አሜሪካ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በዲፕሎማሲ እንደሚቆም ተስፋዋን ገለጸች

የትግራይ ኃይሎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አንድ ዓመት ያስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም ዲፕሎማሲ እንደሚሰራ ተስፋ እንዳላቸው ገለጹ።

ብሊንከን ከአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ከሆኑት ከቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እንዲሁም ከአሜሪካ የቀጣናው ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ጋር መገናኘታቸውን ተናግረዋል።

"ፕሬዚዳንት ኦባሳንጆ እየተሳተፉበት ባለው ጠቃሚ ሥራ እንዲሁም እኛም ሆነ ሌሎች እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት ጋር ተያይዞ ወደተሻለ ቦታ ሊደረስበት የሚችል የዕድል መስኮት እንዳለ ተስፋ እናደርጋለን" በማለት ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።

አንቶኒ ብሊንከን ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር መነጋገራቸውንና "ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ጦርነቱን ለማስቆም በቁም ነገር መደራደር" እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተዋል።

በጦርነቱ ከሁለቱም ወገኖች የሚሰሙት ቃላቶች በማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ውጥረት ሊያባብሱ እንደሚችሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የተኩስ አቁም ድርድሩ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን እንዲሁም ለወደፊቱ "ዘላቂ የሆነ ፖለቲካዊ መፍትሄ ላይ ለመድረስ ያስችላል" የሚል ተስፋም እንዳላቸው አስረድተዋል።

አንቶኒ ብሊንከን ይህንን ያሉት በቅርቡ የትግራይ አማፂ ኃይሎች ወደ መዲናዋ እያደረጉት ያለውን ግስጋሴ ተከትሎ ነው።

መንግሥት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዲደራጁና አካባቢያቸውንም እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርቧል።

ከሰሞኑ በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው አንድ ዓመት ያስቆጠረው ደም አፋሳሽ ጦርነትን ለማርገብ በተጠራው የፀጥታው ምክር ቤት ጉባዔ የአፍሪካ ሕብረት እያደረገ ላለው የሰላም ተነሳሽነት ድጋፍ ሰጥቷል።

ይህ ድጋፍ የተሰጠው ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና ከትግራይ አመራሮች ጋር ድርድሩን አስመልክቶ የነበረው ውይይት በበጎ መልኩ ተቀባይነት ማግኘቱን ከገለጹ በኋላ ነው።

ጥቅምት 29/2014 ዓ.ም በነበረው የፀጥታው ምክር ቤት ጉባዔ፣ የአባል አገራት ተወካዮች ለሕብረቱ ድጋፍ ከመለገስ በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና የትግራይ ኃይሎች የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ፣ ያልተደናቀፈ ሰብዓዊ አገልግሎት እንዲደርስና እና አገሪቱን ከቀውስ ለመታደግ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲገኝ ጠይቀዋል።