ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማንቸስተር ዩናይትድ የከተማ ተቀናቃኙ ማንቸስተር ሲቲን በመርታት የኤፍ ኤ ዋንጫ ባለቤት ሆነ
ማንቸስተር ዩናይትድ እና በኦልድ ትራፈርድ ያላቸው ቆይታ ጥርጣሬ ውስጥ የገባው ኤሪክ ቴን ሀግ የተቺዎቻቸውን አፍ በማስዘጋት የኤፍ ኤ ዋንጫ ባልድል ሆነዋል።
ዩናይትድ አስደናቂ ፍልሚያ ባሳየበት ጨዋታ ለዋንጫው ብዙ ግምት የተሰጠውን ማንቸስተር ሲቲ በማንበርከክ ባልድል ሆኗል።
የማንቸስተር ዩናይትድ አዲሱ ባልድርሻ ሰር ጂም ራትክፍሊፍ የዋንጫ ጨዋታው ውጤት ምንም ይሁን ምን ኤሪክ ቴን ሀግን ለማሰናበት መቁረጣቸው እየተነገረ ነበር።
ቴን ሀግ ኦልድ ትራፈርድን ለቀው የሚሄዱ ከሆነ በማንቸስተር ማልያ ትልቁን ድል አሳክተው ነው የሚሄዱት ሲሉ አስተያየት ሰጭዎች አድናቆት ችረዋቸዋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ በቅርቡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ያሳየው ብቃት እጅግ በጣም የወረደ ነበር።
ቀያይ ሰይጣኖቹ የዋንጫ ባለቤት መሆናቸውን ተከትሎ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ባለቤት የሆነው ሲቲ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ ሁለት የሀገር ውስጥ ዋንጫ ለማንሳት የነበረውን ሕልም ከስሟል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ድንቅ ብቃት ያሳየው ዩናይትድ በታዳጊዎች አሌሃንድሮ ጋርናቾ እና ኮቢ ሜይኑ ጎሎች ሁለት ለምንም እየመሩ ከሜዳ ወጥተዋል።
በሲቲው ተከላካይ ጆስኮ ግቫርድዮል እና በግብ ጠባቂው ስቴፈን ኦርቴጋ መካከል የተፈጠረውን ስህተት ተከትሎ ጋርናቾ ያገኛትን ነፃ ኳስ ከመረብ በማዋሀድ የመጀመሪያውን ጎል አስቆጥሯል።
ሌላኛው ታዳጊ አማካይ ኮቢ ሜይኖ ከአምበሉ ብሩኖ ፈርናንዴዝ የተሻገረችለትን ኳስ በተረጋጋ ሁኔታ በማስቆጠር ከመጀሪያው አጋማሽ በፊት ቡድኑ 2 ለባዶ እንዲመራ ማድረግ ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ እንደተጠበቀው ማንቸስተር ሲቲ ጫና ፈጥሮ ለመጫወት ሞክሯል። ኧርሊንግ ሀላንድ የመታት ኳስ የጎሉን ቋሚ ብረት መትታ ስትመለስ፤ ካይል ዎከር አክርሮ ወደ ጎል የሰደዳት ኳስ ደግሞ በግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና ተመልሳለች።
ተቀይሮ የገባው የሲቲ የክንፍ መስመር ተጫዋች ጄሬሚ ዶኩ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 4 ደቂቃዎች ሲቀሩት አንድ ጎል ቢያስቆጥር የቴን ሀግ ልጆች የቀረውን ደቂቃ በጥንቃቄ በመከላከል ለቡድናቸው 13ኛውን የኤፍ ኤ ዋንጫ አስገኝተዋል።
ጨዋታው ሲጠናቀቅ የዩናይትዱ ተከላካይ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ አሰልጣኙ ኤሪክ ቴን ሀግን አቅፎ ወደሰማይ በመስቀል ደስታውን ገልጧል።
አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ይሰናበታሉ ወይ የሚለው ጥያቄ ከጨዋታው በፊት እና በኋላ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። ነገር ግን የቴን ሀግ ዕጣ ፈንታ ወሳኝ የሆኑት ራትክሊፍ በዋንጫው ስኬት በፈገግታ ተሞልተው ታይተዋል።
ዩናይትድ በግማሽ ፍፃሜው በአስደናቂ ሁኔታ ሊቨርፑልን 4-3 በመርታት፤ በግማሽ ፍፃሜው ደግሞ ከኮቨንትሪ ተገናኝተው ከመዋረድ ለጥቂት በመትረፍ ነው ለመጨረሻው ጨዋታ የደረሱት።
ቅዳሜ ዕለት በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የዩናይትድ ተጫዋቾች የሲቲ ተጫዋቾች ምንም ዓይነት ውጤታማ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ በማድረግ ብዙዎችን ያስደነቀ ብቃት አሳይተዋል።
ሁለተኛዋ የሜይኑ ጎል የማርከስ ራሽፈርድን ረዥም ኳስ አሻግሮ የማቀበል ብቃት ያሳየ እና ጋርናቾ ፈርናንዴዝን ፈልጎ ማቀበል እና የኮቢ ሜይኑን የተረጋጋ አጨራረስ ያስመለከት ሆኗል።
የ19 ዓመቱ ሜይኑ በዚህ ዕድሜው አማካይ ክፍሉን በበሰለ መልኩ ሲቆጣጠር ታይቷል። የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው ሜይኑ በአውሮፓ ዋንጫ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ወክሎ ወደ ጀርመን ያቀናል።
የማንቸስተር ሲቲው ሮድሪ በሲቲ ማሊያ ላለፉት 75 ጨዋታዎች የነበረው ያለመሸነፍ ክብረ-ወሰን ተሰብሯል። የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የዓመት ምርጥ ተጫዋች የተባለው ፊል ፎደን ደግሞ የረባ እንቅስቃሴ ሳያደርግ ወጥቷል።
ድሉን ተከትሎ ማንቸስተር ዩናይትድ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን የዩሮፓ ሊግ ተወዳዳሪ መሆኑን ሲያረጋግጥ፤ ቼልሲ ወደ ኮንፈረንስ ሊግ ተንሸራቷል።