ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትኞቹ አገራት በአሜሪካ ምርጫ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ጣልቃ ይገባሉ?
በቅርቡ የዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን በኢራን አማካይነት የበይነ መረብ መጠለፍ ጥቃት እንደተፈጸመበት አስታውቋል።
ይህም ከአሜሪካ ባሻገር በመላው ዓለም በጉጉት የሚጠበቀው የአሜሪካ ምርጫ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ሊገጥሙት እንደሚችሉ አንድ ማሳያ ነው።
የምርጫው ውጤት በመላው ዓለም ተጽዕኖ ይኖረዋል። ስለዚህም ብዙ አገራት ጣልቃ በመግባት ዕጩዎቹን መደገፍ ወይም ማሰናከል ሊፈልጉ አልያም አሜሪካን ለማወክ ሊጠቀሙበት እየተባለ ነው።
የአሜሪካ ያላት ግልጽ ዴሞክራሲ እና መገናኛ ብዙኃን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ተደማምሮ የምርጫውን ውጤት ለመለወጥ ለሚሹ ምቹ ዕድል ሊከፍት ይችልም ይሆናል።
የአሜሪካው ፕሩዝዳንት የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት ጄክ ሱሌቨን ባለፈው ወር “ጠላቶቻችን የአሜሪካን ምርጫ በመጠቀም ጫና ማሳደር ይሻሉ። ዴሞክራሲያችንን ለማጣጣል ወይም ሚዛኑን ለማዛባት ይሞክራሉ። ይህን በደንብ እናውቃለን። ለመቋቋም ብዙ ጥረት እያደረግን ነው” ብለዋል።
ኢራን፣ ሩሲያ እና ቻይና በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ይገባሉ? የሚለውን ይህ ዘገባ ይዳስሳል።
ኢራን
“ኢራን በውጭ አገራት ጣልቃ ለመግባት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ቀጥላለች። ይህም ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለማሰናከል ነው”ሲሉ የአሜሪካ ብሔራዊ ስለላ ተቋም ኃላፊ አቭሪል ሄንስ ይናገራሉ።
የዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን በኢራን የበይነ መረብ መጥለፍ እንደተፈጸመበት ቢያስታውቅም፣ ከምርጫ ቅስቀሳ ጋር የተያያዙ እና የተሰረቁ ሰነዶች ለመገናኛ ብዙኃን የቀረቡት ከዚህ ጋር በተያያዘ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።
ማይክሮሶፍት በቅርቡ ከኢራን ጋር ትስስር ባላቸው ቡድኖች “ጫና የማሳደር እንቅስቃሴ ተስተውሏል” ሲል አስታውቋል።
ጉግል ደግሞ ኢራን የምትደግፋቸው መረጃ ሰርሳሪዎች የዶናልድ ትራምፕን የምርጫ ቅስቀሳ እና ጆ ባይደን ከውድድሩ ከመውጣታቸው በፊት የምርጫ ቅስቀሳቸውን ዒላማ አድርገዋል ብሏል።
ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ እንዳይመለሱ ለማድረግ በኢራን በኩል ጥረቶች እንዳሉ ይታመናል።
ከኢራን ጋር ከተደረሰው የኑክሌር ስምምነት ከመውጣት ጋር በተያያዘ የትራምፕ ቡድን ያለው ጠንካራ አቋም እና በ2020 የኢራን ጄኔራል ቃሲም ሱሌማኒ ከመገደላቸው ጋር በተያያዘ ኢራን የትራምፕን መምጣት አትሻም።
ከጋዛ ጦርነት ጋር በተያያዘ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚሠራጭ መረጃም ኢራን ስሟ ይነሳል።
ሩሲያ
የአሜሪካ ደኅንነት ተቋም በቅርቡ ባወጣው መረጃ “ለአሜሪካ ምርጫ ቀንደኛ አደጋ ሆና የቀጠለችው ሩሲያ ናት” ብሏል።
ከኢራን አንጻር ግን ሩሲያ እስካሁን በግልጽ የታየ ነገር አላደረገችም።
ሩሲያ ከቀዝቃዛው ጦርነት አንስቶ በአሜሪካ ምርጫ የሕዝብ አስተያየትን ለመለወጥ “ጠንካራ እርምጃ” በመውሰድ ትታወቃለች።
በአውሮፓውያኑ 2016 ምርጫ ያለ አሜሪካ ዕውቅና በሩሲያ የተመራ ነው በተባለ ኦፕሬሽን አማካይነት የዲሞክራቶች ዕጩ ፕሬዝዳንት የነበሩት የሂላሪ ክሊንተን ኢሜሎች ተመዝብረው ይፋ መውጣታቸው ይታወሳል።
የሩሲያ ስለላ ተቋም ኤስቪአር እንዲሁም ወታደራዊ የስለላ ተቋም ጂአርዩ ሥር ያሉ የሩሲያ መረጃ ሰርሳሪዎች በችሎታቸው ከላቁት መካከል እንደመሆናቸው አሁንም ሙከራዎች ሊያደርጉ ይችላሉ።
በ2016 ምርጫ በማኅበራዊ ሚዲያ ሐሰተኛ ምሥሎች በሩሲያ አማካይነት ሲሠራጩ ነበር። እነዚህም ሂላሪ ክሊንተን ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ያስነሱ ነበሩ።
አሁን ግን ሩሲያ በእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ ኃላፊነቱን ለሌሎች ተቋማት ልትሰጥ ትችላለች።
የደኅንነት ባለሙያዎች እንደሚሉት ሩሲያ ጣልቃ የምትገባ ከሆነ የምትደግፈው ትራምፕን ይሆናል።
ትራምፕ ለሩሲያ እንደ ወዳጅ ሲሆኑ ሩሲያ በጠላትነት ከምትመድባቸው መካከል አንዱ የሆነውን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ተቺም ናቸው።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግን ትራምፕን መደገፋቸውን አስተባብለዋል።
ቻይና
ቻይና ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ በአሜሪካ በሚካሄዱ ምርጫዎች ዙሪያ መረጃ ሰርስሮ በማግኘት ትታወቃለች።
ከምርጫው አንዳች ውጤት ለማግኘት በመሞከር ረገድ ከኢራን እና ሩሲያ አንጻር ሲታይ ግን ያን ያህል የጎላ ነው ለማለት አይቻልም።
የአሜሪካ ደኅንነት ተቋም ቻይና “የምርጫው ውጤት ላይ ጫና ለማሳደር ላትሞክር ትችላለች” ሲል ነው የሚገልጸው።
ቻይና ከዕጩዎቹ ማንን ልትደግፍ እንደምትችልም ግልጽ አይደለም።
ትራምፕ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ለማወቅ ከባድ ከመሆኑ ባሻገር ቻይና ላይ ጠንካራ አቋም አላቸው።
ከቻይና ጋር በመተባበር የሚያምነውን የባይደን አስተዳደር ፖሊሲን ሊያስቀጥሉ የሚችሉበት ዕድል ጠባብ መሆኑ ቻይናን ያሰጋል።
ቻይና በአሜሪካ ምርጫ ውስጥ ጣልቃ ገብታለች መባልን አትሻም። ኢራን እና ሩሲያ ግን ይህ አያሳስባቸውም።
ቻይናን በሚመለከቱ ጉዳዮች ግን በኮንግረስ ምርጫ ደረጃ ዕጩዎች ላይ ቻይና ተጽዕኖ ታሳድራለች እየተባለ ይነገራል።
በ2022 (እአአ) የግማሽ ዓመት ምርጫ በዴሞክራቶች እና በሪፐብሊካኖችም ውስጥ ቻይና ጣልቃ መግባቷ ተገልጿል።
ነገር ግን ከአሜሪካ ጋር በዐይነ ቁራኛ የሚጠባበቁት ኢራን፣ ሩሲያ እና ቻይና ስማቸው ቢነሳም በአሜሪካ ምርጫ ወሰጥ ጣልቃ መግባታቸውን በተመለከተ በተደጋጋሚ ያስተባብላሉ።
የአሜሪካ ፈተና
በአወሮፓወያኑ 2016 በሩሲያ የመረጃ ሰርሳሪዎች ይፋ የተደረገ መረጃ ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን አግኝቷል።
አሁን ግን መገናኛ ብዙኃን ለተሰረቀ መረጃ የሚሰጡትን ሽፋን በመቀነስ ሚናቸውን እያሳነሱ መጥተዋል።
በተጨማሪም ከምርጫ ቅስቀሳ ጋር በተያያዘ የተሻለ የመረጃ ደኅንነት ለመዘርጋት ጥረት ይደረጋል። ሆኖም ግን ፈተናዎች አሉ።
የውጭ ጣልቃ ገብነትን ከዲፕሎማሲያዊ ነጻ ንግግር ጋር መለየት አለመቻሉ አንደኛው ፈተና ነው።
አንዳንድ አገራት አሜሪካውያንን በመጠቀም መልዕክታቸውን ለማስተላለፍ ወይም ለማስረጽ ይሞክራሉ።
አንዳንዶቹ አሜሪካውያን ለዚህ ፈቃደኛ ሲሆኑ፣ ሌሎች ግን የሚኖረወን ወጤተ ባለማወቅ ይገቡበታል።
በዚህም ሳቢያ ለሩሲያ እንደሚሠሩ ባለማወቅ ለሩሲያ ድረ ገጾች የሚጽፉ አሜሪካውያን አሉ።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት አና ዲፕፌክ ሌሎቹ የቴክኖሎጂ ዕድገትን ያማከሉ ስጋቶች ናቸው።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተሻለ ሁኔታ ሰዎች ላይ አነጣጥሮ ሐሰተኛ መረጃ ማስተላለፍ የሚቻልበት መንገድ መብዛት፣ ሰዎች እውነቱን አና ውሸትን መለየት እንዲቸገሩ አድርጓል።
ዘንድሮ በተለያዩ አገራት በተካሄዱ ምርጫዎች የተፈራውን ያህል ቴክኖሎጂን ያማከሉ ጣልቃ ገብነቶች አልታዩም።
የአሜሪካ ምርጫ ዓለም አቀፍ ሚናው የጎላ ስለሆነ እና ፉክክሩ የጦፈ በመሆኑ ግን ስጋቶቹ የበለጠ ይስተጋባሉ።
በዚህም ሳቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚታዩ ጫና መፍጠሪያ መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ።
ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ የፖለቲካ ልዩነት መካረር መኖሩ እነዚህን መንገዶች አደገኛ ሊያደርጋቸው የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው።
የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ነበሩ የሚለው ሐሳብ በራሱ ሌላ ፖለቲካዊ ትርጓሜ ተሰጥቶት የምርጫውን ውጤት አጠራጣሪ ሊያደርገውም ይችላል።