የኢቢሲን የፌስቡክ ገጽ ሰብሮ የገባው ማን ሊሆን ይችላል?

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) ሰኞ ዕለት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዓለ ሲመት በፌስቡክ ገፁ በቀጥታ እያስተላለፈ ባለበት ወቅት፣ ከተቋሙ ውጪ የሆነ መረጃ ያጋሩ አካላትን ለመለየት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (INSA) እየሰራ መሆኑን ለቢቢሲ ገለፀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) በድርጊቱ ላይ ስለተሳተፉ አካላት "በአብዛኛው የሚታሰበው ከውስጥ አሻጥር (ሳቦታጅ) ይኖራል ተብሎ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) መስከረም 24/2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዓለ ሲመት ዕለት የኢቢሲን የፌስቡክ ገጽ ለመጥለፍ ከውጪ የሚመጡ የሳይበር ጥቃት ዕድሎች "ሙሉ በሙሉ የተዘጉ ነበሩ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢቢሲ የፌስቡክ ገጽ ሰኞ ዕለት "የመጠለፍ ችግር" አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የሳይበር ደኅንነት ባለሙያዎች "ችግሩ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በፍጥነት ለመቆጣጠር" እንደቻሉ ተገልጿል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር "የችግሩ መንስኤ ከውስጥም ሆነ ከውጪም የማጣራት ሥራ" እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ኤጀንሲው የምርመራ ሥራውን ሲያጠናቅቅ ገፁ ላይ ይህንን አሻጥር በማድረግ የተሳተፉ የድርጅቱ ሠራተኞች መኖራቸው ከተረጋገጠ ተቋሙ ባለው የሥነምግባር ደንብ መሠረት እርምጃ ይወስዳል ብለው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሕግ ፊት ቀርበው እንደሚዳኙ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በምርመራ ሥራው ማጣራት ያለበትን ቴክኒካዊ ጉዳዮች አጣርቶ በቀጣይ ጥንቃቄ ለማድረግ እንዲሁም ግንዛቤ ለመፍጠር ተገቢውን ትምህርት ለመውሰድ በሚያስችል መልኩ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፤ ሲስተሙን የሚያስተዳድሩ፣ የአካውንቱ 'አድሚኖች'፣ አካውንቱ ያላቸው ወይንም አካውንቱን መጠቀም የሚችሉ አንድ ወይንም ከዚያ በላይ የሆኑ ግለሰቦች በአሻጥሩ ተሳትፈው ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል።

"በውስጥ አሻጥር አንዳንድ ጊዜ ባለማወቅ፣ የአካውንቱን ፓስወርድ [የይለፍ ቃል] ማግኘት ከቻሉ፣ ውስጥ ገብተው የሚፈልጉትን ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ኤጀንሲው ጥቃቱ በማን እንደተፈፀመ በግልጽ "ሙሉ በሙሉ ከውስጥ ነው ከውጪ ብሎ ለመናገር" እየሰራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።

ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) ተቋማት አካውንቶቻቸውን የሚያስተዳድሩላቸውን ግለሰቦች በደንብ ማወቅ አለባቸው ሲሉ መክረዋል።

ሌሎች የመገናኛ ብዙኃን፣ የመንግሥትም ይሁን የግል ድርጅቶች ከውጭ ባሉም ሆነ ከውስጥ ባሉ ሠራተኞች የሳይበር ጥቃት ሊፈጸም የሚችል መሆኑን ተረድተው ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የሳይበር ጥቃት

በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መምጣታቸውን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በ2013 ዓ.ም ብቻ ከ2800 በላይ "ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ጥቃቶች" ቢሰነዘሩም ምንም ጉዳት ሳያደርሱ ለመከላከል መቻሉን ተናግረዋል።

የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌትን ተከትሎ ፍላጎት አላቸው ያሏቸው አካላት፣ ከ37 ሺህ በላይ በሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ በኔትዎርክ የተሳሰሩ ኮምፒውተሮች ላይ ጥቃት ሊያደርሱ እንደነበር ገልፀው ይህም በኤጀንሲው የሳይበር ኢንተለጀንስ ቡድን ተለይቶ ሙሉ በሙሉ ማክሸፍ መቻሉን አክለው ገልፀዋል።

የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል በየቀኑ ዝግጅት ያስፈልጋል ያሉት ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር)፣ በየቀኑ ዕይታዎችን መቀየር፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ማጥናት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

ሁልጊዜም፣ የሳይበር ጥቃትን የምንከላከልባቸው ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም በሰለጠነ የሰው ኃይል ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ በተጨማሪም ያለውን የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል አጠቃላይ የአሰራር ሥርዓቶች እንደየተቋሙ እና እንደ ድረገፆቹ ነባራዊ ሁኔታ መኖር እንዳለባቸው ያስረዳሉ።

ከዚህ በተጨማሪም አገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በመዳሰስ፣ ፖለቲካዊ፣ ግለሰባዊ እና የፋይናንስ ፍላጎት ያላቸው አካላት በየት አካባቢ አሉ የሚለው በየጊዜው እየተጠና ኤጀንሲው 24 ሰዓት አገር የመከላከል ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ተቋማት ደግሞ የራሳቸውን መተግበሪያዎች እና ሲስተም በውስጥ ሠራተኞቻቸው አሻጥር እንዳይፈፀምበት መጠበቅ እንደሚያስፈልጋቸው ጨምረው ገልፀዋል።

አማራጭ የማበራዊ ሚዲያ

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኢጀንሲ (INSA) ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ "አማራጭ የማኅበራዊ ድረገጽ" እንዲኖራት ማድረግ የሚያስችል መተግበሪያዎችን መስራቱን ዳይሬክተሩ አክለው ተናግረዋል።

ይህ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ዓለም አቀፍ የሆኑ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለመተካት አማራጭ በመሆን የሚያገለግል እንደሆነ እና ሌሎቹን ከአገልግሎት የሚያስወጣ አለመሆኑን ተናግረዋል።

"እኛ ትልቅ ሕዝብ ነን" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ዓለም አቀፍ የሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ተጠቃሚዎችን "በፈለጉ ጊዜ የሚዘጉበት በፈለጉ ጊዜ የሚከፍቱበት መሆን የለበትም የሚል አቋም አለን" ብለዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም ኢትዮጵያ እንደማንኛውም የዓለም ማኅበረሰብ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ፣ ሌሎች የፖለቲካ ሃሳብ ያላቸው አካላት፣ "የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን እየጠመዘዙ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት ችግር እንዲፈጥሩብን አንፈልግም" ሲሉ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው "ሕዝባችን . . . ሃሳቡን የመግለጽ መብት አለው" ብሎ ስለሚያምን "ለራሳችን አማራጭ የሆነ" ማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ መስራታቸውን ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲጂታል እንዲሁም የሳይበር ሉዓላዊነት አዲስ ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን በማንሳት "ይህንን ታሳቢ በማድረግም የራሳችን የሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ ያስፈልገናል" ብለዋል።

በተጨማሪም "ሌሎች አገሮች አልምተዋል እኛም ማልማት እንችላለን" በማለት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ማኅበራዊ ሚዲያውን ተግባራዊ ለማድረግ ሌሎች መሰራት ያለባቸው ሥራዎች እንደሚቀሩ የተናገሩት ዳይሬክተሩ መቼ ወደ ሥራ እንደሚገባ ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል።

"እነዚህ አሟልተን አማራጭ የሚሆኑ የሶሻል ሚዲያ እና የተግባቦት አማራጮች ለሕዝባችን እያቀረብን እንሄዳለን" ሲሉ አክለዋል።

ኤጀንሲው በአሁኑ ሰዓት በሙከራ ደረጃ እየተጠቀመባቸው ያሉ፣ ደቦ የተሰኘ ስብሰባ ማካሄጃ ፕላትፎርም፣ 'ሲርኩኒ' የሚባል፣ የራሳቸው የሆነ ፋየር ዎል፣ ኤርጋሜል የተሰኘ የኢሜል ሥርዓት፣ እንዲሁም ፀረ ቫይረስ እንዳለ በመግለጽ ይህንን እያሳደጉ እንደሚሄዱ ተናግረዋል።

እነዚህን ከማሳደግ በተጨማሪ፣ በሙከራ እና በእቅድ ደረጃ ያሉ ሌሎች ፕላት ፎርሞችም መኖራቸውን አክለው ተናግረዋል።

እነዚህን ወደ ሰፊው ተጠቃሚ ለማድረስ መሟላት ያለባቸው ትልልቅ መሰረተ ልማቶች መኖራቸውን የገለፁት ዳይሬክተሩ ይህ እንደተሟላ ለኅብረተሰቡ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።