ከጦርነት የሚሸሹ ሱዳናውያን በሕይወት ለመቆየት ከሰል እና ቅጠል እየበሉ መሆኑ ተነገረ

የሚላስ የሚቀመስ ያጡ ሱዳናውያን ተፈናቃዮች ነፍሳቸውን ለማቆየት የዛፍ ቅጠል እና ከሰል እየበሉ መሆናቸውን አንድ የእርዳታ ድርጅት ለቢቢሲ ተናገረ።

በኤል ፋሸር ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የተፈናቃዮች ካምፕ ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ተርፈው የሸሹ ሰዎች ምግብ ለማግኘት ባለመቻላቸው ነው ያገኙትን ለመብላት የተገደዱት ተብሏል።

"እየሰማን ያለው ታሪክ በእውነት በጣም የዘገንን ነው" ሲሉ የኖርዌጂያን ሬፊዩጂ ካውነስል ኃላፊ ኖዋ ታይለር ለቢቢሲ ኒውስ ዴይ ፕሮግራም ተናግረዋል።

ሰዎች ከኤል ፋሸር ወደ ታዊሊ እየሸሹ ነው ነገር ግን "እንደደረሱ ሕይወታቸው እያለፈ ነው" ሲሉ ኃላፊው አክለዋል።

አንዳንዶቹ እጅግ በሚያቃጥል ሙቀት ከዛምዛም ካምፕ ተነስተው 40 ኪሎ ሜትር ሲጓዙ መንገድ ላይ በውሃ ጥም ምክንያት እየሞቱ ነው ብለዋል።

"በኤል ፋሸር እና ታዊላ መካከል ባለው መንገድ ላይ የወደቁ አስከሬኖች እንዳሉ ታሪኮችን እየሰማን ነው።

"ያናገርናቸው ቤተሰቦች ብቻዋን ከኤል ፋሸር ተነስታ ስትጓዝ የነበረች ሴት ልጅ በጉዞ ላይ በተደጋጋሚ የመደፈር ጥቃት እንደተፈጸመባት እና ታዊላ ስትደርስ ከደረሰባት ጉዳት የተነሳ መሞቷን ነግረውናል።"

ኤል ፋሸር በሱዳኗ ምዕራባዊ ግዛት ዳርፉር ውስጥ በሱዳን ሠራዊት እና አጋሮቹ ቁጥጥር ሥር ያለች የመጨረሻዋ ከተማ ናት። በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዛምዛም የተፈናቀዮች ካምፕ ላይ በፈጸመው ጥቃት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጊዜያዊ መጠለያውን ለቀው ሸሽተዋል።

አብዛኞ የዛምዛም ነዋሪዎች ከዚህ በፊት የነበሩትን የዳርፉር ግጭቶችን በመሸሽ ለአስርት ዓመታት ያህል በካምፑ ቆይተዋል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በገደለው እና 13 ሚሊዮን ሕዝብ ከመኖሪያቸው ባፈናቀለው ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሱዳን ጦር ሠራዊት ጋር እየተዋጋ ይገኛል።

የእርዳታ ድርጅቶች በሱዳን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በአሁኑ ወቅት በዓለም አስከፊ የሰብአዊ ቀውስ ያስከተለ እንደሆነ ይገልጻሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሱዳን ረሃብ ለተከሰተባቸው አካባቢዎች የምግብ እርዳታ የሚውል የገንዘብ ችግር ስለገጠመው አቅርቦቱን ለመቀነስ መገደዱን ገልጿል።

በጦርነቱ ውስጥ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዳርፉር የሚኖሩ አረብ ያልሆኑ ነዋሪዎችን ዒላማ አድርጎ ጥቃት ይፈጽማል በሚል ይከሰሳል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዚህ ሳምንት ጥቃቱን አስመልክተው እንደተናገሩት ድርጊቱ "የየዘር ማጽዳት እና በሰብአዊነት ላይ ከሚፈጸም ወንጀል ጋር የሚስተካከል መሆኑን አመልካች ነው" ብለዋል።

ሚኒስትሩ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች "የሰብአዊ እርዳ ሠራተኞች በፍጥነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያርቡ የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጡ" ጠይቀዋል።

በያሌ የሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የሰብአዊ እርዳታ ምርምር ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ናትናኤል ራይሞንድ እንደተናገሩት የዛምዛም ካምፕ ሙሉ ለሙሉ ተቃጥሏል።

ጨምረውም "ቤቶች እና የእርዳታ አቅርቦት መገልገያዎች ሆን ተብሎ በስልታዊ ሁኔታ በእሳት እንዲወድሙ ተደርገዋል"፤ ከዛምዛም ካምፕ ጥቃት ለማምለጥ የቻሉ ሰዎችም በመንገድ ላይ ሳሉ "በረሃብ እየሞቱ ነው" ብለዋል።

ካምፑ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጥቃት ከተፈጸመበት በኋላ "ሙሉ ለሙሉ መውደሙን" የሰሜን ዳርፉር ጤና ሚኒስትር ኢብራሂም ኻቴር ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት ከዛምዛም እየሸሹ የነበሩ ሰዎች ቤታቸው መቃጠሉን እና ተኩስ እንደተከፈተባቸው ለቢቢሰ ተናግረው ነበር። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በካምፑ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ነገር ግን ጭፍጨፋ ፈጽሟል መባሉን አስተባብሏል።