ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታዋቂዋ ራፐር ኒኪ ሚናጅ አደንዛዥ ዕፅ ይዛለች ተብላ በአምስተዳርም ፖሊስ መታሰሯን ተከትሎ 'ኮንሰርቷ' ተሰረዘ
አሜሪካዊቷ ራፐር ኒኪ ሚናጅ በአምስተርዳም ፖሊስ መታሰሯን ተከትሎ በዩናይት ኪንግደሙ ማንቸስተር አሬና የነበራት የሙዚቃ ድግስ ተሰርዟል።
ኒኪ ሚናጅ ጠንካራ ያልሆነ አደንዛዥ ይዛ ተገኝታለች በሚል ተጠርጥራ በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ ቅጣት ተጥሎባት መለቀቋን የኔዘርላንድስ ፖሊስ ገልጧል።
ነገር ግን ቅዳሜ ዕለት በማንቸስተር ለነበራት 'ኮንሰርት' በጊዜ ባለመድረሷ የሙዚቃ ድግሱ ተሰርዟል። 20 ሺህ ገደማ የኒኪ ሚናጅ አድናቂዎች የሙዚቃ ድግሱን በጉጉት ሲጠባበቁ ነበር።
አንዳንድ ታዳሚዎች በ150 ፓውንድ ቲኬት ገዝተው ሥራቸውን ትተው ለ3 ሰዓታት ያክል የሙዚቀኛዋን መገኘት ሲጠባበቁ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የ17 ዓመቲ ኤሊስ ደይ ከቼሻየር ግዛት ወደ ማንቸስተር ያቀናው ኒኪ ሚናጅን ለመመልከት ቢሆንም ያሰበው ሳይሳካ ቀርቷል።
በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ምሽት 1፡00 የራፐሯ አድናቂዎች ወደ አዳራሹ እንዲገባ ቢፈቅድላቸውም ምሽት 3፡30 ግድም ሙዚቀኛዋ እንደማትገኝ ተነግሯቸዋል።
አድናቂዎቹ ማንቸስተር አሬና የተባለውን ግዙፍ አዳራሽ ለቀው ከመውጣታቸው በፊት በብስጭት ድምፃቸውን ከፍተው አድርገው ሲያጉረመርሙ ተሰምተዋል።
ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የተለጠፉ ቪድየዎች እንደሚያሳዩት ሙዚቀኛዋ መድረክ ላይ ወጥታ ሥራዋን ማቅረብ በሚገባት ሰዓት የኒኪ ሚናጅ አውሮፕላን ገና ከአምስተርዳም አልተነሳም ነበር።
ምንም እንኳ ሙዚቀኛዋ ከአቅሟ በላይ በሆነ ምክንያት በሰዓቷ መገኘት ባትችልም አድናቂዎቿ ግን በጊዜ ሊነገረን ይገባል የሚል ቅሬታ ያሰማሉ።
ኒኪ ሚናጅ በማሕበራዊ ሚድያ ገጿ በለቀቀችው መልዕክት ከአምስት እስከ ስድስት ሰዓታት በጊዜያዊ እሥር ቤት እንደቆየችና ማንቸስተር የደረሰችው እኩለ ለሊት እንደሆነ ተናግራለች።
"በሰዓቴ መድረክ ላይ እንዳልወጣ ያደረጉት ሙከራ ተሳክቷል" ስትል በኤክስ [የቀድሞው ትዊተር] ገጿ ብትገልጥም ማንን እየወቀሰች እንደሆነ አላሳወቀችም።
"እባካችሁ፤ ስለምናችሁ ከልብ የመነጭ ይቅርታየን ተቀበሉኝ" በማለት አድናቂዎቿን ይቅርታ ጠይቃለች።
ኒኪ ሚናጅ እንዳለችው ኮንሰርቱ የሚካሄድበት አዲስ ቀን እሑድ ዕለት ይፋ የሚሆን ሲሆን ቀድመው ቲኬት ለቆረጡ አድናቂዎቿ "የምስራች የሆነ ጉርሻ" ተዘጋጅቷል።
ሚናጅ ቅዳሜ ከሰዓት በአምስተርዳም ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ስትውል የነበረውን ሁኔታ በማሕበራዊ ሚድያ ቀጥታ ስታስተላልፍ ነበር።
በዚህ ቪድዮ ላይ እንደሚታየው ከሆነ አንድ የፖሊስ መኮንን "በቁጥጥር ሥር ውለሻል" ሲላት ራፐሯ ደግሞ "እኔ ምንም ዓይነት አደንዛዥ ዕፅ አልያዝኩም" ስትል ትመልሳለች።
የራፕ ሙዚቃ ዘውግ ኮከቧ የነበረውን ሁኔታ የሚገልጡ በርካታ መልዕክቶች በኤክስ ገጿ ስትለጥፍ ነበር።
ምንም እንኳ በኔዘርላንድስ አደንዛዥ ዕፅ ይዞ መገኘት፣ መሸጥ አሊያም ማምረት በሕግ ቢያስቀጣም ሀገሪቱ ላላ ያለ ሕግ በማራመድ ትታወቃለች።
ኒኪ ሚናጅ እሑድ ዕለት በበርሚንግሀም ሌላ የሙዚቃ ድግስ ያላት ሲሆን ቀጥሎ ለንደን እና ግላስጎው አምርታ ሐሙስ ዕለት ተመልሳ ማንቸስተር ከተማ እንደምትመጣ ይጠበቃል።