ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ምግብ ድርጅት በአማራ እና አፋር የመጀመሪያ ዙር የምግብ ስርጭት አድርሻለሁ አለ
የዓለም የምግብ ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ በተስፋፋው ግጭት በአማራ እና አፋር ክልሎች ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የመጀመሪያው ዙር የምግብ ስርጭት ማጠናቀቁን አስታወቀ።
በትግራይ ክልል ግን የሰብዓዊ ዕርዳታው እንቅስቃሴ ላይ ባጋጠሙ የተለያዩ መሰናክሎች እርዳታ የማቅረቡ ሂደት ወደ ኋላ ቀርቷል ብሏል።
የዓለም የምግብ ድርጅት ቃል አቀባይ ቶምሰን ፊሪ፤ በመላው ሰሜን ኢትዮጵያ አስከፊ የሆነ የሰብዓዊ ጥፋት ከመድረሱ በፊት ለተጎጂዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንድናደርስ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ ትብብር እና ድጋፍ ማግኘታችን በጣም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
"በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል። 5.2 ሚሊዮን የሚሆኑት በትግራይ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ይገኛሉ"ሲሉ በጄኔቫ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
እንደ የኢትዮጵያ መንግሥት ግምት ከሆነ በግጭቱ ምክንያት በአማራ እና አፋር ክልሎች ከ840,000 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ መካከል 700 ሺህ ገደማ በአማራ እንዲሁም ወደ 140 የሚጠጉት በአፋር ክልል መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ከነሐሴ 9 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የዓለም የምግብ ድርጅት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ወደ 300,000 ለሚጠጉ ሰዎች ምግብ ማድረሱን እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ እና በደቡባዊ ትግራይ ወደ 2.5 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች ዕርዳታ ማድረሳቸውን ቃል አቀባዩ ፊሪ ተናግረዋል።
በቀጣይ ዙር በሦስቱ ክልሎች በአጠቃላይ ለ3.5 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ ለማድረስ ታቅዷል። በትግራይ 2.7 ሚሊዮን፣ በአማራ 210 ሺህ እና በአፋር እስከ 540 ሺህ ሰዎች በቀጣዩ ስርጭት ለመድረስ ታስቧል።
ፊሪ በሰኔ ወር የምግብ ዋስትናን አስከፊነት የሚገመግመው የተቀናጀ የደረጃ ምደባ (አይ.ፒ.ሲ) በትግራይ ክልል እስከ 400 ሺህ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ረሃብ መሰል ሁኔታዎች እንደሚገጥማቸው አመልክቷል።
"ከሦስቱም ክልሎች የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የምግብ ዋስትና እጦት እየጨመረ ነው" ብለዋል።
በትግራይ ያለው የምግብ ሁኔታ "ከእጅ ወደ አፍ" ሆኖ መቀጠሉንና "የተሽከርካሪዎችን ነፃ እንቅስቃሴ የሚያውኩ ብዙ ጉዳዮች" እንዳሉም ተናግረዋል።
እንደ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ገለፃ አዎንታዊ ዜናም አለ። "ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የደህንነት ጉዳዮች በብዛት ተፈተዋል። 171 የጭነት መኪናዎች ከነሐሴ 5- መስከረም 19 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ትግራይ ገብተዋል" ብለዋል።
ተሽከርካሪዎቹ 6,150 ሜትሪክ ቶን ምግብ እና ተጨማሪ ምግቦችን ይዘዋል። ይህም ለአንድ ወር ያክል ከ 360,000 በላይ ሰዎችን ለመመገብ በቂ ነው ተብሏል።
ፊሪ እንደገለፁት የጭነት አቅርቦትን ካደናቀፉት አንዱና ትልቁ የንግድ መኪናዎች ከትግራይ መመለስ አለመቻላቸው ነው።
የዓለም ምግብ ድርጅት የጭነት መኪኖቹ እንዳይመለሱ የሚያደርጓቸውን ማናቸውም ችግሮች ለመቅረፍከ ከአጓጓዦቹ ጋር መሥራቱን ቀጥሏል ብለዋል። በቅርቡ "ከትግራይ ወጥተው አሁን ወደ ክልሉ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማንቀሳቀስ የሚረዱ ከ90 በላይ የጭነት መኪናዎች አሉ" ብለዋል።
"በየቀኑ ለ210 ሺህ ሰዎች እህል፣ ጥራጥሬ እና የአትክልት ዘይት ለማቅረብ 100 የጭነት መኪናዎች መድረስ አለባቸው" ብለዋል።
ፊሪ አክለውም የዓለም የምግብ ድርጅት 90 የጭነት መኪናዎች ከትግራይ እንዲወጡ በማድረግ ስኬታማ ቢሆንም "የነዳጅ ክምችት በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ነው" ብለዋል።
ሥራው እንዲቀጥል እና የሰብዓዊ ዕርዳታው ወደ አካባቢው እንዲያቀና ነዳጅ በጣም አስፈላጊ መሆኑን በማስታወስ፤ የዓለም ምግብ ድርጅት ወደ ትግራይ ለመድረስ በየሳምንቱ 200 ሺህ ሊትር ነዳጅ እንደሚያስፈልግው ገልጸዋል።
የዓለም ምግብ ድርጅት በመላው ኢትዮጵያ እአአ በ2021 ብቻ 11.9 ሚሊዮን ሰዎችን በምግብ እና በገንዘብ ድጋፍ ደርሶ ማህበረሰቦች የምግብ ዋስትናቸውን አንዲያሳድጉ የማድረግ ዓላማ አለው።
ሆኖም የዓለም የምግብ ድርጅት ከሃብት አንፃር ተግዳሮቶች እንደተጋረጡበት ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። "በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገውን ድጋፍ ለማስቀጠል 184 ሚሊዮን ዶላር እንፈልጋለን" ብለዋል።
የዓለም የምግብ ድርጅት ቃል አቀባይ በሃገሪቱ ያሉትን እንቅስቃሴዎቹ ለማስፈጸም 426 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ እጥረት አለበት። "በወቅቱ ድጋፍ መስጠታችንን እንድንቀጥል ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እና ለዘላቂ የተደራሽነት መንገድ እንዲኖር መጠየቁን እንቀጥላለን" ሲሉ አስረድተዋል።