብታቸውን ከለላ ይሰጣል።
ይህ ማለት አንድ ሰው በሕንፃ ውስጥ መኖር ከጀመረ እና ሌላ የሚሄድበት ቦታ እንደሌለው ካረጋገጠ፣ መንግሥት አማራጭ መጠለያ እስካልሰጠው ድረስ ሊወጣ አይችልም።
ይህ በአካባቢው አስተዳደር ላይ ተጨማሪ ወጪን ያስከትላል። እና ሰዎችን ከሕንፃው ማስወጣት ውድ ነው።
የከተማዋ ማዕከል የሚመለከተው የጆሃንስበርግ ማዕከላዊ ፖሊስ፣ በገንዘብ ችግር ምክንያት ነዋሪዎችን በአንድ ጊዜ ጠራርጎ ማስወጣት ወይም ቶሎ ቶሎ ማባረር እንደማይችል ተናግሯል።
የፖሊስ ባልደረባ የሆኑት ማርክ ማንጋባ ሚናቸው የፍርድ ቤት መመሪያዎችን መፈጸም ሲሆን ይህም አንድ የንብረት ባለቤት የማስልቀቂያ ትዕዛዝ ካመጣ ነዋሪዎቹን ከሕንፃዎቹ ማስወጣትን ያካትታል።
አከራዮች መንግሥትም ይሁን ግለሰብ፣ የፍርድ ቤት ማዘዣ ሲያመጡ ግለሰቡን ለማስወጣት መክፈል አለባቸው። ነገር ግን ማንጋባ መጠነ ሰፊ ማፈናቀል "በጣም ውድ የሆነ እንቅስቃሴ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስወጣ ነው" ብለዋል።
ነገር ግን የጆሃንስበርግ ከተማ ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ማፈናቀል ቢችል እንኳን ከፍተኛ የቤት እጦት ቀውስ ይፈጥራል እናም የከተማው ምክር ቤት ማረፊያ ለማዘጋጀት ይገደዳል።
በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ ሕግ መሠረት ከቤት ማስወጣት ለመከላከል የጸደቀው ሕግ እያንዳንዱን ሰው ከቤት ለማስወጣት ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማምጣት ይጠይቃል።
ይህም ሰዎችን ለማስወጣት የሚደረጉ ሙከራዎች በሕግ ስርዓቱ ውስጥ እገዳ ሊገጥማቸው ይችላል።
በመጋቢት ወር ላይ ፕሬዝዳንቱ የጆሃንስበርግ በጉልበት የተወሰዱ ሕንፃዎች "ሕዝባችን በክብር ወደ ሚኖርባቸው መኖሪያ ሕንጻነት መቀየር" አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል ።
ነገር ግን እዚህ ለሚኖሩ በርካታ ነዋሪዎች ያ ሩቅ ነው።
በኤምቢቪ1 ሕንፃ የሚኖረው ኬታኒ ምንም እንኳን ጊዜያዊ መጠለያው መሆን የነበረበት ቢሆንም እአአ ከ2008 ጀምሮ በቋሚነት እየኖረ እንደሆነ ተናግሯል።
የከተማው ምክር ቤት "እኛን ለማስገባት የሚሆን" ምንም ቋሚ ማረፊያ እንደሌለ ነግረውናል ይላል።
"ከተማዋ ገንዘብ የላትም እና ማንም ግድ አይሰጠውም።"