ብሊንከን በአፍሪካ ጉዟቸው ከኬንያው ፕሬዝደንት ጋር ስለ ኢትዮጵያ እንደሚመክሩ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ አፍሪካ አገራት በሚያደርጉት ጉዞ ከኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ተገናኝተው ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሚመክሩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታወቀ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መረጃ መሠረት፤ ብሊንከን ከሦስት ቀናት በኋላ (ከሰኞ ኅዳር 06/2014 ዓ.ም ጀምሮ) ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ሴኔጋልን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።
ከኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲሁም ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ራይቼሌ ኦማሞ ጋር ሲገናኙ ስለ ኢትዮጵያ የፀጥታ ጉዳይ እንደሚወያዩ ተጠቁሟል።
ከኢትዮጵያ ጉዳይ በተጨማሪ ስለ ሶማሊያ እና ሱዳን እንዲሁም በአጠቃላይ የቀጠናው ጉዳይ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉም ተገልጿል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከጉዟቸው በፊት ዋሽንግተን ውስጥ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት የሚቀጥል ከሆነ ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት እንዳለቸው ገልጸዋል።
"ግጭቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ከባድ ነውጥን በመፍጠር በሕዝቡ ላይ ከባድ አደጋን ሊያስከትልና በአካባቢው ወዳሉ አገራት ሊስፋፋ ይችላል" ብለዋል።
ሌላኛው መንገድ ደግሞ ተኩስ አቁምና ድርድር መሆኑን በመግለጽም አገራቸው አሜሪካ የአፍሪካ ሕብረቱ የሽምግልና መልዕክተኛ የሆኑትን ኦባሳንጆን እየደገፈች መሆኗን ብሊንከን ተናግረዋል።
ብሊንከን ሦስቱን አገራት ሲጎበኙ፤ ሰላምና ደኅንነትን ስለማስጠበቅ እንዲሁም ዴሞክራሲን ስለማስፈን ውይይት እንደሚያደርጉ ተነግሯል።
በተጨማሪም የአሜሪካ እና የአፍሪካ የጋራ ጉዳዮች በሆኑት የኮሮናቫይረስ ወረርሽን መግታት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ማሸነፍ እና አካታች ዓለም አቀፍ ምጣኔ ሀብት መገንባትን በተመለከተ ከሦስቱ አገራት ጋር ይወያያሉ ተብሏል።
ብሊንከን ጉብኝታቸውን የሚጀምሩት በኬንያ ሲሆን ከፕሬዝደንት ኬንያታ ጋር ሲገናኙ "የሁለታችንም አገሮች የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ስለሆንን በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ እንመክራለን" ብለዋል።
የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት በተፋፋመበት በዚህ ወቅት የአፍሪካ ሕብረት እና የመንግሥታቱ ድርጅትም በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት አማጽያን መካከል ሰላማዊ የድርድር መንገድ ለመክፈት ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
ጦርነቱ "በዲፕሎማሲ መንገድ ይቆማል" ብላ እንደምታምን አሜሪካ ከሰሞኑ መግለጿ ይታወሳል።
የብሊንከን ጉብኝት
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ፤ ኬንያ በቀጣይ ዓመት ለምታደርገው ብሔራዊ ምርጫ አሜሪካ ስለምታደርገው ድጋፍ ከፕሬዝዳንት ኬንያታ ጋር ውይይት ይካሄዳል።
"ምርጫው ሰላማዊ እና አካታች እንዲሆን አሜሪካ ድጋፍ ትሰጣለች" ተብሏል።
ከኬንያ ቀጥሎ ከናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሀሪ እንዲሁም ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የሚገናኙት ብሊንከን፤ ስለ ዓለም አቀፍ የጤና ትስስር፣ ታዳሽ ኃይልን ማስፋፋት እና ዴሞክራሲን ስለማስፈን ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ብሊንከን በጉብኝታቸው ወቅት "የአፍሪካ ትልቋ የዴሞክራሲ መቀመጫ በሆነችው ናይጄሪያ ስለ አሜሪካ እና አፍሪካ የጋራ ፖሊሲ ንግግር ያደርጋሉ" ተብሏል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉብኝታቸውን የሚያጠናቅቁት በሴኔጋል ነው።
ከፕሬዝዳንት ማኪ ሳል እና ሌሎችም የአገሪቱ አመራሮች ጋር ስለ ንግድ እና ስለ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ይወያያሉ ተብሏል።
ፕሬዘዳንቱ ቀጣዩ የአፍሪካ ሕብረት መሪ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት "የጋራ ጉዳዮችን እና ቀጠናዊ አጀንዳዎችን እናነሳለን" ብለዋል።
ብሊንከን ባለፈው ዓመት ከናይጄሪያ እና ከኬንያ መሪዎች ጋር "ቨርችዋል ቱር ቱ አፍሪካ" በሚል በበይነ መረብ ውይይት ማድረጋቸው አይዘነጋም።












