አፍጋኒስታን፡ ባይደን አሜሪካ ካቡልን የመልቀቅ ጥረቷ አጠናክራለች አሉ

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሰዎችን ከካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ለማውጣት የሚደረገው ጥረት እየተፋጠነ ነው ብለዋል።

ነሐሴ 9 ላይ ታሊባን ስልጣን መያዙን ተከትሎ ብዙ ሺህ አፍጋኒስታናዊያን አገሪቱን ለመልቀቅ በሚያደርጉት ጥረት በአውሮፕላን ማረፊያው በሮች ላይ ወረፋ ይዘው እየተጠባበቁ ነው።

ባይደን እሁድ ዕለት እንዳሉት አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ወደ 28 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ከአፍጋኒስታን አስወጥታለች።

ባይደን በዋይት ሃውስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሰዎችን ያለ ስቃይ እና አሳዛኝ ባልሆነ ሁኔታ ከአፍጋኒስታን ማስወጣት ቀላል አይደለም ብለዋል።

"በአውሮፕላን ማረፊያው ዙሪያ ያለውን ደህንነቱ የተጠበቀ ቀጠናን ማስፋትን ጨምሮ ለውጦችን አድርገናል። ገና ብዙ ይቀረናል። አሁንም ብዙ ስህተት ሊኖር ይችላል"ብለዋል።

ቀደም ሲል ፔንታጎን 18 የንግድ አውሮፕላኖች ከአፍጋኒስታን ውጭ ካሉ ደህንነታቸው ከተጠበቁ ስፍራዎች ሰዎችን ወደ ሦስተኛ አገር ለማዛወር ጥቅም ላይ ይውላሉ።

ከካቡል አየር ማረፊያ ውጭ በሺህዎች በሚቆጠሩ ተሰልፈው ያሉ ሲሆን ቢያንስ 20 ሰዎች መሞታቸውን አንድ የኔቶ ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

እሑድ ዕለት የነበረው ትዕይንት ካለፉት ቀናት የተሻለ መረጋጋት የታየበት ነው ተብሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጦር ኃይሎች ሚኒስትር ጄምስ ሂፔይ እንዳሉት ታሊባኖች በሐሚድ ካርዛይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመውጣት ተስፋ ያላቸውን ሰዎችን በማስተባበር እና ወረፋ በማስያዝ ለሂደቱ ፍጥነት እገዛ አድርገዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከነሐሴ 7 ጀምሮ 5,725 ሰዎችን ማስወጣቷን የመከላከያ ሚኒስቴር እሑድ ዕለት ገልጿል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከ1000 በላይ የጦር ኃይሎች ሠራተኞቿ በካቡል ተሰማርተዋል።

እሑድ ዕለት የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ሰዎችን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ይረዳው ዘንድ የሲቪል አየር መንደጎች አውሮፕላን ጥቅም ላይ እንዲውሉ አስደርጓል።

በመግለጫው መሠረት ከዩናይትድ እና አሜሪካን አየር መንገዶች ጨምሮ 18 አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ይውላሉ።

የሲቪል የአየር መንገዶች ጥቅም ላይ መዋል ወታደራዊ አውሮፕላኖች በካቡል ውስጥ እና ውጭ በሚደረጉ ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ይረዳቸዋል ሲል መግለጫው አክሏል።

ባይደን ትናንት "እነዚህ የሲቪል በረራዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ ጉዞን ወደ ሦስተኛ አገራት ለማመቻቸት ይረዳሉ በካቡል አየርፉም" ብለዋል።

የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመለየት በበርካታ አገራት "የማጣሪያ ጣቢያዎች" መቋቋማቸውን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

የጂ7 አገራት ጥሪ

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የዓለማችን ሰባቱ ታላላቅ ኢኮኖሚ ባለቤቶች ተብለው የሚጠሩት የጂ7 መሪዎችን አስቸኳይ ስብሰባ እንዲካሄድ ጠርተዋል።

"ደህንነቱ የተጠበቀ የማስወጣት ሥራ ለማከናወን፣ የሰብዓዊ ቀውስን ለመከላከል እና የአፍጋኒስታን ህዝብ ባለፉት 20 ዓመታት ያገኘውን ደህንነትን ለመጠበቅ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጋራ መሥራቱ አስፈላጊ ነው" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር በበኩላቸው አሜሪካ ከአፍጋኒስታን መውጣቷን ክፉኛ ተችተዋል።

"በዓለም ዙሪያ ሲያማትሩ እና ይህንን ውሳኔ በእውነት የሚያደንቁት ብቸኞቹ ሰዎች የምዕራባውያን ፍላጎቶችን የሚቃወሙት ሰዎች ናቸው" ብለዋል።

አሜሪካ ከነሐሴ 25 በፊት ሁሉንም ወታደሮቿን ከአፍጋኒስታን ሙሉ በሙሉ ለማውጣት አቅዳለች።