በትግራይ ክልል ለነዋሪዎች የሚቀርበው ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደናቀፍ እና እንዲሻሻል ተጠየቀ

በትግራይ ክልል ለሲቪል ነዋሪዎች የሚቀርበው ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደናቀፍ እና እንዲሻሻል የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ ተገቢውን ሥራ ሊያከናውኑ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ።

በትግራይ ክልል ከፍተኛ የምግብና የጥሬ ገንዘብ እጥረት መከሰቱን፣ የምግብና ሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መናሩን ኮሚሽኑ መስከረም 1/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

ከዚህም በተጨማሪ የነዳጅ አቅርቦትና የትራንስፖርት አገልግሎት ውስን ስለሆነ ነዋሪዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ መቸገራቸውን ተረድቻለሁ ብሏል - ኢሰመኮ።

በአንዳንድ ቦታዎች የተወሰነ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የተመለሰና አንዳንድ ባንኮችም ኔትወርክ ባይኖርም በአካባቢው አስተዳዳሪዎች ትዕዛዝ መሰረት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም አስታውቋል።

ምንም እንኳን የጦርነቱ ወደ አጎራባች ክልሎች መዛመት በሰብዓዊ እርዳታ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚኖረው ኮሚሽኑ እንደሚገነዘብ የገለጸ ሲሆን በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ ግን አሳሳቢ መሆኑን የሚመለከታቸው አካላት ልብ ሊሉት እንደሚገባም በመግለጫው አሳስቧል።

ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ በወንጀል ጉዳይ ተጠርጥረዋል በሚል በቁጥጥር ስር ስለዋሉ የትግራይ ተወላጆች እና የንግድ ቤቶች መዘጋት በርካታ አቤቱታዎች ደርሰውኛል ብሏል።

እነዚህንም አቤቱታዎች መሰረት አድርጎ በሁለት ክፍለ ከተሞች ክትትል ማድረጉን ጠቁሞ የንግድ ድርጅቶቹ የተዘጉት በደንብ መተላለፍ እና በወንጀል በመጠርጠር በሚል አዲስ በተቋቋመውና የሕገ ወጥ ንግድ ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ግብረ ኃይል ውሳኔ ነው ብሏል።

ነገር ግን በርካታ የድርጅቶቹ ባለቤቶች በተጠረጠሩበት ወንጀል ወይም ደንብ መተላለፍ ጉዳይ ውሳኔ ስላልተሰጣቸው ድርጅቶቹ ለረዥም ጊዜ ተዘግተው እንዲቆዩ መደረጉንም የሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ ጠቅሷል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ፖሊስና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የምርመራ ሥራውን በማፋጠን መፍትሄ ሊያበጁለት እንደሚገባም ተጠቁሟል።

በቁጥጥር ስር ያሉት የትግራይ ተወላጆች የተወሰኑት በአዲስ አበባ ከተማ እና አፋር ክልል ወደሚገኙ ወታደራዊና የፖሊስ ካምፖች መወሰዳቸውንና ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከጠበቆቻቸው ጋር ያልተገናኙና ፍርድ ቤትም ያልቀረቡ እንዳሉ ለማወቅ እንደቻለም ገልጿል።

ማንኛውም ተጠርጣሪ በሕጋዊ መንገድ ሊያዝና ሕጉ በሚያዘው የጊዜ ገደብ ውስጥ ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚገባም ኢሰመኮ በመግለጫው ላይ አፅንኦት ሰጥቷል።