ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አባላት ከወንዶቹ እኩል እንዲከፈላቸው ከስምምነት ተደረሰ
የዩናይትድ ስቴትስ የሴቶች የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከወንድ ብሔራዊ ቡድን አባላት እኩል እንዲከፈላቸው ከስምምነት ተደረሰ።
ይህ ስምምነት የተደረሰው ከአገሪቱ የእግር ኳስ አስተዳደሪ ጋር በእኩል ክፍያ ዙሪያ ስምምነት ከተደረገ በኋላ ነው።
ስምምነቱን የቡድኑ አጥቂ አሌክስ ሞርጋን "ትልቅ እርምጃ" ስትል ገለጸች።
ተጫዋቾቹ 24 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኙ ሲሆን ዩኤስ ሶከር (የአሜሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን) የዓለም ዋንጫን ጨምሮ በሁሉም የውድድር ዓይነቶች ለሴቶች እና ወንዶች እኩል ክፍያ ለመፈጸም ቃል ገብቷል።
28ቱም የቡድኑ አባላት እአአ የካቲት 2019 አድልዎ ተፈጽሞብናል በሚል ክስ መስርተዋል።
ሞርጋን "ይህ የማይታመን ቀን ነው" ስትል ለጉድ ሞርኒንግ አሜሪካ ገልጻለች።
የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ አክላም "ይህ ዋጋ በመስጠት፣ በመከባበር እና ከዩኤስ ሶከር ጋር የነበረውን ውጥረት ቀንሶ ግንኙነቱን በማስተካከል ረገድ ትልቅ እርምጃ ነው" ብላለች።
"ጉዳዩ ወደፊት መራመዱ መልካም ነው። ይህ ለቡድናችን ወይም በስፖርት ውስጥ ላለን ሴቶች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የሴቶች ድል አድርጌ ነው የማየው።"
ሌላኛዋ የዩናይትድ ስቴትስ የቡድን አጋሯ ሜጋን ራፒኖ "ይህን ቀን ወደ ኋላ መለስ ብለን የምንመለከት ይመስለኛል። ይህንንም የአሜሪካ እግር ኳስ ወደ ተሻለ ሁኔታ የተቀየረበት በዚህ ወቅት ነው እንላለን" ብላለች።
ዩናይትድ ስቴትስ የሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን የዓለም ዋንጫን እአአ በ2019 ለአራተኛ ጊዜ አንስታለች። አምስት ጊዜም የኦሎምፒክ ወርቅ ባለቤት ሆናለች።
ሞርጋን እና ራፒኖን ጨምሮ አምስት የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም ዋንጫ አሸናፊው ቡድን አባላት እአአ በ2016 ፌዴሬሽኑ የደመወዝ መድልዎ ላይ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
የእኩል ክፍያን ምከንያት በማድረግ 66 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ቢጠይቁም በ2020 ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎታል። በኋላም ጉዳዩ ላይ ይግባኝ ቀረበበት።
የአሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መስከረም ላይ የክፍያ አለመግባባት ለመፍታት ለወንዶች እና ለሴቶች ብሔራዊ ቡድኖቹ ተመሳሳይ ውል አቅርቧል።
ዩኤስ ሶከር እና የሴቶቹ ብሔራዊ ቡድን ማክሰኞ በጋራ በሰጡት መግለጫ "ድርድር ላይ በመመስረት በእኩል ክፍያ ላይ ያለንን የቆየ አለመግባባት እንደፈታን እና በእግር ኳስ ውስጥ እኩልነትን ለማስፈን በቁርጠኝነት በጋራ እንደምንቆም ስንገልጽ በደስታ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
አክለውም "ዛሬ ላይ መድረስ ቀላል አልነበረም። የሴቶቹ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ለራሳቸው እና ለቀጣይ ስፖርተኞች ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እኩል ክፍያ ለማግኘት መሥራታቸው ስኬት አስገኝቶላቸዋል።"
"ይህ እንዲሳካ የረዱትን ያለፉት የሴቶቹ ብሔራዊ ቡድን መሪዎች እና የሚከተሏቸውን ሴቶች ሚና እናደንቃለን።"