በጅማ ዞን "ንብረትህን ስለሰረቅኩ ይቅር በለኝ" ሲል ደብደቤ የጻፈው ሌባ አነጋጋሪ ሆኗል

በጅማ ዞን አንድ ሌባ ለግል ተበዳይ "ንብረትህን ስለሰረቅኩ ይቅርብ በለኝ" ሲል የጻፈው ደብደቤ አነጋገሪ ሆኗል፡፡

በጅማ ዞን ከግል ተባዳይ መኖሪያ ቤት በመስኮት በኩል ገብቶ የወሰደውን ወስዶ፤ በልቶ ጨርሶ ሲያበቃ "ፈጣሪ አድሎሃልና ቻለኝ። ንብረትህን ስለሰረቅኩ ይቅር በለኝ" ብሎ የጻፈው ሌባ በስፋት እያነጋጋረ ነው።

ፖሊስ እስካሁን ድረስ ከሰው ቤት ገብቶ ንብረት በመስረቅ ወንጀል የጠረጠረውን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ባያውለውም ተጠርጣሪው ከጻፈው ደብደቤ በመነሳት ግን ግለሰቡ ተማሪ ሳይሆን እንደማይቀር ገምቷል።

ይህ ክስተት ያጋጠመው በኦሮሚያ ክልል፣ ጅማ ዞን፣ ጌራ ወረዳ ውስጥ ነው።

እስካሁን በቁጥጥር ሥር ያልዋለው እና በስርቆት ወንጀል የተጠረጠረው ግለሰብ ከግል ተበዳይ አቶ ጋሪ ተስፋዬ መኖሪያ ቤት ገብቶ 9 የተለያዩ እቃዎችን ይወስዳል።

ይህን ተከትሎ የግል ተበዳይ የሆኑትና በወረዳው በሚገኝ ገቢዎች ጽ/ቤት የሚሠሩት አቶ ጋሪ ጉዳዩን ለፖሊስ ሪፖርት ያደርጋሉ።

"ሌባ ቤቴ ገብቶ የተለያዩ እቃዎችን እንደወሰደብኝ እና ቤት ውስጥ የነበረውን ምግብ በልቶ እንደሄደ ለፖሊስ አሳውቂያለሁ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ጋሪ ለፖሊስ ሪፖርት ባደረጉ በቀጣይ ቀን ግን ብዙዎችን ያስነደቀ ጉዳይ ይከሰታል።

ተጠርጣሪው ከሰረቃቸው 9 እቃዎች መካከል 6ቱን እቃዎች ማንም ሳያየው ከግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት መልሶ አስቀምጧል።

ቀሪዎቹን ሦስቱ እቃዎች "ይጠቅሙኛል" በማለት አስቀርቷቸዋል፡፡

ከዚህ ሁሉ አስገራሚው ደግሞ የይቅርታ ደብዳቤ አብሮ ቤት ውስጥ ማኖሩ ነበር፡፡

አቶ ጋሪ፣ ሌባ ቤታቸው ገብቶ መዘረፋቸውን ለፖሊስ ሪፖርት ባደረጉ ማግስት፤ ጠፍተው ከነበሩት ዘጠኝ ዕቃዎች 6ቱ መመለሳቸውን ለማሳወቅ እና በተለይም ደግሞ የተጻፈላቸውን የይቅርታ ደብዳቤ ይዘው ዳግም ወደ ፖሊስ ጣቢያ መሄዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጌራ ወረዳ ዐቃቤ ሕግ አቶ ተሬሳ ኢዶሳ ተርጣሪው ከሰው ቤት ገብቶ የወሰዳቸውን 9 እቃዎች በደብዳቤው መዘርዘሩን እና ከእነዚህም መካከል ሦስቱን ማስቀረቱን በትክክልም ገልጿል ይላሉ።

ተጠርጣሪው ከግል ተበዳይ ቤት ገብቶ የወሰዳቸው እቃዎች፤ የሰውነት ሙቀት መለኪያ ቴርሞሜትር፣ የሰውነት ውስጥ ድምጽ ማዳመጫ (ስቴቴስኮፕ)፣ አንድ ሞባይል ስልክ ከነ ሲም ካርዱ፣ ሙዚቃ ማዳመጫ፣ ሁለት ሞባይል ቻርጀር፣ የሕክምና የእጅ ጓንት፣ እስክሪፕቶዎች፣ 25 ብር እና የኪስ ቦርሳ ናቸው።

ዐቃቤ ሕጉ አቶ ተሬሳ፣ የአቶ ጋሪ ባለቤት የጤና ባለሙያ በመሆናቸው የሕክምና መገልገያ ቁሳ ቁሶች በመኖሪያ ቤቱ ሊገኝ መቻሉን ይገልጻሉ።

ተጠርጣሪው ስርቆቱን ከፈጸመ በኋላ መጸጸቱን ከጻፈው ደብዳቤ መረዳት ይቻላል ይላሉ ዐቃቤ ሕግ ተሬሳ።

"ተማሪ መሆኑን እና እንደተቸገረ በደብዳቤው ገልጿል። 'ፈጣሪ ይጠይቀኛል' ብሎ ከወሰዳቸው በርካታ እቃዎች የእጅ ጓንት፣ እስክሪቢቶዎች እና 25 ብር ብቻ አስቀርቶ የተቀረውን መልሷል።"

"ከዚህ በተጨማሪም በጣም እርቦኝ ስለነበረ 'ምግብ ወስጄ በልቻለሁ' ሲል በደብዳቤው ጽፏል" ሲሉ አቶ ተሬሳ ያስረዳሉ።

ይህ ብቻ አይደለም ታዲያ በደብዳቤው የተብራራው፤ ተጠርጣሪው እንዴት አድርጎ ወደ መኖሪያ ቤቱ ዘልቆ እንደገባ እና እቃዎቹን ይዞ እንደወጣ በደብዳቤው በዝርዝር ተተርኳል ብለዋል።

ዐቃቤ ሕጉ ይህ በወረዳው ያጋጠመው ክስተት፣ "የትኛውም ወንጀል የአእምሮ እረፍት ስለሚከለክል እራሳችንን ከወንጀል እንድንጠብቅ ያስተምረናል" በማለት ኅብረተሰቡ ራሱን ከወንጀል ድርጊት እንዲጠብቅ እግረ መንገዱን መልዕክት አስተላልፈዋል።