ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለጡረታ ገንዘብ ብሎ የእናቱን አስከሬን የደበቀው የኦስትሪያ ዜጋ በቁጥጥር ሥር ዋለ
አንድ የኦስትሪያ ዜጋ የጡረታ ክፍያ ለመቀበል በሚል የእናቱን ሞት በመደበቅ ብሎም አስከሬናቸውን ከአንድ ዓመት በላይ በመኖሪያ ቤታቸው ከወለል በታች ባለ ክፍል ማቆየቱን ፖሊስ አስታወቀ።
ባለፈው ሰኔ ወር በተፈጥሯዊ ምክንያት አንደሞቱ የተነገረው የ89 ዓመቷ እናቱን አስከሬን ሽታ እንዳያመጣ በተለያዩ መንገዶች ማቆየቱም ተነግሯል።
የ66 ዓመቱ ልጅ በረዶ የያዙ ከረጢቶችን እንዲሁም ፋሻ በመጠቀም ሽታውን ለመደበቅ ሞክሯል ተብሏል።
ፖሊስ ግለሰቡ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ 50 ሺህ ዩሮ የጡረታ ክፍያ ተቀብሎ ሊሆን እንደሚችል እንደሚያምን አስታውቋል።
የግለሰቡ ተግባር ፖሊስ ጆሮ እንዲደርስ ያደረገው የሟችን ጥቅማ ጥቅሞች ይዞ ወደ መኖሪያቸው ያመራው የፖስታ አገልግሎት ባልደረባ ነበር።
ግለሰቧን ለማግኘት በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ሊያገኛቸው አለመቻሉን ተከትሎ ፖሊስ ምርመራ ማድረግ መጀመሩን እና ይህም አስደንጋጭ ወደሆነው ክስተት ማምራቱን ፖሊስ ገልጿል።
ግለሰቡ ለአንድ ዓመት ሲጠቀም በነበራቸው ስልቶች ምክንያት ፖሊስ አስከሬኑን ሲያገኝ ደርቆ እንደነበር ገልጿል።
የሟች ልጅ ይህንን ያደረገው ሌላ ገቢ ስለሌለው መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱን ማመኑን የፖሊስ መግለጫ ያመለክታል።
የእናቱን ህልፈት ይፋ ካደረገ ክፍያዎች ወዲያውኑ እንደሚቆሙ እና ለእናቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወጪዎች ለመክፈል ብሎም የሚኖሩበትን ቤት ለማቆየት አቅም እንዳልነበረው መግለጹን ፖሊስ ተናግሯል።
ተጠርጣሪው ለወንድሙ እናታቸው በሆስፒታል እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሆነ እና እናታቸውን ለመጠየቅ ቢመጡም እንደማያስታውሷቸው በመግለጽ እንዳሄዱ እንዳደረጋቸው ኦአርኤፍ ዘግቧል።