ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተመድ እና ኢሰመኮ በትግራይ ክልል የመብት ጥሰት ምርመራ የመስክ ሥራ መጠናቀቁን ገለጹ
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል የሚያካሂዱት የመብት ጥሰት ምርመራ የመስክ ሥራ መጠናቀቁን አስታወቁ።
ተመድ እና ኢሰመኮ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየመረመሩ እንደሆነ ይታወቃል።
ጦርነቱን ተከትሎ በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ሁሉም አካላት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስለመፈጸማቸው በተደጋጋሚ ተዘግቧል።
ሁለቱ አካላት በጋራ ባወጡት መግለጫ የምርመራ ውጤት የሆነው ሪፖርት ጥቅምት 22/2014 ዓ. ም ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ኢሰመኮ ከግንቦት 8 እስከ ነሐሴ 14/2013 ዓ. ም ድረስ በመቀለ፣ ውቅሮ፣ ሳምረ፣ አላማጣ፣ ቦራ፣ ማይጨው፣ ዳንሻ፣ ማይካድራ፣ ሑመራ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር እና አዲስ አበባ ምርመራዎችን አከናውነናል ብለዋል።
የምርመራ ቡድኑ 200 የጥቃት ሰላባዎች እና የዓይን እማኞችን ከማነጋገሩ በተጨማሪ፤ የክልል እና የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የሲቪል ማኅበራትን፣ የእምነት ተቋማትን፣ የጤና እና የፍትሕ ባለሥልጣናትን እንዲሁም በትግራይ የሚንቀሳቀሱ በጎ አድራጊ ድርጅቶችን አነጋግሯል ብለዋል።
በተጨማሪም መርማሪ ቡድኑ ፎቶ፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን እና ሰነዶችን መርምሯል።
ምንም እንኳን በፀጥታ ችግር እና በሌሎች ምክንያቶች መርማሪ ቡድኑ ያልተጓዘባቸው ስፍራዎች ቢኖሩም፤ ከእነዚህ አካባቢዎች ሸሽተው የወጡ ተፈናቃዮችን እንዳነጋገረ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ኢሰመኮ ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ ተመልክቷል።
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚቼል ባችሌት፤ በትግራይ ክልል ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና ጥምር የምርመራ ሥራው የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ መስከረም 3/2014 ዓ. ም ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሪፖርት ያቀርባሉ።
ከሚቼል ባችሌት በመቀጠል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዳይሬክተር ዶ/ር ዳንኤል በቀለን ጨምሮ ሌሎች አካላትም ንግግር ያደርጋሉ።
ሚቼል ባችሌት በርካታ የደኅንነት እና የሎጂስቲክ ፈተናዎች ቢኖሩም ጥምር መርማሪ ቡድኑ ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መንገድ በትግራይ ክልል ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዝርዝር እና ገለልተኛ ምርመራ ማካሄድ ችሏል ብለዋል።
የኢሰመኮ ዳይሬክተር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው፤ የምርመራ ቡድኑ በገለልተኝነት፣ በግልጸኝነት እና በሚስጥር ጠባቂነት መርሆች እንደሚመራ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የተመድ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥምር ቡድን የተሰበሰቡ መረጃዎችን እየመረመረ ይገኛል።
ሙሉ የምርመራ ውጤቱ ጥቅምት 22/2014 ዓ. ም ይፋ ከመሆኑ በፊት መርማሪ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት የተሰበሰቡ መረጃዎችን በመተንተን ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።