አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ዩኬ በትግራይ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ አካላት በፍጥነት ወደ ድርድር እንዲገቡ ጥሪ አቀረቡ

ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ዩናይትድ ኪንግደም ኢትዮጵያ ውስጥ በትግራይ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ አካላት በፍጥነት ወደ ድርድር እንዲገቡ ጥሪ አቀረቡ።

ይህንን ይፋ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ ናቸው።

ቃል አቀባዩ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ የአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ፣ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ጨምሮ ከፍተኛ የአሜሪካ፣ የአውሮፓና የአፍሪካ ባለሥልጣናት የተገኙበት ስብሰባ እንዳካሄዱ ተናግረዋል።

የወቅቱ የኢጋድ ሊቀ-መንበርና የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ፣ የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል፣ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ጸሐፊ፣ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የፈረንሳይ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ውይይቱን መታደማቸውን ኔድ ፕራይስ አሳውቀዋል።

የውይይቱ ታዳሚዎች የግጭቱ ተሳታፊዎች በአፋጣኝ ሁሉን አካታች ወደ ሆነ ውይይት አምርተው ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲያሰፍኑ እና የሃገሪቱን ደህንነት እንዲጠብቁ ጥሪ አስተላልፈዋል ብለዋል ቃል አቀባዩ።

አልፎም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ዓለም አቀፍ ሕግን አክብረው የሰብዓዊ እርዳታ ያለ ምንም ገደብ ስቃይ ውስጥ ላሉ ኢትዮጵያዊያን እንዲደርስ ይፍቀዱ ማለታቸውን ኔድ ፕራይስ አሳውቀዋል።

የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የአፍሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ካካሄዱት ስብሰባ በፊት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ከአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ ጋር በኢትዮጵያ ጉዳይ መወያየታቸውም ተሰምቷል።

"ለድርድር ዝግጁ ነን"

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተባባሩት መንግሥታት የቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት እና በአሁኑ ወቅት የህወሓት ቃል አቀባይ ፍሰሃ አስግዶም ህወሓት ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

"ይህ ጠረቤዛ ዙሪያ መቋጨት ያለበት ጦርነት ነው። ለድርድር ዝግጁ ነን" ሲሉ የህወሓት ቃል አቀባይ አምባሳደር ፍሰሃ አስግዶም ለቢቢሲ የእንግሊዘኛው ክፍል ተናግረዋል።

አምባሳደር ፍሰሃ የፌደራሉ መንግሥት በተደጋጋሚ የድርድር ጥያቄዎችን ውድቅ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ጭምረውም ሁለቱ አካላት ወደ ድርድር ለመምጣት ከተስማሙ ማን ያደራድረናል የሚለው "ለእኛ ሁለተኛው ጉዳይ ነው" ብለዋል።

"ይህን መሰል ጦርነት ለአንድ ቀንም በኢትዮጵያ መቀጠል የለበትም። . . . ዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ ጦርነቱን ከማውገዝ እና ድርድር እንዲደረግ ከመጠየቅ ባለፈ ተጨባጭ የሆነ እርምጃ እንዲወስድ እንፈልጋለን" ብለዋል አምባሳደሩ።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ውጊያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያፈናቀለ ከመሆኑ በተጨማሪ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ለረሃብ እንዳጋለጠ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

መንግሥት ወደ ክልሉ እርዳታ እንዳይገባ እንቅፋት ፈጥሯል እየተባለ የሚወቀስ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ክሱን አይቀበለውም።

የፌደራሉ ሠራዊት በሰኔ ወር ላይ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ የህወሓት አማጺያን ኃይሎች በመልሶ ማጥቃት ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልል ገብተው የተለያዩ ስፍራዎችን ተቆጣጥረው ይዘዋል።

በዚህም ሳቢያ በሁለቱም ክልሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀያቸው ለመፈናቀል የተገደዱ ሲሆን 1.7 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የምግብ እርዳታን ለመጠበቅ ተገደዋል።

በሕወሓት አማፂያንና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ያለው ጦርነት ለጥቂት ሳምንታት የተቀዛቀዘ መስሎ ቢቆይም ከሰሞኑ አማፂያኑ መንግሥት ጥቃት ከፍቶብናል ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።

ህወሓት በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች እየተሰነዘረበት ያለው ጥቃት "በከባድ ጦር መሳሪያ፣ በታንክ፣ በሮኬቶች፣ በድሮኖች እና በተዋጊ ጀቶች" የታገዘ እንደሆነ በመግለጫው አመልክቷል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት የፌደራሉ መንግሥት በህወሓት ኃይሎች ላይ "ከባድ" የተባለ ጥቃት በአማራ እና አፋር ክልሎች በሚገኙ ግንባሮች እየፈጸመ እንደሆነ ሲዘገብ ቆይቷል።

ወታደራዊ ጥቃት መከፈቱን በተመለከተ የተጠየቁት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም በሰጡት ምላሽ፣ መንግሥት በመላው አገሪቱ ዜጎችን ከሽብር ድርጊቶች የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት ከማለት ውጪ ተጨማሪ ዝርዝር ከመስጠት መቆጠባቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።