ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወርቅ እና ወሲብ - በደቡብ አፍሪካ ማዕድን ማውጫዎች በታዳጊዎች ላይ የሚፈጸም አሰቃቂ ብዝበዛ
ይህ ታሪክ አንዳንድ ሰዎች የሚረብሽ ይዘቶች አሉት።
በደቡብ አፍሪካ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ስፍራ ስድስት አስጨናቂ ወራትን ላሳለፈው ጆናታን በጣም የሚያስደነግጠው ነገር በልጆች ላይ ሲደርስ የተመለከተው በደል ነው።
አንዳንዶቹ ለርካሽ የጉልበት ሥራ የሚቀጠሩ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ለወሲብ ተብሎ የሚመጡ ናቸው ይላሉ ተግባሩን የሚቃወሙ አንቂዎች።
አሁን ዕድሜው በ20ዎቹ መገባደጃ ላይ የሚገኘው ጆናታን ወደ ደቡብ አፍሪካ የተሰደደው በማዕድን ማውጫዎች በመሥራት በቀላሉ ገንዘብ እንደሚያገኝ ተነግሮት ነው።
ማዕድን ማውጫዎቹ ትላልቅ ኩባንያዎች ተጠቅመውባቸው የተተዉ በደርዘን የሚቆጠሩ ጉድጓዶች ናቸው።
ለመገናኛ ብዙኃን በመናገሩ ምክንያት ሕገወጥ የማዕድን ኢንዱስትሪውን ከሚመሩ ወንጀለኛ ቡድኖች የሚደርስበትን ጥቃት በመፍራት ሙሉ ስሙን ከመጠቀም ተቆጥበናል።
በተረጋጋ ድምፅ ሰውነቱን የጎዳው ሙቀት፣ ረጅም የሥራ ሰዓት እና ውስን የምግብ እና የመኝታ ሰዓት እንዳለ ይገልጻል።
ከሁሉም የሚከፋው ግን በሚሠራበት ጉድጓድ ውስጥ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ የማዕድን ቆፋሪዎች ላይ የሚደረሰው ጥቃት ነው።
"ልጆች በማዕድን ማውጫው ውስጥ አያቸው ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው። የ15፣ የ17 ዓመት ልጆች ናቸው።"
"አንዳንድ ጊዜ ሌሎች እነሱን ይጠቀሙባቸው ነበር። ትንሽ የሚያስፈራ ነበር። እኔንም አልተመቸኝም።"
ለወሲብ ሲሉ ካገኙት ወርቅ የተወሰነውን እንደሚሰጣቸው ቃል በሚገቡ ጎልማሶች መደፈራቸውን ተናግሯል።
"ያ ልጅ ገንዘብ ለማግኘት በጣም የሚፈልግ ከሆነ ለመፈጸም ይገደዳል።"
ልጆቹ ጥበቃ ለማግኘት ወደ ማዕድን አውጪዎች ቡድን እንዴት እንደሚቀርቡ ጆናታን ገልጿል። ይህ ቡድን ግን ቅድመ ሁኔታ አለው።
ታዳጊዎቹ ለቡድናቸው የተሰጣቸውን ተግባር ማከናወን ካልቻሉ ወሲብ እንደ ቅጣት ይወሰድ ነበር።
በማዕድን ማውጫው ውስጥ ያሉት ሕጻናት በሙሉ ከሌላ አገር የመጡ በመሆናቸው ወደ ምን እየገቡ እንደሆነ እንኳን አያውቁም ብሏል ጆናታን።
የማዕድን ተመራማሪ እና የኅብረተሰብ አንቂው ማክሆትላ ሰፉሊ ይህንን ሃሳብ ይደግፋል።
ወንጀለኛ ቡድኖች በደቡብ አፍሪካ በሕገወጥ ማዕድን ማውጫ ውስጥ የሚሠሩ ሕጻናትን በተለይ ዒላማ ያደርጋሉ ብሏል።
ብዙዎቹ ከጎረቤት አገራት ታፍነው በሕገወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ ናቸው። በመደበኛው የማዕድን ኢንዱስትሪ ውስጥ ሥራ እንደሚያገኙ የማይጨበጥ ተስፋ ይሰጣቸዋል።
ሰፉሊ እንደሚለው ከሆነ "ደቡብ አፍሪካ ሲደርሱ ፓስፖርታቸው ይነጠቃል…እነዚህ ታዳጊ ወንዶች በደል እንደሚደርስባቸው የታወቀ ነው።"
ቢቢሲ ቢያንስ በሁለት ሌሎች ሕገወጥ የማዕድን ማውጫዎች ይሠሩ የነበሩ ማዕድን አውጪዎችን አነጋግሯል። በሚሠሩበት ጉድጓዶች ታዳጊዎች ጥቃት ሲደርስባቸው ማየታቸውን ተናግረዋል።
ጼፖ (ስሙ ተቀይሯል) አዋቂ ወንዶች ታዳጊ ወንዶችን በድብቅ ወሲብ እንዲፈጽሙ ሲያስገድዷቸው መመልከቱን ተናግሯል።
"በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለገንዘብ ሲሉ ይፈጽማሉ። አንዳንዶቹ የሚቀጠሩት ለዚሁ ዓላማ ብቻ ነው። ምክንያቱም በማዕድን ማውጫዎቹ ውስጥ ከወሲብ ንግድ ልማድ ጋር በሚመጣ ገንዘብ ሊሆን ይችላል።"
በታዳጊዎቹ ላይ የደረሰው በደል በእጅጉ እንደጎዳቸው አክሏል።
"ባህሪያቸው ይለወጣል። የመተማመን ችግር አለባቸው። ማንንም እንዳያምኑ ስለሚሆኑ ወደ እነርሱ እንድትቀርብ አይፈልጉም።"
በደቡብ አፍሪካ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በፖሊስ እና በሺህዎች በሚቆጠሩ ሕገወጥ ማዕድን አውጪዎች መካከል በተፈጠረው እሰጣ አገባ ወቅት ወጣቶቹ ላይ ምን እየተፈጸመ ያለው ዝርዝር መረጃ ወጣ።
በሰሜን ምዕራብ ግዛት በስቲልፎንቴን ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው በብሉምፎንቴን የወርቅ ማዕድን ማውጫ የተካሄዱ ዘመቻዎች በመላው ዓለም ርዕሰ ዜና ለመሆን በቃ።
ባለፈው ዓመት የደቡብ አፍሪካን ኢኮኖሚ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ያከሰረውን ሕገወጥ ማዕድን ለመግታት ባለሥልጣናት እየሞከሩ ነበር ።
በታኅሣሥ 2023 ቫላ ኡምጎዲ የሚባል ዘመቻ ጀመሩ። ጉድጓዱን አሽጉት እንደማለት ነው። በወንበዴዎቹ ላይ ጠንካራ እርምጃም እንደሚወስዱም ቃል ገቡ።
ዘመቻው በስቲልፎንቴይን ማዕድን ማውጫ የሚገባውን ምግብ እና ውሃ መጠን መገደብ ነው።
አንድ ሚኒስትር እንዳሉት ከሆነ በዚህ መንገድ አስገድዶ ሕገወጥ ማዕድን አውጪዎችን "ለማስወጣት" ነው። ግለሰቦቹ እንዳይታሰሩ በመፍራት ለመውጣት ፍቃደኛ አልነበሩም ብለዋል ባለሥልጣናቱ።
ብዙም ሳይቆይ ግን ከማዕድን ማውጫው አድኑን የሚሉ ተማጽኖዎች ተሰሙ። በርካታ አስከሬን መሸፈኛዎችም ተገኙ። በመጨረሻም የአገሪቱ ፍርድ ቤት ማዕድን አውጪዎቹን መንግሥት እንዲታደግ ለባለሥልጣናቱ ትዕዛዝ አስተላለፈ።
እንዲወጡ ከተደረጉት ውስጥ ብዙዎቹ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች በመሆናቸው ባለሥልጣናቱ ዕድሜያቸውን ለማወቅ የሕክምና ምርመራ አድርገዋል።
የደቡብ አፍሪካ ማኅበራዊ ልማት መሥሪያ ቤት (ዲኤስዲ) ከታደጋቸው የስቲልፎንቴይን ማዕድን አውጪዎች መካከል 31ዱ ሕጻናት መሆናቸው አረጋገጠ። ሁሉም የሞዛምቢክ ዜጎች ሲሆኑ በኅዳር ወር 27ቱ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደረጓል።
ሴቭ ዘ ችልድረን ደቡብ አፍሪካ ለአቅመ አዳም ባልደረሱ የማዕድን ቆፋሪዎች እና በነፍስ አድን ሠራተኞች መካከል የተደረጉትን አንዳንድ ቃለ ምልልሶች በመተርጎም ረድቷል።
የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጉጉ ዛባ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "አሰቃቂ ተጽዕኖ ፈጥሮባቸዋል። ምክንያቱም አንዳንዶቹ ሌሎች ላይ ወሲባዊ ብዝበዛ ሲፈጸሙ አይተዋል።"
"ላልወጣ እችላለሁ የሚለው ስሜት እነዚያን ልጆች አእምሮ ጎድቷል።"
"አዋቂዎቹ ማዕድን ቆፋሪዎች እነርሱን በመንከባከብ፣ እንደወደዷቸው በመምሰል ይጀምራሉ።"
በኋላም ይላሉ ጉጉ ዛባ በአዋቂዎች ላይ የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ መደረጉን እና ከዚያም ከቀን ወደ ቀን እንደሚደፈሩ ተናግረዋል።
"አዋቂዎቹ ተመሳሳይ ነገር የሚያደርጉባቸው ሦስት ወይም አራት ታዳጊዎች ይኖራቸዋል።"
ዛባ እንዳሉት ከሆነ የማዕድን ማውጫ ወንበዴዎቹ ሕጻናትን የሚመለምሉት ለመጠመድ ቀላል እና ርካሽ ስለሆኑ ነው።
"ልጆች በቀን አንድ ዶላር እከፍልሃለሁ ስትል አይረዱም። አዋቂዎች አንዳንድ ጊዜ ለመሥራት እምቢ ቢሉም ሕጻናት ግን ምንም አማራጭ የላቸውም። ስለዚህ ታዳጊዎችን ተጠቅመው ሥራውን መሥራት ቀላል ነው።"
በገንዘብ ከመበዝበዝ ባለፈ ልጆችን ለወሲብ የሚቀጥሩ ወንበዴዎች እንዳሉም ተናግረዋል።
ብዙ ሕገወጥ ማዕድን አውጪዎች ከመሬት በታች ወራትን ያሳልፋሉ። የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማቅረብ የሚሠሩ ንግዶች ከመሬት በታች ይጧጧፋሉ።
"አብዛኞቹ ሕጻናት ለወሲብ ባሪያነት እንዲውሉ ነው የሚዘዋወሩት። ገንዘቡን የሚወስድ ደላላ ስለሚኖር ይህ ልጅ በየቀኑ እንደ ወሲብ ነጋዴ ያገለግላል ማለት ነው።"
በፆታዊ ጥቃት የተከሰሰ ሰው ስለመኖሩ ቢቢሲ ፖሊስን እና ዲኤስዲን ጠይቋል። ሁለቱም ተቋማት ለጥያቄው ምላሽ አልሰጡም።
በስቲልፎንቴይን ማዕድን ቆፋሪዎች ጉዳይ ላይ የሚሠራ አንድ ምንጭ እንዳለው ደግሞ ብዙዎቹ ሕጻናት መመስከር አልፈለጉም።
ሕገወጥ የማዕድን ኢንዱስትሪው መስፋፋቱን ቀጥሏል።
በግምት ወደ 6 ሺህ የሚገመቱ ባዶ ጉድጓዶች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ ንግድ በቅርቡ ያበቃል ተብሎ የማይታሰብ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎችን ለአደጋ ያጋለጠ ነው።