ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አይኤስ በካምፓላ ለደረሱት ጥቃቶች ኃላፊነት ወሰደ
ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ለደረሱት ጥቃቶች ኃላፊነቱን እንደሚወሰድ አስታወቀ።
አይኤስ በቴሌግራም ገጹ ይፋ እንዳደረገው በፍንዳታዎቹ ምክንያት ከ30 በላይ ሰዎች ሟች እና ቁስለኛ ሆነዋል።
የአይኤስ "የዜና ወኪል" አማቅ እንዳስታወቀው በማዕከላዊ አፍሪካ ከአይኤስ ተዋጊዎች ጋር ጦርነት ከገጠሙ አገራት መካከል ኡጋንዳ አንዷ ናት። በዚህም ምክንያት አገሪቱን ኢላማቸው ስለማድረጋቸው አስታውቋል።
ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ በኡጋንዳ ለደረሱት ጥቃቶች አይኤስ ኃላፊነት ሲወሰድ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።
በካምፓላ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ተከትሎ ኬንያ የጸጥታ መዋቅሯ በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኝ አስታውቃለች።
የመንግሥት ቃል አቀባይ ሳይረስ ኦጉና ዜጎች ንቁ ሆነው የሚያጠራጥሩ ጉዳዮችን ሪፖርት እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በካምፓላ ትናንት ማክሰኞ ጠዋት የፖሊስ ጣቢያ የፍተሻ ስፍራ እና በአገሪቱ ፓርላማ አቅራቢያ በደረሱ ፍንዳታዎች ሦስት ሲቪሎች ተገድለዋል። ሦስት አጥፍቶ ጠፊዎች መሞታቸውንም ኦፊሴላዊው መረጃ አስታውቋል።
በፍንዳታው ምክንያት ከሰዓት በኋላ ሊሰበሰብ የነበረው ፓርላማ የተበተነ ሲሆን ህንጻው በአነፍናፊ ውሾች እንዲፈተሽ ተደርጓል።
ከ30 በላይ ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን አንዳንዶቹ አሁንም ህክምናቸውን በሆስፒታል በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
ፖሊስ አራተኛ አጥፎፍቶ ጠፊን በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና ፈንጂውን መያዙን አስታወቋል።
የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በተከታታይ በትዊተር ገጻቸው ላይ ድርጊቱን አውግዘው ጥቃቱ "ግራ በገባቸው ሰዎች" የተፈጸመ ነው ብለዋል።
አክልውም አሸባሪዎቹ ባለፈው ሰኔ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ጄነራል ካቱምባ ዋማለን ሲያጠቁ ራሳቸውን አጋልጠዋል ሲሉ ገልጸዋል። በጥቃቱ የጄነራሉ ሴት ልጅ እና አሽከርካሪ ሕይወታቸው አልፏል።
ከዚያ ወዲህ ሰባት ተጠርጣሪ አሸባሪዎች እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሲገደሉ ከ80 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።
የኡጋንዳ ፖሊስ ጥቃቱ መቀመጫውን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባደረገው በአላይድ ዲሞክራቲክ ፎርስስ (ኤዲኤፍ) የደረሰ ነው ብሎ ነበር። ኤዲኤፍ አይኤስን እንደሚደግፍ ይገለጻል።