ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ቀውስ ምላሽ ለመስጠት አማራጮችን እያየሁ ነው አለች
ዩናይትድ ስቴትስ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተባባሰ ላለው ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የኢኮኖሚ ማዕቀብን መጣልን ጨምሮ ያሏትን አማራጮች እየተመለከተች መሆኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ለጋዜጠኞች ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን እና የአውሮፓ ሕብረት ባለስልጣናት ማክሰኞ በኢትዮጵያ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
በዚህ ስብሰባ ላይ የግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነትን አድርገው ወደ ድርድር እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ የምዕራባውያኑ ጥሪ የተሰማው የኢትዮጵያ ጦር በትግራይ ኃይሎች ላይ በሁሉም ግንባሮች የተቀናጀ ጥቃት መክፈቱን አማጺያኑ ከገለጹ በኋላ ነው።
በሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል የተከሰተው ጦርነት በድርድር እንዲቆም ዋሽንግተን ተደጋጋሚ ጥሪ ስታቀርብ ቆይታለች።
በተያያዘ ዜና የቡድን 7 አባል ሃገራት እና ሌሎች ለጋሽ ሃገራት በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) አስታውቋል።
ተሳታፊዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጭዎች እና ዓለም አቀፍ ለጋሾችን ለሚያጋጥማቸው ውስብስብ ችግሮች ፈጣን መፍትሔዎችን ለመፈለግ እና እነዚህን ተግዳሮቶች ለማለፍ የተለያዩ ዘዴዎችን ከግምት ማስገባት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል ብሏል ድርጅቱ።
ተሳታፊዎች በመጪው የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ስብሰባ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት በግጭቱ የሚሳተፉ አካላት ወደ ፖለቲካዊ ድርድር እንዲሸጋገሩ ከስምምነት መድረስ አስፈላጊነት ላይ ተወያይተዋል።
"ዩናይትድ ስቴትስ እና ለጋሽ አጋሮቻችን የሰብዓዊ ሠራተኞችን ላይ የሚደርሰው ጥቃት እና ዜጎች እያጋጠማቸው ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ የተሳሳተ መረጃ መስፋፋታቸውን አውግዘዋል። የግጭቱ ተሳታፊዎች በእርዳታ ሠራተኞች ላይ የሚደርሰው ትንኮሳ እና ማስፈራራት እንዲቆምም ጠይቀዋል" ይላል የዩኤስኤይድ መግለጫ።
ለጋሾች በትግራይ የመገናኛ፣ የባንክ እና ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ እና ወደ ትግራይ የሚወስዱ የትራንስፖርት ኮሪደሮች እና የአየር ጉዞ ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት እንዲመለስ መስማማታቸውን አስታውቋል።
"ይህም ባለፉት ሁለት ወራት በመንግሥት የታገደው ነዳጅ፣ መድኃኒቶች እና የህክምና አቅርቦቶችን ወደ ክልሉ እንዲገባ መፍቀድን ያጠቃልላል" ብሏል።
በዚህ ረገድ አፋጣኝ ለውጦች ካልተደረጉ የሰብዓዊ ድርጅቶች ሥራቸውን ለመገደብ ወይም ለማቆም እንደሚገደዱ አስታውቋል። የጤና ተቋማትም ከህክምና አቅርቦት ውጭ ይሆናሉ ብሏል።
መጠነ ሰፊ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት እና ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎችን ጨምሮ ለደረሱ ጥቃቶች ተሳታፊዎች የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርቡ በጋራ በሚያቀርቡት ሪፖርት እና ምክረ ሃሳብ መሠረት አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።
አንድ ዓመት ሊደፍን የተቃረበው ግጭት ከስድስት እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ለከባድ የምግብ ዋስትና ችግር አጋልጧቸዋል ያለው ዩኤስአይድ፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ብሏል።
በትግራይ እስከ 900,000 የሚደርሱ ሰዎች ረሃብን የመሰለ ሁኔታ እያጋጠማቸው ሲሆን፣ ሰዎች ምግብ ሳያገኙ ለቀናት በመቆየታቸው ቅጠል መብላት ጀምረዋል ሲል አስታውቋል።