ሩሲያ በኻርኪቭ ሱፐርማርኬት ላይ ባደረሰችው ጥቃት 11 ሰዎች ተገደሉ

በሰሜን ዩክሬኗ ኻርኪቭ ከተማ የሚገኝ ሱፐርማርኬት በሩስያ ጦር ግላይድ ቦምብ ከደረሰበት በኋላ 11 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ቆስለዋል ሲሉ የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግሩ።

በከተማው ሰሜናዊ ዳርቻ በሚገኘው ኤፒሴንተር ኬ በተባለው መደብር ላይ ከፍተኛ እሳት መነሳቱም ታይቷል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ፤ ጥቃቱ በተፈፀመበት ወቅት ከ200 በላይ ሰዎች በሱፐርማርኬቱ ውስጥ ሊገኙ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የኻርኪቭ ገዥ ኦሌህ ሲኒዬሁቦቭ የሟቾች ቁጥር ወደ 11 ከፍ ማለቱን እሑድ ዕለት አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል ስድስት ሰዎች “በጥቃቱ ቦታ ሞተዋል" ሲሉ ተናግረው ነበር። 40 ሰዎች መቁሰላቸውን እና 16 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁንም ገልጸው ነበር።

የኻርኪቭ ከንቲባ ኢጆር ቴሬኮቭ “ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ጠፍተዋል፤ ይህ ግልጽ ሽብርተኝነት ነው” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ አክለውም “በኻርኪቭ ላይ የተደረገው ይህ ጥቃት የሩሲያ እብደት መገለጫ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

"እንደ (የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር) ፑቲን ያሉ እብዶች ብቻ ናቸው በዚህ መንገድ ሰዎችን መግደል እና ማሸበር የሚችሉት።"

ቴሬኮቭ አክለውም በማዕከላዊ ኻርኪቭ በደረሰ ሁለተኛ ጥቃት ስምንት ሰዎች ቆስለዋል።

ጥቃቱ ዩክሬናውያን የአየር መከላከያ ስለሌላቸው የሚሰማቸውን ጭንቀት የሚያጎላ ነው ተብሏል።

ዜለንስኪ አክለውም ዩክሬን እራሷን መከላከል እንድትችል ከምዕራባውያን አጋሮች የአየር መከላከያ መሣሪያዎችን እንደምትፈልግ በድጋሚ ገልጸዋል ።

በጣሊያን በተካሄደው የጂ7 የገንዘብ ሚኒስትሮች ስብሰባ ከታገዱ የሩሲያ ንብረቶች የሚገኘውን ትርፍ ለዩክሬን የጦርነት ዘመቻ እንዲውል ለማድረግ የቀረበውን ሃሳብ መደገፋቸውን ተከትሎ የመጣ ጥቃት ነው።

የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ጃኔት ዬለን ሃሳቡ ሰፊ ድጋፍ አለው ብለዋል።

አሜሪካ ባዘጋጀቸው ዕቅድ መሰረት የጂ7 አባል አገራት እና አጋሮቻቸው ለኪዬቭ 50 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት በምዕራባውያን ባንኮች እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ የሩሲያ ንብረቶችን እንደ ብድር ማስያዣ ይጠቀማሉ። ሃሳቡ በሚቀጥለው ወር ተጨማሪ ውይይት ይደረግበታል።

ሩሲያ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች።

በካርኪቭ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሞስኮ ያላት በራስ የመተማመን ስሜት እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ሌላ ምልክት ነው ተብሏል። ዩክሬን ተጨማሪ የምዕራባውያን ጦር ድጋፍ ለማግኘት እየተጠባበቀች ባለችበት ጊዜ ሩሲያ ዕድሉን ተጠቅማ ለማጥቃት የወሰነች ይመስላል።

በጥቃቱ ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉት ግላይድ ቦምቦች በአሮጌ የሶቪየት ቦምቦች ላይ የሚተጣጠፉ ክንፎችን እና የሳተላይት መረጃ እንዲያገኙ በማድረግ የተሠሩ ናቸው። ርካሽ ቦምቦች ቢሆኑም ግን አጥፊ ናቸው ተብሏል።

ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ እንዳሉት ከሆነ በመጋቢት ወር ብቻ ሦስት ሺህ ያህል ግላይድ ቦምቦች በአገሪቱ ላይ ተጥለዋል።

የአውሮፓ የፖሊሲ የጥናት ማዕከል (ሲኢፒኤ) በቅርቡ ባወጣው ዘገባ እንደገለጸው ከሆነ በየካቲት ወር ቁልፍ የሆነችውን አቪዲቪካ ከተማ ለመያዝ ቦምቡ ወሳኝ ነበር።