በትግራይ የሰብዓዊ ቀውሱ እየተባባሰ ነው - የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መምጣቱንና እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል።

በመላው ትግራይ፣ አማራ እና አፋር እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እና የሌሎች እርዳታ ፈላጊዎች መሆናቸውንም በትናትናው ዕለት ኃላፊው ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረእየሱስ አስረድተዋል።

አስራ አንድ ወራት ባለፈው ጦርነት ስድስት ሚሊዮን የሚሆን የትግራይ ህዝብ ለችግር እንደተጋለጠና በክልሉም ለአንድ ዓመት ያህል ክልከላ በመጣሉ መብራት፣ ባንክ እና ቴሌኮምን ጨምሮ መሰረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል ብለዋል።

በክልሉ ያለው ያለው የሰብዓዊ ቀውስ እየተባባሰ በመሄዱም የምግብ እና የመድኃኒት እጥረት በተጎዱ አካባቢዎች ሥር የሰደደ በሽታ ላለባቸው ሰዎች ሞት ምክንያት እየሆነ ነው ብለዋል።

በክልሉ የጤና ተቋማት መውደም እንዲሁም ከተጣለው እገዳ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የመድኃኒትና ህክምና አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙንም የትግራይ ተወላጅ የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አስረድተዋል።

በተለይም ከሐምሌ ወር ጀምሮ ምንም ዓይነት የመድኃኒትና ህክምና አቅርቦት ወደ ክልሉ እንዲገባ ባለመፈቀዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶች እንዳይኖራቸው አድርጓል ብለዋል።

በክልሉ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ የምግብ ዕርዳታ እንደሚፈልግና እስከ 400 ሺህ የሚደርሱ ነዋሪዎች በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውንም ኃላፊው የተባበሩት መንግሥታትን መረጃን ዋቢ አድርገው ጠቅሰዋል።

ከአስር አመት በፊት በሶማሊያ ረሃብ ላይ የታየው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ደረጃ ላይ መድረሱንም ዶክተር ቴድሮስ አክለዋል።

የኮሚዩኒኬሽን መቋረጥ የሚያስፈልገውን የእርዳታ መጠን ለመገምገም አስቸጋሪ አድርጎታል ሲሉ የተናገሩት ኃላፊው በተለይም ጦርነቱ ወደ አጎራባቾቹ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋት የእርዳታ ፈላጊውን ህዝብ ጨምሮታል እንዲሁም የእርዳታ ጥረቶችንም አወሳስቦታል ብለዋል።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሌሎች ተቋማትም የዓለም ጤና ድርጅትም ተጎጂ ለሆኑ አካባቢዎች ያልተገደበ ተደራሽነት እንዲኖር ጥሪውን አቅርቧል።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በህወሃት ስር ባሉ አማራ ክልል አካባቢዎችና በትግራይ- አፋር ድንበር ጦርነቱ የተጋጋለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጥሪው ምን ያህል ተፅእኖ እንደሚያሳድር ማየት አስቸጋሪ ነው።