አይኦኤም ለ1.8 ሚሊዮን ተፈናቃዮች መጠለያ ለመስጠት 21.1 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል አለ

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ኢትዮጵያ ውስጥ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ 1.8 ሚሊዮን ሰዎች መጠለያ ለማቅረብ 21.1 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ይፋ አደረገ።

ከትግራይ፣ አማራ እና ሶማሌ ክልሎች የተፈናቀሉ እና በአሁኑ ወቅት በመጠለያ ጣቢያዎች እንዲሁም በሰዎች ቤት ተጠግተው ለሚኖሩ ዜጎች መጠለያ ለማዘጋጀት የሚያስፈገው ወጪ 21.1 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የተፈናቀሉ ከ233 ሺህ በላይ ሰዎች በ53 መጠለያዎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል።

እነዚህ መጠለያዎች ከዚህ ቀደም ትምህርት ቤት የነበሩ ሲሆኑ አሁን ወደ ተፈናቃዮች ማቆያነት ተለውጠው አገልግሎት እየሰጡ ነው።

አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ሜዳ ላይ ለመተኛት መገደዳቸውን የአይኦኤም ኢትዮጵያ መረጃ ይጠቁማል።

በመጠለያ ጣቢያዎቹ ምግብ፣ ውሃ፣ የህክምና አገልግሎት እና ሌሎችም መሠረታዊ አቅርቦቶች ለማሟላት የሚውለው በጀት እየተገባደደ እንደሚገኝ ድርጅቱ አክሏል።

ለተፈናቃዮቹ የጋራ መጠለያ፣ መጸዳጃ ቤት፣ ኩሽና እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት መስጫ ክፍሎችንም ለመገንባት ድርጅቱ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው በመግለጫው አስታውቋል።

ድርጅቱ የሚያስፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ ካገኘ ለተፈናቃዮቹ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡ መጠለያዎች መገንባት እንደሚችል ተገልጿል።

የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄውን በዋነኛነት የሚመራው አይኦኤም ኢትዮጵያ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) እና የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲም ለተፈናቃዮች ድጋፍ በመስጠት ላይ ናቸው።

በመላው ኢትዮጵያ ከ1500 በላይ የተፈናቃዮች ካምፖች የሚያስተዳድሩ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል 300 መጠለያዎች በሰሜን ኢትዮጵያ ነው የሚገኙት።

በትግራይ ክልል በጦርንት ሳቢያ የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ሲጨምር ካምፕ ኮርድኔሽን ኤንድ ካምፕ ማኔጅመንት ክላስተር (ሲሲሲኤም) በተባለ ክፍል ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል።

የዚህ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት ራፋኤል አቢስ እንደሚሉት፤ አሁንም ግጭቱ በመቀጠሉ ምክንያት አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ወደ ቤት ንብረታቸው መመለስ አልቻሉም።

አያይዘውም "ትምህርት ቤቶቹን ወደ ቀደመ አገልግሎታቸው እንመልሳቸው ብንል እንኳን ለተፈናቃዮቹ ሌላ መጠለያ ማዘጋጀት አለብን። ይህ ደግሞ ተጨማሪ ወጪ ይጠይቃል" ብለዋል።

ሐምሌ ላይ አይኦኤም ወደ 70 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲደረግለት ጠይቆ እስካሁን ያገኘው 31.7 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።

ለሲሲሲኤም ክፍል የሚውል አራት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ጠይቆ ደግሞ እስካሁን ማሟላት የቻለው 3.8 ሚሊዮን ነው።

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ መሠረት፤ ይህ ዓመት እስኪጠናቀቅ ድረስ ለተፈናቃዮች መጠለያ ለመሥራት 21.1 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያስፈልገዋል።

በአይኦኤም ኢትዮጵያ የሲሲሲኤም የፕሮግራም ማናጀር የሆኑት ስቲፋኒን ኒክ ዮምሂርድ "ይህ ገንዘብ ለተፈናቃዮቹ የተሟላ መጠለያ ለመሥራት ያስፈልገናል። ድጋፍ ካላገኘን ተፈናቃዮቹ ወደከፋ ሁኔታ ይገባሉ" ብለዋል።