ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጣሊያን ውስጥ የተገደለችው ኢትዮጵያዊት ቤተሰብ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ደስተኛ አለመሆናቸውን ገለጹ
አጊቱ ጉደታን በአሰቃቂ ሁኔታ ባለፈው ዓመት በገደለው ግለሰብ ላይ የ20 አመት እስር ተፈረደበት።
ግለሰቡ ሰኞ እለት የካቲት 07/2014 ዓ.ም እንደተፈረደበት የጣሊያን መገናኛ ብዙኃን የዘገቡ ሲሆን በተወሰነው ቅጣት ቤተሰቧ ደስተኛ አለመሆኑን እህቷ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ታዋቂዋ ኢትዮጵያዊት አጊቱ ጉደታ ከአንድ ዓመት በፊት ጣሊያን ውስጥ በቤቷ ውስጥ ሳለች ነው በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችው።
የፍርድ ቤት ውሳኔውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ የምትገኘው የአጊቱ እህት ሀወኒ ኤዳዎ ጉደታ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ፍርድ ቤቱ በገዳዩ ላይ ያሳለፈው የእስር ቅጣት በቂ ነው ብሎ አያምንም።
"ምንም እንኳን ቅጣቱ እሷን የሚመልሳት ባይሆንም፣ ከተፈጸመው ወንጀል አኳያ ውሳኔው በቂ አይደለም። እኛ የእድሜ ልክ አስራት ይፈረዳል ብለን ጠብቀን ነበር።"
ሀወኒ ለቢቢሲ እንደገለጸችው ከቤተሰቧ መካከል እዚያው ጣሊያን ሆኖ የፍርድ ሂደቱን የሚከታተል እንደነበረና ኢትዮጵያ ያሉትም ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉት ቆይተዋል። ቢሆንም ግን በመጨረሻ በተሰጠው ውሳኔ ደስተኞች እንዳልሆኑ አመልክታለች።
ወደ ጣሊያን በስደት ከሄደች በኋላ ፍየሎችን በማርባት ተወዳጅ አይብ በማምረት እውቅናን አግኝታ የነበረችው የ42 ዓመቷን አጊቱ ጉደታን ቤቷ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ የገደላት ቀጥራ ታሰራው የነበረ ጋናዊ ነው።
የ33 ዓመቱ ጋናዊ ስደተኛ ሱሌይማን አዳምስ ግድያውን የፈጸመው ከአንድ ዓመት በፊት ሲሆን ከወንጀሉ በኋላ በፖሊስ ተጠርጥሮ ተይዞ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ ነው 20 ዓመት የተፈረደበት።
ጣሊያን ትሬንቶ ውስጥ ጉዳዩን ሲመለከቱ የነበሩት ዳኛ ኤኔሪኮ ቦሬሊ ባሳለፉት ውሳኔ ጋናዊው ሱሌይማን 15 ዓመት ከስምንት ወር ሆን ብሎ ነፍስ በማጥፋት እንዲሁም አራት ዓመት ከአራት ወር ወሲባዊ ጥቃት በመፈጸም እንዲታሰር ተፈርዶበታል።
አጊቱ በጣሊያን
አጊቱ ትኖርበት በነበረው በሰሜናዊ ጣሊያን ትሬንቲኖ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ፍራሲሎንጎ አካባቢ ሊጠፉ ተቃርበው ነበር የተባሉ የፍየል ዝርያዎችን በማርባት ከወተታቸው የተለያዩ ተዋጽኦዎችን እያመረተች ምርቷ ተወዳጅነትን እሷም ታዋቂነትን አትርፋ ነበር።
አዲስ አበባ ውስጥ ተወልዳ ያደገችው አጊቱ ጉደታ ለስደት የተዳረገችው፣ በትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄድ የነበረውን የመሬት ነጠቃ በመቃወም በምትሰጠው አስተያየት፣ የግድያ ዛቻ ይደርሳት ስለነበረ ነው።
አጊቱ ጉደታ ከአስር ዓመት በፊት በመንግሥት የሚደርስባትን ጫና ሸሽታ ወደ ጣሊያን ከገባች በኋላ የስደተኝነት ፈቃድ አግኝታ የእንስሳት እርባታና የወተት ተዋጽኦ ምርት ሥራን በመጀመር በአጭር ጊዜ ስኬታማ በመሆን ለበርካታ ስደተኞች ምሳሌ ለመሆን ችላ ነበር።
በሥራዋ ዝናን ያተረፈችውን የአጊቱን ሞት በተመለከተ በርካታ የጣሊያን ጋዜጦች ጽፈዋል።
ሁሉም አጊቱ በትሬንተን ግዛት ውስጥ ወደ ደረሰችበት ስኬት ለመብቃት ከባድ ፈተናዎችን ማሳለፏን የጠቀሱ ሲሆን፤ ከነበራት ጥንካሬና ቆራጥነት የዘረኝነት አመለካከቶችን ተጋፍጣ በምትኖርበት አካባቢ ተወዳጅነትን እንዳተረፈች ሁሉም መስክረዋል።
አጊቱ በምትሰራው የፍየል እርባታና የወተት ተዋጽኦ ምርት ሥራ ውስጥ ለበርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች የሥራ ዕድል ፈጥራ የነበረ ሲሆን፤ ግድያውን መፈጸሙ ስደተኛም እዚያው ለሦስት ዓመታት ተቀጥሮ መስራቱ ተነግሯል።
አጊቱ እዚያው ጣሊያን ውስጥ ሶሲዮሎጂ ተምራ ዲግሪ ያገኘች ሲሆን በተገደለችበት ዕለት የግብርና ሥራዋን ለማስፋፋት ከቅየሳ ባለሙያዎች ጋር ቀጠሮ ነበራት።