ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኤኳዶር አንድ የአደገኛ ቦዘኔ ቡድን መሪ እስረኛን ለማዘዋወር በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ተሰማሩ
በኤኳዶር አንድ የአደገኛ ቡድን መሪ እስረኛን ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግለት እስር ቤት ለማዘዋወር በሺዎች የሚቆጠሩ ጸጥታ አስከባሪዎች ተሰማሩ።
ፊቶ በሚለው መጠሪያ ስሙ በስፋት የሚታወቀውን ጆሴ ኦልፎ ማሲአስ ከነበረበት እስር ቤት ወደ ሌላ ለማዘዋወር የአገሪቱ ወታደሮች እና ፖሊስ አባላት በምሽት ኦፕሬሽን አከናውነዋል።
ፊቶ በእስር ቤት እያለ በቅርቡ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለተገደሉት ፕሬዝዳንታዊ እጩ የግድያ ማስፈራሪያ ሲልክ ነበር የሚል ክስ ቀርቦበታል።
በጸረ ሙስና እንቅስቃሴያቸው የሚታወቁት ፈርናንዶ ቪላቪሴንሲዮ ከቀናት በፊት የምርጫ ቅስቀሳ አድርገው ሲመለሱ ሦስት ግዜ ጭንቅላታቸው ላይ ተመትተው ተገድለዋል።
ፕሬዝዳንታዊ እጩ ከመገደላቸው በፊት ፊቶ የግድያ ዛቻ እያላከባቸው መሆኑን ተናግረው “በእንቅስቃሴዬ የሎስ ቾኔሮስ (አደገኛ ቦዘኔ ቡድን) ስም ማንሳት ከቀጠልኩ ጉዳት ያደርሱብኛል” ብለው ነበር።
ፈርናንዶ ቪላቪሴንሲዮ በዕጽ አዘዋዋሪዎች እና በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መካከል የጥቅም ትስስር አለ በማለት በይፋ ይናገሩ የነበሩ ብቸኛው እጩ ነበሩ።
የፕሬዝዳንታዊ እጩ ግድያ በዕጽ ዝውውር ጋር የተያያዙ ግጭቶች እና ሙስና ውስጥ ለዓመታት ተዘፍቀው ለቆዩት ኤኳዶራውያንን ከፍተኛ ድንጋጤን የፈጠረ ነበር።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በኮሎምቢያ እና ሜክሲኮ የዕጽ አዘዋዋሪዎች አቅም ማደግን ተከትሎ በኤኳዶር የሚፈጸመው የወንጀል ብዛት ጨምሯል።
የአደገኛ ቦዘኔ ቡድን መሪው ፊቶ ከእአአ 2011 ጀምሮ ፕሪዝን 8 ተብሎ በሚጠራ እስር ቤት ውስጥ ታስሮ ይገኛል።
ፊቶ ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበት እስር ቤት ሲዘዋወር የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ወጥቷል።
በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ፊቶ በውስጥ ሱሪው ብቻ ሆኖ እጁ ወደ ኋላ ታስሮ እና በኃይል በታጠቁ በርካታ ወታደሮች ታጅቦ ሲወሰድ አሳይተዋል።
የኤኳዶር ፕሬዝዳንት ጉኢሌርሞ ላሶ እንዳሉት ፊቶ ላ ሮካ ተብሎ ወደሚጠራው እና 150 እስረኞችን ወደሚይዘው ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግለት እስር ቤት ተዘዋውሯል።