ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጀርመንና ጣሊያን ከናዚ ዘመን የካሳ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ተካሰሱ
ጀርመን ጣሊያንን በተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሳታለች፡፡
ምክንያቱ ደግሞ ጣሊያን በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ናዚ በዜጎቿ ላይ ላደረሰው ስቃይ ካሳ እየጠየቀች ስላስቸገረቻት ነው፡
ጀርመን ጉዳዩን ወደ ኔዘርላንድስ፣ ሄግ ዳኝነት የወሰደችው ይህን የጣሊያንን የካሳ ጥያቄ ለማስቆም ነው፡፡
ጣሊያን በበኩሏ የጀርመን መንግሥት በናዚ ዘመን በዜጎቿ ላይ ላደረሰው ሞት፣ ስቃይና እንግልት ካሳ ይገባኛል በሚል በርካታ ክስ በአገሯ ፍርድ ቤቶች ከፍታ ጉዳዩ እየታየ ነው፡፡
ጀርመን የምትለው ደግሞ በፈረንጆቹ 2012 በተሰጠ ፍርድ ከእንግዲህ አገሮች በናዚ ዘመን ለተፈጠረ ጉዳይ የካሳ ጥያቄን አያስተናግዱም የሚለውን ውሳኔ ጣሊያን ቸል ብላዋለች ነው፡፡
ይህ ውሳኔ ከተሰጠ ወዲህ በርካታ የካሳ ጉዳዮችን በአገሯ ፍርድ ቤት እንዲስተናገዱ እያደረገች ነው ስትል ጀርመን ጣሊያንን ከሳለች።
በናዚ ዘመን ለተፈጸሙ ወንጀሎች የካሳ ጉዳዮችን እየተመለከቱ ያሉ የጣሊያን ፍርድ ቤቶች አንዳንዶቹ ጀርመን ካሳ እንድትከፍል ውሳኔ የሰጡ ናቸው፡፡
አሁን ጀርመን ጉዳዩን ወደ ሄግ የወሰደችው በቅርቡ ሁለት በጣሊያን ፍርድ ቤት የታዩ የካሳ ክሶች በሮም የሚገኙና የጀርመን መንግሥት ንብረት የሆኑ ሕንጻዎች ተሸጠው ለተጎጂ ቤተሰቦች ገንዘቡ እንዲሰጥ መወሰናቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የጣሊያን ፍርድ ቤት በቅርቡ የጀርመን ባሕልና የትምህርት ማዕከላት የሚገኙባቸው ሕንጻዎች ሽያጫቸው በግዳጅ ይፈጸም ወይስ ይቆይ በሚለው ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔን ይሰጣል፡፡
ይህ በጀርመንና ጣሊያን መካከል በናዚ ዘመን በደሎች ዙርያ መካረሩ የጀመረው እንደነርሱ አቆጣጠር በ2008 የጣሊያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጀርመን በናዚ ዘመን ተጎጂ ለሆኑ ጣሊያናዊያን ቤተቦች 1 ሚሊዮን ዩሮ እንድትከፍል ከፈረደ በኋላ ነበር፡፡
ይህም በቁጥር 203 ለሚሆኑና በጀርመን የናዚ ቡድን በ1944 በተለይም በቱስካኒ ለተገደሉባቸው ቤተሰቦች ካሳ እንዲሆን ነበር፡፡
ጀርመን በበኩሏ የ2ኛው የዓለም ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ በቢሊዮን የሚቆጠር ካሳ በጦርነቱ ለተጎዱ አገሮች ስለከፈልኩ ከእንግዲህ ይህን ዓይነት የካሳ ጥያቄ አልመልስም ስትል ሞግታለች፡፡
ጀርመን አሁን የሄግ ፍርድ ቤት ጉዳዩን እንዲመለከተው፣ ከሁሉ በፊት ግን የጣሊያን ፍርድ ቤቶች ሊያሸጧቸው ያሉ ሕንጻዎቿን በአስቸኳይ እንዲያስቆምላት ጠይቃለች፡፡
የሄግ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ዓመታት ያስፈልጉታል፡፡