ቱርክ የምትታወቅበት ስሟ ላይ ለውጥ ልታደርግ ነው

የቱርክ መንግሥት የአገሪቱን ይፋዊ መጠሪያ ስም ወደ ተርኪዬ ሊቀይር ነው።

ቱርክ እስካሁን የምትታወቅበትን "ተርኪ" በሚለው ዓለም አቀፍ መጠሪያዋ ትታወቃለች።

ቱርክ በተለይ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ አገራት ዘንድ አዲሱ ስሟ እንዲሰርጽ #helloTürkiye በሚል መሪ ቃል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና በመደበኛ መገናኛ ብኃን ላይ ዘመቻ ጀምራለች።

በቀጣይ ቀናትም ቱርክ ለተባበሩት መንግሥታት የስም ለውጡን በማስመልከት ማመልከቻ እንደምታስገባ ተጠቁሟል።

ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን አዲሱ የቱርክ መጠሪያ ስም፤ "የቱርክ ሕዝብን ባህል፣ ስልጣኔን እና እሴት የሚወክል እና የሚገልጽ ነው" ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ ይህን ይበሉ እንጂ የቱርክ መንግሥት የአገሪቱን ስያሜ መቀየር ያስፈለገው ቱርክ በእንግሊዘኛው 'ተርኪ' ተብላ ከምትጠራው የዶሮ ዝርያ እራሷን ለመለየት ነው የሚሉ አሉ።

የፎሬን ፖሊሲ ኢንስቲቲዩት ተመራማሪው ሳሊም ኮሩ፤ ፕሬዝደንቱ እና ሌሎች የቱርክ ባለሥልጣናት፤ ቱርክ በስሟ ምክንያት ከዶሮዋ ጋር አብራ መነሳቷ እጅጉን ምቾት ይነሳቸዋል ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም፤ በእንግሊዘኛ የመዝገበ ቃላት 'ተርኪ' የሚለው ቃል፤ 'ሙሉ በሙሉ ያልተሳካ' ወይም 'ውድቀት የሆነ ነገር' የሚል ትርጓሜን ይሰጣል።

ይህም አገሪቱ ለዘመናት የዘለቀውን ስሟን ለመቀየር ያስገደዳት ሌላኛው ምክንያት ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ ቱርክ በጦር መሳሪያ አቅርቦት እና በተከታታይ የቴሌቪዥን ደራማዎቿ የዓለምን ቀልብ ገዝታለች። ይህች በአውሮፓ እና በእስያ አህጉራት መካከል ያለች ጥንታዊት አገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለገጽታ ገንባታዋ ከፍተኛ ትኩረት እንደሰጠች ሳሊም ኮሩ ይናገራሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዚህ ቀደም አፍሪካዊቷ አገር ስዋዚላንድ ስሟን ወደ ኢስዋቲኒ መቀየሯ ይታወሳል። ስዋዚላንድ ስሟን መቀየር ያስፈለጋት ሰዎች ከአውሮፓዊቷ ስዊትዘርላንድ ጋር እያምታቱ ነው በሚል ምክንያት ነው።