ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር በፕሬዚዳንቱ ግድያ ላይ ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠየቁ
የሄይቲ ዋና አቃቤ ህግ በፕሬዚዳንት ጆቬኔል ሞይሴ ግድያ ዋና ተጠርጣሪ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያብራሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሄንሪን ጠይቀዋል።
የሄይቲ ፕሬዚዳንት ጆቬኔል ሞይሴታጣቂዎች ቤታቸውን ሰብረው ገብተው በጥይት የገደሏቸው በሃምሌ ወር ነው ።
አቃቤ ህጉ ቤድፎርድ ክላውድ እንዳስረዱት ፕሬዚዳንቱ ከተገደሉ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሄንሪ ከተጠርጣሪው ጆሴፍ ፊሊክስ ባዲዮ ጋር ብዙ የስልክ ጥሪ ማድረጋቸውን ነው።
አቃቤ ህግ ቤድፎርድ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በይፋ የመጥራት ስልጣን ስለሌላቸው እንዲገኙ "ተጋብዘዋል" ብለዋል።
አቃብያነ ህግ እንደሚሉ ዲጂሴል ከተባለው የቴሌኮም ኩባንያ መዛግብት እንደተገኘው ፕሬዚዳንቱ በተገደሉበት ዕለት ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ተጠርጣሪው ጆሴፍ ፊሊክስ ባዲዮ ሁለት ጊዜ መነጋገራቸውን አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት የት እንዳለ የማይታወቀው ተጠርጣሪ በፕሬዚዳንቱ ግድያ ወቅት ወንጀሉ ከተፈጸመበት ስፍራ አካባቢ መገኘቱንም መረጃዎች ጠቁሟል።
አቃቤ ህጉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ ግብዣው አማራጭ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል ፣ ግን "ለሀገሪቱ እጅግ ከባድ ጉዳይ" ከመሆኑ አንፃር ምክንያታዊ ነው ብለዋል።
ችሎቱ በፖርት ኦው ፕሪንስ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ማክሰኞ በ4 ሰዓት ይካሄዳል።
በፍትህ ሚኒስቴር ውስጥ የቀድሞ ባለስልጣን የነበረው ጆሴፍ ፊሊክስ ባዲዮ ግድያውን በማስተባበር ተሳትፎ ሊሆን ይችላል ሲሉ መርማሪዎች ክስ መስርተዋል። በእነዚህ ክሶች ላይ በይፋ አስተያየት አልሰጠም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጆሴፍ ፊሊክስ በግድያው ተሳትፏል ብለው እንደማያምኑና ምክንያቱም አቅም የለውም በማለትም ለአገሪቱ ሚዲያዎች ተከላክለው ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ቃል አቀባይ ለፍርድ ቤቱ ግብዣ አስተያየት እንደማይሰጡ ለአሶሺየትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ባለስልጣናት በግድያው ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚያደርጉትን ጥረት በእጥፍ አሳድገዋል።
ፖሊስ እንዳስታወቀው ከግድያው ሴራ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት 44 ሰዎች በቁጥጥር ስር ያዋሉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 18 ጡረታ የወጡ የኮሎምቢያ ጦር አባላት አሉበት።