የሊቢያው ማዕከላዊ ባንክ ባለሥልጣን ከእገታ መለቀቃቸውን ተከትሎ ባንኩ ሥራ ጀመረ

የሊቢያው ማዕከላዊ ባንክ [ሲቢኤል] ከቤታቸው ታፍነው የተወሰዱት የባንኩ ባለሥልጣን መለቀቃቸውን ተከትሎ አቁሞ የነበረውን ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።

ሰቢኤል እንዳለው የባንኩ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሙሳብ ሙስላም እሑድ ዕለት ነው “ባልታወቁ ሰዎች” ከመኖሪያ ቤታቸው ታፍነው የተወሰዱት።

ባንኩ እንዳለው ሙሳብ ከዋና ከተማዋ ትሪፖሊ ሲሆን ታፍነው የተወሰዱት ሌሎችም የባንኩ ሠራተኞች የእገታ ማስፈራሪያ ደርሷቸዋል።

ሲቢኤል፤ ሙሳብ እስካልተለቀቁ ድረስ በሩን ለደንበኞች እንደማይከፍት አስታውቆ ነበር።

ሰኞ ከሰዓት አጠር ያለ መግለጫ የለቀቀው ባንኩ፤ ሙሳብ “ደኅንነታቸው ተጠብቆ” በመለቀቃቸው ምክንያት ሥራ መጀመሩን ይፋ አድርጓል።

ማዕከላዊው የሊቢያ ባንክ ገለልተኛ ቢሆንም የሊቢያ መንግሥት ንብረት ነው።

ባንኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሊቢያን የነዳጅ ግብይት መፈፀም የሚችል ብቸኛው እውቅና ያለው ድርጅት ነው።

በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀው ሊቢያ ለበርካታ ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት እየማቀቀች ሲሆን ትሪፖሊ የሚገኘው መንግሥት እና መቀመጫውን ቤንጋዚ ያደረገው መንግሥት ለሥልጣን እየተጋደሉባት ይገኛሉ።

ባንኩ ከአንድ ሳምንት በፊት በታጠቁ ኃይሎች ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ነው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ግለሰብ ታግተው የተወሰዱት ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ፅፏል።

ኤኤፍፒ ዋቢ ያደረገው አንድ የሀገር ውስጥ ዘገባ እንደሚለው የታጠቁት ግለሰቦች ጥቃት የፈፀሙት የባንኩ ገዥ ሰዲቅ አል-ካቢር ከሥልጣን እንዲወርዱ ለማስገደድ ነው።

ከአውሮፓውያኑ 20212 የባንኩ ገዥ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ካቢር የነዳጅ ምርቶችን በብቃት አላስተዳደሩም እንዲሁም የሀገሪቱን በጀት አዛብተዋል የሚሉ ትችቶች ይድርስባቸዋል።

ሰኞ ዕለት የባንኩ ገዥ “በባንኩ ደኅንነት እና ፀጥታ እንዲሁም በሠራተኞቹ እና ሲስተም ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ስላለው ጥቃት” በተመለከተ በሊቢያ የብሪታኒያ አምባሳደር ከሆኑት ማርቲን ሎንግዴን ጋር መምከራቸውን ባንኩ አስታውቋል።

የሊቢያው መሪ ሙአማር ጋዳፊ በአውሮፓውያኑ 2011 ከሥልጣን እንዲወርዱ ተደርገው ከተገደሉ በኋላ ሀገሪቱ በከፍተኛ መመሰቃቀል ውስጥ ትገኛለች።

በሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት የተከፋፈለችው ሊቢያ ሁለት መንግሥታት ያሏት ሲሆን ትሪፖሊ የሚገኘው እና በተባበሩት መንግሥት እውቅና የሚሰጠው መንግሥት እንዲሁም በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኘው በጀኔራል ኻሊፋ ሀፍጣር የሚመራው አገዛዝ ለበርካታ ዓመታት ጦርነት ሲያደርጉ ቆይተዋል።