ሴኔጋል ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን ሆነች

ሴኔጋል ግብጽን 4 ለ 2 በመለያ ምት በመርታት የመጀመሪያዋን የአፍሪካ ዋንጫ ለማንሳት በቃች።

ጨዋታው በሁለቱ የሊቨርፑል አጥቂ ሳዲዮ ማኔ እና መሐመድ ሳላህ መካከል የተደረገ ፍልሚያ ተብሎ በብዙዎች በከፍተኛ ጉጉት የተጠበቀ ነበር።

ጨዋታው ያለምንም ጎል በመጠናቀቁ ነበር ወደ መለያ ምት የተሸጋገረው።

ማኔ በሰባተኛው ደቂቃ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

የቼልሲው የግብ ዘብ ኤዱዋርድ ሜንዲ በበኩሉ በመለያ ምቱ ወቅት ሞኢሃናደድ ላሺን ኳስ አድኖ ለቡድኑን አሸናፊነት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

የፈርንኦቹ ግብ ጠባቂ ጋባስኪም ድንቅ ሆኖ አምሽቷል።

ሴኔጋል ከዚህ ቀደም በሁለት የፍጻሜ ጨዋታዎች ከተሸነፈች በኋላ በመጨረሻም የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ለመሆን በቅታለች። ግብጽ ውድድሩን በማሸነፍ ክብረወሰኗን ወደ ስምንት የምታሳድግበትን ዕድል ሳትጠቀም ቀርታለች።

የሴኔጋሉ አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ "ጠንክረህና ጸንተህ ከሠራህ የምትፈልገውን እንደምታገኝ ያሳያል" ሲሉ ድሉን ገልጸውታል።

"በጣም ስሜታዊ ሆኛለሁ ምክንያቱም የሴኔጋል ህዝብ ይህን ዋንጫ ለ60 ዓመታት ናፍቋል" ብለዋል አሰልጣኙ።

በውድድሩ ላይ አራቱም የግብጽ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ወደ ተጨማሪ ሰዓት ተሸጋግረዋል። ፈርኦኖቹ አይቮሪኮስትን እና አስተናጋጇ ካሜሩንን በመለያ ምት አሸንፈው ነበር ለፍጻሜው የደረሱት።

ጨዋታው ወደ መለያ ምት ከመሸጋገሩ በፊት ጋባስኪ ቀደም ሲል በውድድሩ ላይ አራት መለያ ምቶችን አድኖ ነበር።

ግብጻዊው ተከላካይ መሀመድ አብደልሞኔ መለያ ሳይጠቀምበት የቀረ ሲሆን በፍጥነት ጋባስኪ የቡና ሳርን ኳስ ለመዳን ችሎ ነበር።

የላሺን መለያ ምት በሜንዲ ሲድን የመጨረሻዋን ኳስ ማኔ አስቆጥሮ ለዋንጫ ሴኔጋሎች ዋንጫውን አንስተዋል።

የሊቨርፑል የቡድን አጋሩ ሳላህ አምስተኛ መቺ በመደረጉ የመለያ ምቱን እንኳን ለመምታት ዕድል አላገኘም።

ሴኔጋል በፈረንጆቹ 2002 እና 2019 ለፍጻሜ ቀርባ ተሽንፋለች።

ሳላህ በሴኔጋል ተከላካዮች ቁጥጥር ስር ባመሸበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ሙከራዎችን አድርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ ፈርኦኖቹ ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ሙከራ ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጭማሪው ሰዓት ሞቅ ብሎ ተከናውኗል።

በመጨረሻም ድሉ ላለፉት ሦስት ዓመታት የአፍሪካን የሃገራት ደረጃ ለመራችው ሴኔጋል ሆኗል።

አሰልጣኝ አልዩ ሲሴም በተጫዋችነት በ2002 ወሳኟን የመለያ ምት ከሳቱ እና ከሦስት ዓመት በፊት በፍጻሜው ከተሸነፉ በኋላ ያገኙት ድል ሆኖ ተመዝግቧል።

ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ከአንድ ዓመት በኋላ በአይቮሪ ኮስት ይከናወናል።

ሁለቱ ቡድኖች በሚቀጥለው ወር ለኳታር የዓለም ዋንጫ ለማነፍ በድጋሚ ተገናኝተው በደርሶ መልስ ስለሚጫወቱ ግብጽ በቅርቡ የመበቀል ዕድል ይኖራታል።